በሐማስ ታግተው ስለተወሰዱ እስራኤላውያን እስካሁን የምናውቀው

የፎቶው ባለመብት, TWITTER
በጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እስራኤላዊ ሰላማዊ ሰዎች እና ወታደሮች በፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ ታግተው እንደሚገኙ የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
የተወሰኑት በሕይወት ያሉ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ እንደሞቱ እንደሚገመት የጦሩ ቃል አቀባይ ሌተናንት ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት በታጣቂ ቡድኑ ከተወሰዱት መካከል ሕጻናት ፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል።
“እነዚህ ቁጥሮች ሊታሰቡ የማይችሉ ናቸው።ይህ የዚህን ጦርነት የወደፊት ሁኔታ ይወስናል።” ብለዋል።
ሃማስ በበኩሉ የተያዙት እስራኤላውያን ከደርዘን በብዙ እጥፍ እንደሚበልጡ እና ወደ ጋዛ ሰርጥ እንደተወሰዱ ገልጿል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለእስራኤላውያኑ ደኅንነት ሃማስ ተጠያቂ እንደሆነና “በጎዳቸው ላይ እስራኤል ሂሳብ እንደምታወራርድ” ተናግረዋል።
ምስሎች እስራኤላውያን ከቤታቸው ሲወሰዱ አሳይተዋል
እስራኤላውያን በሐማስ ተዋጊ እጅ ውስጥ እንዳሉ የሚያሳዩ በኦንላይን የሚዘዋወሩ በርካታ ቪዲዮዎች አሉ።
አንድ በቢቢሲ የተረጋገጠ ቪዲዮ እስራኤላውያን ታጋቾችን ይዟል የተባለ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ በጋዛ ሰርጥ ሰዎች በተሰበሰቡበት አካባቢ ሲያልፍ ያሳያል።
የጋዛ ሰርጥን በሚያሳይ ሌላ ቪዲዮ ደግሞ በባዶ እግሯ የሆነች ሴት በደም የተጨማለቁት እጆቿ ወደኋላ የፊጥኝ ታስረው ከመኪና ኋላ ስትጎተት ያሳያል።
ጥንዶች ከቤት ውጭ ይካሄድ ከነበረ ድግስ (ፓርቲ) ላይ ተወስደዋል
የተወሰኑ ታጋቾች ከጋዛ ብዙም በማትርቀውና በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል ከምትገኘው ኦፋኪም ከተማ፣ በኪቡዝ ሬኢም፣ ከቤት ውጭ ይካሄድ ከነበረ ድግስ (ፓርቲ) ላይ እንደተወሰዱ ተነግሯል።
የዓይን ምስክሮች ለእስራኤል ሚዲያ እንደተናገሩት ከሆነ በሞተር ሳይክል የመጡ ጥቃት ፈፃሚዎች በታዳሚዎች ላይ የተኩስ እሩምታ የከፈቱ ሲሆን በርካቶችም እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩና በቢቢሲ ያልተረጋገጡ ቪዲዮዎችም በፓርቲው ላይ ታድማ የነበረች አንዲት ሴት ታግታ በሁለት ወንዶች ተይዛ በሞተር ሳይክል ስትወሰድ አሳይተዋል።
ይህች እስራኤላዊት ኖዋ አርጋማኒ እንደምትባል የባለቤቷ ወንድም ሞሸ ኦር ተናግሯል።
ሞሼ እርሷና ወንድሙ በበርካታ ታጣቂዎች ተይዘው በቪዲዮዎች ላይ ከማየቱ በፊት መጥፋቷን አሳውቋል።
“ ኖዋን በቪዲዮው ላይ ተጨንቃ እና ፈርታ አይቻታለሁ። በአዕምሮዋ ምን እያሰላሰለች እንደሆነ መገመት አልችልም። በሞተርሳይክሉ ላይ በድንጋጤ ስትጮኽ ነበር” ሲል ኦር ከእስራኤሉ ቻነል 12 ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግሯል።
ሌላ በቢቢሲ ያልተረጋገጠ ቪዲዮም በጋዛ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ኖዋ ውሃ ስትጎነጭ የሚመስል ምስል አሳይቷል።
በእስራኤል ከተሞች ውስጥ ስላሉ እገታዎች
የእስራኤል ጦር ኃይል በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙና ከጋዛ ሰርጥ ውጭ በሆኑ ሁለት ቦታዎች ታግተው የነበሩ ሰላማዊ እስራኤላውያንን ማስለቀቁ ተዘግቧል።
በኪቡትዝ ቤሪ የእገታ ቦታ በመመገቢያ ክፍል ውስጥ ታግተው የነበሩ እስራኤላውያንን ከ18 ሰዓታት በኋላ መታደግ እንደተቻለ የእስራኤል የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
የእስራኤል ሚዲያዎች እንደዘገቡት እዚህ ቦታ ላይ 50 የሚደርሱ ሰዎች ታግተው ነበር።
ኢላ የተባለች ሴት በከተማዋ ውስጥ በተዘጋ እና የጦር መሣሪያ ጥቃት በሚከላከል መጠለያ ለሰዓታት እንደቆየች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች።
“ ብዙ የተኩስ ድምጽ ይሰማናል። ከዚያም ሽብርተኞቹ በመመገቢያ ክፍሉ ውስጥ እንዳሉ ተነገረን። ብዙ ጥይት ይሰማናል። ከቤተሰቦቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት ተቋርጧል። አባቴ መታገቱን አውቃለሁ። ምን እየተካሄደ እንዳለ ማንም ሊነግረን አልቻለም። እናቴ በሕይወት ስመኖሯም አላውቅም።” ብላለች።
በቢቢሲ በተረጋገጠው ቪዲዮ በቤሪ ሰዎች በባዶ እግራቸው ሆነው በታጣቂዎች እየተነዱ ሲወሰዱ አሳይቷል። እነዚህ ሰዎች በመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ የታገቱት ሰዎች ይሁኑ አይሁኑ ግን ግልጽ አይደለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በፋኪም ከተማ በምትገኘው ኪቡትዝ ኡሪም፣ ቅዳሜ ዕለት ሁለት እስራኤላውያን በሐማስ ታጣቂዎች ከተወሰዱ እና ለሰዓታት ታግተው ከቆዩ በኋላ መታደግ መቻሉን የእስራኤል የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ካን ዘግቧል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የሮኬት ማስጠንቀቂያ ከተሰማ በኋላ ነዋሪዎች ከቦምብ በሚከላከል መጠለያ ለመግባት ሲሞክሩ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ተኩስ ከፍተዋል።
ሁለት ነዋሪዎች በመኖሪያ አፓርታማቸው ውስጥ የነበሩ ሲሆን በአራት ታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል። በኋላ ላይ ታጣቂዎቹ በእስራኤል ጦር ተገድለዋል።
በነፍስ አድን ሥራውም ሦስት የእስራኤል ወታደሮች ቀላል እና መጠነኛ ጉዳት እንዳጋጠማቸው ካን ዘግቧል።












