ፖለቲከኛው ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
በ1922 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መስራች ናቸው።
በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ዋና አላማዉ ኦሮሞ እንደ ህዝብ ያጣቸዉንና ሊያገኛቸው ይገባል ብለን የምናስባቸውን መብቶች ለማስገኘት የተመሰረተ ፓርቲ ነው። በወቅቱ አብዛኛዉ ኦሮሞ በሩን ዘግቶ ነበር የሚቀመጠዉ።ስለዚህ እኛም 'ኦሮሞ አለ' ለማለት ነዉ" ብለው ነበር።
ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ድረመጂ ወረዳ የተወለዱት አቶ ቡልቻ የቤተሰባቸው አራተኛ እና ብቸኛ ወንድ ናቸው።
አቶ ቡልቻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊንቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኩየራ አድቬንቲስት ተከታትለዋል።የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያኔው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል።
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የመንግስት ስራን የጀመሩት በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን ነበር።
አሜሪካ ሀገር በሚገኝ ሴርኪኡዝ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተማሩት አቶ ቡልቻ ለአስር ዓመታት ያህል ምክትል ሚኒስትር ሆነው ካገለገሉ በኋላ በ1966 አብዮቱ ሲፈነዳ ተመልሰው ወደ ውጭ አገር ሂደዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የሰሩት አቶ ቡልቻ ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የፓርላማ አባል ነበሩ። በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ "የኢትዮጵያን ፓርላማን ለማየት እንጅ የእዉነት ነው ብየ አይደለም የገባሁት" ብለዋል።
አቶ ቡልቻ ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪ ከቀዳሚ የግል ባንኮች አንዱ የሆነውን አዋሽ ባንክ አቋቁመዋል። አቶ ቡልቻ የባንኩ ዓላማ ለኦሮሞ አርሶ አደሮች ብድር ማመቻቻት እንደሆነ ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአቶ ቡልቻን ማለፍ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "[አቶ ቡልቻ] በሚችሉት ሁሌ ሀገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑትን የትምና መቼም የሚናገሩ ነበሩ" ብለዋል።












