በሕንድ አንድ ተፈላጊን ለመያዝ ፖሊስ እያካሄደ ባለው አሰሳ ምክንያት ኢንተርኔት ተዘጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፖሊስ አንድ የእምነት ሰባኪን ለመያዝ ከከፈተው አሰሳ ጋር በተያያዘ ፑንጃብ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ውስጥ የመልዕክት መለዋወጫ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተነገረ።
እራሱን የእምነት ሰባኪ ነኝ የሚለውን አወዛጋቢውን አምሪትፓል ሲንግን ለመያዝ ከቅዳሜ ጀምሮ ፖሊስ ሰፊ አሰሳ እያካሄደ ሲሆን፣ ለዚህም ጥብቅ የደኅንነት ቁጥጥር እየተደረገ ከመሆኑ በተጨማሪ ኢንተርኔት ተቋርጧል።
የ30 ዓመቱ የእምነት ሰባኪ የሲኮች የመኖሪያ አካባቢ የሆነውን ግዛት ለመገንጠል የሚንቀሳቀሰውን ኻሊስታን የተባለውን ቡድን እንደሚደግፍ ተነግሯል።
ፖሊስ እስካሁን ድረስ በርካታ የግለሰቡን ረዳቶች እና ደጋፊዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ተነግሯል።
ፖሊስ ይህንን ሰፊ ዘመቻ የጀመረው፣ የሲንግ ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች እንዲለቀቁ በመጠየቅ አንድ ፖሊስ ጣቢያን ከወረሩ ከሳምንታት በኋላ ነው።
ባለፈው ቅዳሜ ፖሊስ ሲንግን “ተፈላጊ” ብሎ በማወጅ በመላው የፑንጃብ ግዛት ግለሰቡን ለመያዝ አሰሳ ጀምሯል። መንገዶች ላይ ኬላዎችን በማቆምም በተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ እየተደረገ ነው።
ባለፉት ሁለት ቀናት ፖሊስ ባካሄደው አሰሳ እና ፍተሻ የተፈላጊው ረዳቶች እና የቅርብ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተነገረ ሲሆን፣ ሲንግም ለጥቂት በፖሊስ ከመያዝ ማምለጡ ታውቋል።
የፖሊስ ባለሥልጣናት እንዳሉት ሲንግ እና ረዳቶቹ ሲጓዙባቸው ከነበሩ ተሽከርካሪዎች መካከል ሦስት መኪኖች እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች ተይዘዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የተፈላጊው ተባባሪዎች በፖሊስ የተያዘዙ ሲሆን፣ በሲንግ እና በተባባሪዎቹ ላይ ክስ መመስረቱን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እሁድ ዕለት “ኻሊስታን” የሚል ጽሁፍ ያነገቡ ሰልፈኞች ለንደን ከሚገኘው የሕንድ ኤምባሲ ውጪ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር።
በተጨማሪም አንድ ተቃዋሚ ኤምባሲው ሕንጻ ላይ የተሰቀለውን የሕንድ ሰንደቅ ዓላማን ሲያወርድ በአንድ ቪዲዮ ላይ ታይቷል።
በዚህ የተበሳጩ የሕንድ ባለሥልጣናት ዴልሂ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የዩናይትድ ኪንግደም ዲፕሎማትን በመጥራት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተፈላጊው ግለሰብ የሕግ አማካሪ የሆነው ኢማን ሲንህ ኻራ፣ ሲንግ “በሕገወጥ መንገድ እና በኃይል” በፖሊስ ተይዟል በማለት፣ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ የፑንጃብ እና ሃሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤትን መጠየቁን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱም የፑንጃብ ግዛት መንግሥት ለማክሰኞ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠ አዟል።
በአሁኑ ወቅት ፖሊሶች በግዛቲቱ ውስጥ በሚገኙ በርካታ ጎዳናዎች ላይ በሰልፍ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ሲሆን፣ ሕዝቡንም ሕግ እና ሥርዓት እንዲያከብሩ ጥሪ እያቀረቡ ነው ተብሏል።












