ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን በየመን የታቀደ ምሥጢራዊ ጥቃትን ጋዜጠኛ ባለበት የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድን በማጋራታቸው ቁጣ ተቀሰቀሰ

የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ዋልዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ዋልዝ

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋዜጠኛ ባለበት የሲግናል ቡድን ውስጥ በየመን ላይ ለማድረስ የታቀደ ጥቃትን በተመለከተ መረጃ በማጋራታቸው ከፍተኛ ቁጣ ተነስቷል።

ይህ የሲግናል ቡድን ብሔራዊ ምሥጢርን ባለሥልጣናት የሚለዋወጡበት ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ቡድኑን መቀላቀሉን ዋይት ሀውስ አረጋግጧል።

በአትላንቲክ መጽሔት የሚሠራው ጀፍሪ ጎልድበርግ እንዳለው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የመከላከያ ጸሐፊ ፒት ሀግስት የሚገኙበት ቡድን ውስጥ ነው የተቀላቀለው።

አሜሪካ በሁቲ አማጺያን ላይ ለማድረስ ያቀደችውን ምሥጢራዊ ጥቃት ጋዜጠኛው መመልከቱን ተናግሯል።

ምን ዓይነት መሣሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልና የትኛው ዒላማ ላይ መቼ ጥቃቱ እንደሚፈጸም መረጃውን ጋዜጠኛው ያየው ከጥቃቱ ሁለት ሰዓት ቀድሞ ነበር።

ዲሞክራቶች የትራምፕን አስተዳደር ሲተቹ ሪፐብሊካኖችም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው ወደ ሲግናል ቡድኑ እንዲቀላቀል የተደረገው በድንገት እንደሆነ ታውቋል። የዋይት ሀውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ዋልዝ ወደ ቡድኑ አካቶት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

"ሁቲዎችን የሚደግፍ ሰው ወደ ሲግናል ቡድኑ እንኳንም አላካተቱ። የአሜሪካውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ ነበር እያጋሩ የነበረው" ብሏል ጋዜጠኛው።

ዶናልድ ትራምፕ አትላንቲክ ላይ ስለወጣው ዘገባ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮላይን ሌቪት "በሁቲዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ስኬታማ ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በብሔራዊ ደኅንነት ቡድናቸው ይተማመናሉ" ብላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመከላከያ ሚኒስትር ጸሐፊም ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው በሲግናል ቡድኑ መቀላቀሉን በተመለከተ ሲጠየቁ "አሳሳችና ዋጋ ቢስ" ጋዜጠኛ ነው ሲሉ መልሰዋል።

ሪፐብሊካኑ አፈ ጉባዔ ማይክ ጆንሰን "ባለሥልጣኖች በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ" መሆናቸውን በመጥቀስ የጋዜጠኛው በሲግናል ቡድኑ መግባቱ ግን ስህተት ነው ብለዋል።

ዴሞክራቶች ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲከፈት ጠይቀዋል። የብሔራዊ ደኅንነት ቅሌት ነው ሲሉም ተችተዋል።

ዴሞክራቱ ቻክ ሹመር "ለረዥም ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር አልሰማሁም። የወታደራዊ ደኅንነት ክፍተት ነው" ብለዋል።

ጋዜጠኛው ቡድኑ ውስጥ እንዲገባ ስለመደረጉ በአትላንቲክ ላይ ዘገባ ጽፏል።

ቡድኑ ምናልባትም ሐሰተኛ ሊሆን እንደሚችል አስቦ ነበር። ሆኖም ግን በየመን ስለታቀደ ጥቃት በቡድኑ መረጃ ሲለቀቅ በጣም ነበር የተደነቀው።

የሁቲ ባለሥልጣን በኤክስ ገጻቸው እንዳሉት፣ በአሜሪካ የአየር ጥቃት 53 ሰዎች ተገድለዋል።

ሲግናል ደኅንነቱ አስተማማኝ የሆነ መተግበሪያ ስለሆነ በጋዜጠኞችና ባለሥልጣኖች ይመረጣል።

ጋዜጠኛው እንዳለው፣ ስለ ጥቃቱ ባለሥልጣኖቹ መልዕክት በሚለዋወጡበት ወቅት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከፕሬዝዳንቱ የሚጻረር አስተያየት ሰጥተዋል።

ጄዲ ቫንስ "ፕሬዝዳንቱ አውሮፓ ላይ ከሚያስተላልፈው መልዕክት ጋር ጥቃቱ የሚጋጭ መሆኑ የገባው አልመሰለኝም" ብለው መጻፋቸውን ጋዜጠኛው በዘገባው አስነብቧል።

የምክትል ፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ ዊልያም ማርቲን ግን ፕሬዝዳንቱና ምክትል ፕሬዝዳንቱ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሲግናል ቡድኑ ውስጥ የነበሩት ባለሥልጣናት የአሜሪካን መርከቦች ለመጠበቅ የአውሮፓ አገራት ገንዘብ እንዲመድቡ ስለመጠየቅም ተወያይተዋል።

ጄዲ ቫንስ በቡድኑ በጻፉት መልዕክት ላይ አውሮፓውያን አሜሪካ በየመን ከምታደርሰው ጥቃት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

"መላልሶ አውሮፓን መታደግ ያታክታል። በነጻ እየተጠቀሙብን መሆኑ በጣም ያናድዳል" ብለው እንደጻፉም ጋዜጠኛው በዘገባው አስነብቧል።