ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት አደረሰች

ጥቃት የደረሰበት የካርኪፍ ግዛት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ አዲስ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት እንደፈጸመች የዩክሬን ባለስልጣናት ገለጹ።

በዚህ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት በካርኪቭ እና ኦዴሳ ክልሎች የመኖሪያ ህንጻዎችና መሰረተ ልማቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

በዚህ ጥቃትም በበርካታ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ መቋረጡንም የክልሎቹ አስተዳደር ገልጸዋል።

በኦዴሳ የወደብ ከተማ የሚገኘው የኃይል ማዕከል ላይ ከፍተኛ የሚሳኤል ጥቃት በመድረሱም መብራት መቋረጡንም የግዛቱ አስተዳዳሪ ማክሲም ማርቸንኮ ተናግረዋል።

በጥቃቱ የመኖሪያ አካባቢዎች ቢመቱም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱንም አክለው ገልጸዋል።

የካርኪፍ ግዛት አስተዳዳሪ ኦሌግ ሴኔጉቦቭ በበኩላቸው ሩሲያ አስራ አምስት የሚጠጉ የሚሳኤል ጥቃቶችን በከተማዋና በክልሉ ላይ አድርሳለች ብለዋል።

በዚህም በአካባቢው ወሳኝ የሚባሉ የመረተ ልማት አውታሮችና የመኖሪያ ህንጻዎች የተመቱ ሲሆን ዒላም መደረጋቸውንም ነው የገለጹት።

ማዕከላዊ ክልሎች ዲኒፕሮና ፖልታቪያ እንዲሁም በምዕራብ ዩክሬን የሚገኙት ቪንይቲሲያ እና ራቪን ክልሎችም ተጨማሪ ጥቃቶች መድረሳቸው ተገልጿል።

የአሜሪካ የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር አቭሪል ሄይን ረቡዕ እለት እንደገለጹት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቱን ጦርነቱን ለዓመታት ሊያራዝሙት ይችላሉ ብለዋል።

ነገር ግን ሩሲያ በዚህ ዓመት አዳዲስ ጥቃቶችን ለመፈጸም የሚያስችል ጥንካሬ የላትም ሲሉም ተናግረዋል።

በዩክሬን ጦርነት ሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሌለም ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት።

“የሩሲያ ጦር በዚህ ዓመት በበቂ ሁኔታ አገግሞ ግዛቶችን ይቆጣጠራል ብለን አናስብም። ነገር ግን ፑቲን ወቅቱ ለሱ ጠቃሚ እንደሆነ በማስላት ጦርነቱን መሃል፣ መሃል ላይ ረገብ በማድረግ ለረዥም ጊዜ መቀጠል ያስባል። በዚህም ዓመታት ቢፈጅም በዩክሬን ውስጥ የሩሲያን ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ያስባል” ሲሉም ተናግረዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸሙ አንድ ዓመትን አስቆጥረዋል።

በጦርነቱም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች እና ሲቪሎች ተገድለዋል፣ በርካቶች የአካል ጉዳተኞች ሆነዋል እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ስደተኞች ሆነዋል።