ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ ሊጓዙ የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን 27 ሺህ ዶላር ተወረሰባቸው
የአሜሪካ የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ወደ አዲስ አበባ ሊጓዙ ከነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቤተሰብ አባላት 27 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መውረሱን አስታወቀ።
የአገሪቱ ጉምሩክና ድንበር ጥበቃ ተቋም እንዳስታወቀው እሁድ ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. ከቤተሰብ አባላቱ 27 ሺህ 330 ዶላር የወረሰው የቤተሰብ አባላቱ የያዙትን የገንዘብ መጠን ይፋ ባለማድረጋቸው ነው ብሏል።
የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ እንደገለጸው፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ በረራ ለማድረግ አምስቱ የቤተሰብ አባላት ዋሽንግተን ደለስ ዓለም አቀፍ አውሮእፓለን ማረፊያ ተገኝተው ነበር።
የቤተሰብ አባላቱ አውሮፕላን መሳፈሪያ በር ላይ እንደደረሱ ምን ያክል ገንዘብ እንደያዙ በጉምሩክ እና ድንበረ ጥበቃ መኮንኖች እንዲያሳውቁ ተጠይቀው ነበር።
ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና የአሜሪካ ዜግነት ያለው አባት 8 ሺህ ዶላር ገደማ እንደያዙ በቃል ምላሽ ሰጥቷል።
በመቀጠል የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ ባለሥልጣናት ተጓዞቹ በጉዞ ወቅት የያዙት ገንዘብ በተመለከተ ሪፖርት ስለማድረግ የአገሪቱን ሕግ ለተጓዦች አስታውሰዋል።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ተጓዦች ወደ አገር ውስጥ ይዘው በሚገቡትም ሆነ በሚወጡት የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ የለም።
ይሁን እንጂ አንድ ተጓዥ ከ10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የሌላ አገር ገንዘብ በላይ ከያዘ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ቅጽ ላይ አሳውቆ ለአሜሪካ ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኛ ማሳወቅ ይኖርበታል።
የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ 8 ሺህ ዶላር ገደማ ብቻ መያዙን የተናገረው አባት፤ የተጠየቀውን ቅጽ እየሞላ ሳለ፤ በእድሜ ትልቁ የሆነው ልጅ ሌላ 8 ሺህ ዶላር መያዙን ለባለሥልጣናቱ ተናግሯል።
በመቀጠል የጉምሩክ እና ድንበር ጥበቃ መኮንኖቹ የቤተሰብ አባላቱ ሻንጣዎች ላይ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ያገኙትን 27 ሺህ 330 የአሜሪካ ዶላር ወርሰዋል።
“ይህን በተደጋጋሚ ተናግረናል። ተጓዦች የፈለጉትን ያክል ገንዘብ ከአሜሪካ ይዘው መውጣት እና መግባት ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ የአሜሪካ ፌደራል ሕግ ተጓዦች ከ10ሺህ ዶላር በላይ ከያዙ ማሳወቅ እንዳለባቸው ያስገድዳል። ይህ በጣም ቀላል ነው” ሲሉ የአካባቢው የጉምሩክ እና ድንበር ባለሥልጣን ዳንኤል ኤስኮቤዶ ተናግረዋል።
የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ባለሙያዎች ለቤተሰብ አባላቱ 830 ዶላር ከመለሱ በኋላ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ አሰናብቷቸዋል።
ይሁን እንጂ በረራው አምልጧቸው የነበሩት የቤተሰብ አባላት፤ ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቲኬት ተቆርጦ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጓል።
የጉምሩክ እና የድንበር ጥበቃ ገንዘብ የተወረሰባቸው ሰዎች በወንጀል ስላልተከሰሱ የማናቸውንም ስም ይፋ እንደማያደርግ ጨምሮ ገልጿል።