የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በቀጣይ ቀናት ሥልጣን እንደሚለቁ ተጠቆመ

ጀስቲን ትሩዶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጀስቲን ትሩዶ

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስር ጀስቲን ትሩዶ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሥልጣን መልቀቃቸውን እንደሚያሳውቁ ተገለጸ።

በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ መሠረት ትሩዶ ከገዢው ሊበራል ፓርቲ ኃላፊነታቸው የሚለቁ ይሆናል። በዚህም ከዘጠኝ ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸው ይለቃሉ ማለት ነው።

ባለፈው ወር የፋይናንስ ሚኒስትራቸው የፖሊሲ አለመስማማትን ምክንያት በማድረግ ከሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሯ የለቀቁት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ ምርቶች ላይ ሊጥሉ ያሰቡትን ታሪፍ በተመለከተ ከትሩዶ አስተዳደር ምላሽ ጋር ባለመስማማታቸው ነበር።

የቀድሞዋ የፋይናንስ ሚኒስትር ክርስቲና ፍሪላንድ፣ ትሩዶ በምጣኔ ሃብት አማካሪነት እንደማይፈልጓቸው ገልጸውላቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን ገልጸዋል።

ትሩዶ በሕዝብ ያላቸው ድጋፍ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን ፓርቲያቸው በጠቅላላ ምርጫ ሊሸነፍም ይችላል።

ዘ ግሎብ ኤንድ ሜል እንደዘገበው፣ ትሩዶ ሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት ከፓርቲው ጠቅላላ ውይይት ቀድመው ነው። ይህም በሕዝብ ተወካዮች ተገፍተው ከመውጣት ራሳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ በመምረጣቸው ነው ተብሏል።

ትሩዶ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሚመረጥ ስለመቆየታቸው ወይም ሳይመረጥ ስለመልቀቃቸው በግልጽ አልታወቀም።

የሚተካቸው መሪ ፓርቲው ከሚገጥመው የጠቅላላ ምርጫ ፈተና ማውጣት የሚችልና ከአሜሪካ ጋር ለሚደረግ የንግድ ጦርነት ዝግጁ መሆን አለበት።

ምርጫው ከጥቅምት ቀድሞ መካሄድ ይኖርበታል።

የትሩዶ መልቀቅ በካናዳ ፖለቲካ አንድ ምዕራፍ የመገባደድ ያህል ነው።

እአአ በ2015 ሳይጠበቁ ፓርቲያቸውን ከሦስተኛ ደረጃ አንስተው አሸናፊ አድርገዋል።

ያኔ 43 ዓመታቸው የነበረ ሲሆን ለስደተኞች ክፍት የሆነ አሠራርና የአየር ንብረት ለውጥን መታገልን ጨምሮ አዲስ የፓለቲካ አካሄድ ለመተግበር ቃል ገብተው ነበር።

የኑሮ ውድነትና አመራራቸው ላይ የተነሱ ጥያቄዎች በሕዝብ ያላቸውን ተቀባይነት ቀንሰውታል።

የኩዌቤክ፣ ኦንታሪዮና አትላንቲክ ግዛት የሊበራል ፓርቲ እንደራሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲወርዱ ሲጠይቁ ነበር።

ሁለት ሦስተኛ መራጮችም ትሩዶን መደገፍ አቁመዋል።

26% ድምጽ ሰጪዎች ትሩዶን እንደደገፉና ይህም ከወግ አጥባቂው መሪ ፒሬ ፒቬሬ 19 ነጥብ ከፍ እንደሚያደርጋቸው ኢፕሶስ ሰርቬይ የሠራው ጥናት ይጠቁማል።

ወግ አጥባቂው መሪ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋምና ግብር ለመቀነስ ባደረጉት ቅስቀሳ በፓርቲያቸው ተቀባይነት አግኝተዋል።

በካናዳ ታሪክ ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ብቻ ናቸው አራት ተከታታይ ዓመት ያገለገሉት።

ትራምፕ ካናዳ በግዛቷ ድንበር የስደተኞች እንቅስቃሴን የማትቆጣጠር ከሆነ የካናዳ ምርቶች ላይ የ25% ቀረጥ ለመጣል መዛታቸውን ተከትሎ ቀጣዩ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል።