በሱዳን በደረሰ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 1,000 ሰዎች መሞታቸውን አማፂ ቡድኑ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራብ ሱዳን የማራ ተራራዎች አካባቢ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 1,000 ሰዎች መሞታቸውን የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ/አማፂ ቡድን አስታወቀ።
ለቀናት ሲጥል በነበረው ከባድ ዝናብ የተነሳ እሁድ ዕለት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ታራሲን የምትባለውን መንደር "ያወደመ" ሲሆን፣ ከአደጋው አንድ ሰው ብቻ በሕይወት መትረፉን ቡድኑ በመግለጫው ላይ ገልጿል።
የተመድ ባለሥልጣናት በማራ ተራራማ አካባቢ ቢያንስ 370 ሰዎች በመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተመድ በሱዳን የሰብዓዊ ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት አንቶኒ ጀራልድ የአደጋውን መጠን አሊያም የሟቾች ቁጥር ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ከሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቋል።
አንቶኒ ጀራልድ "ወደ አካባቢው እርዳታ በአፋጣኝ ማቅረብ ከባድ ነው" ብለዋል።
"ሂሊኮፕተሮች የሉንም። ምቹ ባልሆኑ መንገዶች ሁሉም ነገር በተሽከርካሪ መጓጓዝ አለበት። ጊዜ ይወስዳል፤ እናም ዝናባማ ወቅት ነው። ሸለቆውን ለመሻገር አንዳንዴ ሰዓታትን ምናልባትም አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን መጠበቅ አለብን። ግብዓቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ለማምጣት ከበድ ነው" ብለዋል።
የዳርፉር ጦር አስተዳደር ገዥ የሆኑት ሚኒ ሚናዊ የመሬት ናዳውን "የሰብዓዊነት አደጋ" ያሉት ሲሆን የረድኤት ድርጅቶች በአፋጣኝ እርዳታ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል በተካሄደው ጦርነት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ የሰሜን ዳርፉር ግዛት በርካታ ነዋሪዎች በማራ ተራሮች አካባቢ ተጠልለው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 2023 በሱዳን ጦር እና በአርኤስኤፍ መካከል በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት አገሪቱን ከፍተኛ ረሃብ ያጋጠማት ሲሆን፣ በምዕራብ ዳርፉር ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙ ተዘግቧል።
በእርስ በርስ ጦርነት ስለ ሞቱት ሰዎች የሚቀርበው ቁጥር በጣም የተለያየ ቢሆንም ባለፈው ዓመት አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን እአአ በ2023 ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 150,000 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል፤ 12 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል ብለዋል።
የመሬት መደርመስ የተከሰተበትን አካባቢ የሚቆጣጠሩት የሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄ/ሠራዊት አንጃዎች ከሱዳን ጦር ጋር በማበር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እየተፋለሙ መሆኑን ይናገራሉ።
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ከ4.5 ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት ወደ ጎረቤት አገራት ተፈናቅለዋል።















