ቻይና ለትራምፕ የታሪፍ ዛቻ ምላሽ የሚሆን "የአጸፋ እርምጃ" ማዘጋጀቷን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና መንግሥት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቤጂንግ ወደ ዋሽንግተን በሚገቡ ምርቶች ላይ 100 በመቶ ቀረጥ ለመጣል መዛታቸውን "ቁልጭ ያለ የአድሏዊነት ምሳሌ ነው" በማለት ተቸ።
አሜሪካ ይህንን ዛቻዋን ተፈጻሚ ማድረግ የምትጀምር ከሆነ ቻይና በምላሹ የምትወስደውን "የአጸፋ እርምጃ" እንዳዘጋጀች የአገሪቱ ንግድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ተናግረዋል። የአጸፋ እርምጃው ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል ግን አልተገለጸም።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ ቻይና ከአሜሪካ ጋር የንግድ ጦርነት ቢጀመር ሊያመጣ ስለሚችለው መዘዝ "እንደማትፈራ" አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ላይ ታሪፍ ለመጣል የዛቱት አገሪቱ ብርቅዬ የምድር ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ማቅረብን በተመለከተ የምትከተለውን ህግ በማጥበቋ ነው። ቻይና "እጅግ ጠበኛ እየሆነች መጥታለች" እንዲሁም መላው ዓለምን "እስረኛ" አድርጋ ለመያዝ እየሞከረች ነው በማለት ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ከስሰዋል።
ትራምፕ፤ በዚህ ወር በቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ ጋር ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን ስብሰባ እንደሚያቋርጡም ዝተዋል።
እሁድ ዕለት ግን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት "አትስጊ ቻይና፤ ሁሉም ደህና ይሆናል" በማለት ጽፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ "እጅጉን የተከበሩት ፕሬዝዳንት ዢ መጥፎ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። አገሪቱ [የኢኮኖሚ] ድብርት ውስጥ እንድትገባ አይፈልጉም፤ እኔም አልፈልግም። አሜሪካ ቻይናን ማገዝ እንጂ መጉዳት አትፈልግም" ብለዋል። ዝርዝር ጉዳዮችን ግን ሳያብራሩ ቀርተዋል።
ትራምፕ አርብ ዕለት ቻይና ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ መናገራቸው በአሜሪካ የፋይናንሻል ማርኬት ላይ ነውጥ አስከትሏል። እንደ 'ኤስ ኤንድ ፒ 500' ያሉ የአክስዮን ጠቋሚዎችን ከሚያዝያ ወር ወዲህ ትልቅ የተባለውን የ2.7 በመቶ ቅናሽ አሳይተዋል።
የፕሬዝዳንቱ አስተያየት ቻይና እና አሜሪካ የንግድ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚለውን ስጋት እንደ አዲስ ቀስቅሶታል።
ሁለቱ አገራት አንዳቸው በሌላኛቸው ምርት ላይ በመቶዎች ፐርሰንት የሚቆጠር ታሪፍ ለመጣል ከተዛዛቱ በኋላ ግንቦት ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በወቅቱ የነበረው መካረር በአገራቱ መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር።
የቻይና ንግድ ሚኒስቴር ሰሞነኛውን ዛቻ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ በጽሑፍ የሰጠው ምላሽ ከወራት በፊት አገራቱ ተመሳሳይ መካረር ውስጥ ገብተው በነበረበት ወቅት ይስተጋቡ የነበሩ ቃላትን ያንጸባረቀ ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ አሜሪካ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለመስራት የሚውሉት 'ቺፕ' እና 'ሰሚ ኮንዳክተር' ወደ ቻይና እንዲላኩ ገደብ መጣሏን ተችቷል።
ቤጂንግ ብርቅዬ የምድር ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ማቅረብን በተመለከተ ሕጓን ማጥበቋ የቻይናን እና የሁሉም አገራትን ብሔራዊ ደህንነነት ለማስጠበቅ የተወሰደ "መደበኛ እርምጃ" እንደሆነ በመግለጽ ተከላክሏል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ፤ አሜሪካ "ለረጅም ጊዜ" ያህል "ብሔራዊ ደህንነት የሚለውን ሀሳብ በመለጠጥ የውጭ ገበያ ቁጥጥር እርምጃዎች አላግባብ ተጠቅማለች" ብለዋል።
"ቻይና ላይም አግላይ ልምምዶችን ተግብራለች" በማለት ተችተዋል።
"የታሪፍ ማስፈራሪያዎችን መጠቀም ከቻይና ጋር ግንኙነት ለማድረግ ትክክለኛ መንገድ አይደለም" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም፤ "የቻይና የታሪፍ ጦርነትን በተመለከተ ያላር አቋም ሁል ጊዜም ወጥነት ያለው ነው። እንዲኖር አንፈልግም፤ ግን አንፈራም" በማለት ለአሜሪካ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቻይና ብርቅዬ ማዕድናት እና ለላቀ የቴክኖሎጂ ምርት በሚውሉ ሌሎች ወሳኝ ቁሶችን የተመለከተ ሕጓን ያጠበቀችው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ብርቅዬ ማዕድናት እንደ የሶላር ፓኔሎች እና ስማርት ስልኮች ያሉ ምርቶችን ለመስራት የሚያገለግሉ ሲሆን በዓለም ላይ የእነዚህ ማዕድናት 90 በመቶው ክምችት የሚገኘው ቻይና ውስጥ ነው።
ዋሽንግተን እና ቤጂንግ ሊያደርጉት ካቀዱት ንግግር በፊት እነዚህን እርምጃዎች እንደሚወስዱ መዛታቸው በሁለቱ መሪዎች በስብሰባቸው ወቅት ጠንካራ አቋም ይዞ ለመገኘት የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በዚህ ወር በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የትራምፕ እና ዢ ስብሰባ እንደታቀደው ይካሄድ እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።















