የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ተዋጊዎች በከፍተኛ ቁጥር ቤላሩስ መግባታቸውን ዩክሬን ገለጸች

የቫግነር ቡድን አባላት የቤላሩስ ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ምስሎች እየወጡ ነው

የፎቶው ባለመብት, VOENTV VIA REUTERS

የምስሉ መግለጫ, የቫግነር ቡድን አባላት የቤላሩስ ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ምስሎች እየወጡ ነው

የዩክሬን ድንበር ጥበቃ አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቫግነር ቅጠረኛ ቡድን አባላት ከሩስያ ወደ ቤላሩስ መግባታቸውን ገለፁ።

የድንበር ጥበቃ ዘቡ አሁን ላይ ምን ያክለ የቫግነር ቡድን አባላት ወደ ቤላሩስ እንደተሻገሩ፣ መገኛቸው እና ለምን ወደ ጎረቤት አገር ቤላሩስ መሄድ እንዳስፈላጋቸው እያጣራሁ ነው ብሏል።

አንድ ያልተረጋገጠ ሪፖርት በ60 መኪኖች የተጫኑ የቡድኑ ተዋጊ አባላት ቅዳሜ ጠዋት ከሩስያ ወደ ቤላሩስ ተሻግረዋል ብሎ ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቫግነር የተባለው የሩስያ ቅጠረኛ ቡድን በፕሬዝዳንት ቭላድርሚር ፑቲን ላይ ለ24 ሰዓታት የዘለቀ አመጽ ቀስቅሶ እንደነበረ ይታወሳል።

ይህ ቡድን በአመጹ ወቅት አንድ የሩስያ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ሞስኮ መገስገስ ጀምሮ አመጹ በአጭር እንዲቋጭ ሆኗል።

ሞስኮ ኪዬቭ ላይ በከፈተችው ጦርነት ቫግነር ከፑቲን ቀለብ እየተሰፈረለት ከሩስያ ጦር ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል።

በተለይ በምሥራቅ ዩክሬን የምትገኘውን ባክሙት ከተማን ለመያዝ በተደረገው ደም አፋሳሽ ውጊያ ቫግነር ለሩስያ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ይህ ቡድን በአሁኑ ወቅት በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ያለው ተሳትፎ እየቀነሰ መጥቷል። ከቀናት በፊት አሜሪካ ቅጥረኛው ቫግነር ተዋጊ ቡድን በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ውጊያ ያለው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብላ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቫግነር በፑቲን አስተዳደር ላይ የቀሰቀሰው አመጸ ከከሸፈ በኋላ ቡድኑ ትቅጥ እንዲፈታ ተደርጎ የቡድኑ ተዋጊዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው የሩስያን ጦር መቀላቀል፣ ወደ ቤላሩስ ማቅናት አልያም ትጥቅ ፈትተው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ በፑቲን አስተዳደር አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር።

የቅጠረኛው ቡድን መሪ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ አማራጭ ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ የቭጌኒ አሁን መገኛው የት እንደሆነ በትክክል አይታወቅም።

ቫግነር ትናንት ቅዳሜ የተዋጊዎቹ ቡድን አባላት በቤላሩስ እንደሚገኙ ያወጣውን አጭር መግለጫ የዩክሬን ድንበር ጥበቃ አገልግሎት ቃል አቀባይ አንድሪይ ዴማቼንኮ አረጋግጠዋል።

ቃል አቀባዩ ዩክሬንን በስተሰሜን በኩል በምታወሳነው ቤላሩስ እየሆነ ያለውን ነገር አገራቸው በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን ተናግረዋል።

ቅዳሜ ንጋት ላይ አንድ የቤላሩስ መንግሥት ተቃዋሚ የሆነ የቴሌግራም ቻናል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቫግነር ቡድን አባላት ከሩስያ ተነስቶ ቤላሩስ ገብቷል ሲል መረጃ አካፍሎ ነበር።

እንደ ቴሌግራም ገጹ ከሆነ የቫግነር ቡድን አባላት በአውቶብሶች፣ በከባድ የደረቅ ጭነት መኪኖች እና ፒክአፕ መኪኖች ተጨነው እና በቤላሩስ ፖሊስ ታጅበው ከመዲናዋ ሚንስክ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 85 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ኦሲፖቪችይ ከተማ ተወስደዋል።

የቤላሩስ መንግሥት እስካሁን ድስረ የቡድኑ አባላት ወደ አገሪቱ ስለመግባታቸው ያለው ነገር ባይኖርም፤ ዓርብ ዕለት ግን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የቫግነር ተዋጊዎች ለአገሪቱ ጦር ሠራዊት እንደ አሰልጣኝ ሆነው እየሰሩ ነው ብሎ ነበር።

“በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች” የቫግነር ተዋጊዎች ለቤላሩስ ጦር ሠራዊት አባላት ስልጠና እየሰጡ ነው በኋላ የቤላሩስ መከላከያ ሚኒስቴር።

ይህ ቡድን ተሰማርቶ በሚገኝባቸው አገራት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ እና ከጦር ወንጀሎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።