ሴራ ሊዮን በሥራ ቅጥር እና በኃላፊነት ቦታዎች ሴቶች ቢያንስ 30 በመቶውን እንዲይዙ ወሰነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴራ ሊዮን የሴቶችን በመንግሥት እና በግል ተቋማት ውስጥ የኃላፊነት ቦታን የመያዝ እና የሥራ ቅጥር መብትን በማስከበር ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ያስችላል የተባለ ታሪካዊ ሕግ አፀደቀች።
ሴራ ሊዮን ያወጣችው ይህ አዲስ ሕግ ‘የጾታ እኩልነት እና ሴቶችን የማብቃት ድንጋጌ’ የሚባል ሲሆን በሥራ ቅጥር ሂደት ውስጥ በሴቶች ብቻ የሚያዙ ቦታዎች ተለይተው እንዲቀመጡ የሚያዝ ነው።
ረቂቅ ሕጉ ለአገሪቱ ፓርላማ ከቀረበ ከአንድ ዓመት በኋላ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በሙሉ ድምጽ ከጸደቀ በኋላ፣ አሁን ደግሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮም ተቀብለውት ሕግ ሆኖ እንዲተገበር ፈርመውበታል።
በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ካሏቸው አጠቃላይ የሥራ ቦታዎች 30 በመቶው በተለየ ሴቶች ብቻ የሚቀጠሩባችው እንዲሆኑ የሚያስገድድ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከኃላፊነት ቦታዎቹም 30 በመቶው በሴቶች እንዲያዝ ያዛል።
የሴራ ሊዮን የሥርዓተ ጾታ ሚኒስትር የሆኑት ማንቲ ታራዋሊ አዲሱን ሕህ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “አሁን ሴራ ሊዮን ከጾታ እኩልነት አንጻር ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ በጥንቃቄ የተቀረጸ ሕግ አለኝ ለማለት ያስቻለ ታሪካዊ ውሳኔ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም “ይህ በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ በጣም ወሳኝ እርምጃ ነው። ነገር ግን ከጾታዎች አንጻር የሚጠበቀውን እኩልነት አረጋግጠናል ከማለታችን በፊት ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።
በአዲሱ ሕግ መሠረት በመንግሥት እና ሕዝባዊ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በምርጫም ሆነ በሹመት ከሚያዙ ኃላፊነቶች 30 በመቶው በሴቶች የሚሸፈን መሆን አለበት።
ለሴቶች ተጨማሪ የቅጥር ዕድል ካመቻቸው አዲስ ሕግ በተጨማሪ አዲሱ ሕግ በሚሰሩባቸው ቦታዎች ካሉ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ውስጥ በሴቶች መያዝ አለባቸው የተባሉ ቦታዎችም ተለይተው እንዲቀመጡ ያደርጋል።
እንዲሁም ቢያንስ አምስት ወራት የወሊድ ፈቃድ፣ ከባንክ ብድር ለማግኘት እንዲችሉ ማድረግ እና የተለያዩ የሥልጠና ዕድሎች እንዲመቻቹላቸው ይደረጋል ተብሏል።
አዲሱ ሕግን ተከትሎ የጾታ የቅጥር ምጥጥኑን ተግባራዊ በማያደርጉት ቀጣሪዎች ላይ ከባድ ቅጣት የሚጣል ሲሆን፣ ሴቶች የሚገባቸውን የብድር እና ሌሎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ ያደረጉ የመዋዕለ ነዋይ ተቋማት ከሆኑ ደግሞ እስር ቅጣትም ይጠብቃቸዋል።
ይህ ጠንካራ ቅጣት ሴቶች በሥራው መስክ እኩል ዕድል እንደያገኙ ከማድረጉ ባሻገር የራሳቸውን ሥራም እንዲጀምሩ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ያደርጋል ተብሏል።
የሴራ ሊዮን መንግሥት ተግባራዊ እንዲሁን ካወጣው ሕግ ውስጥ ሠራተኞች ቁጥር ሴቶችን ያካተተ እንዲሆን የሚያዘው ክፍል ከ25 በላይ ሠራተኞች ባሏቸው ድርጅቶች ውስጥ ሁሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።












