አፍሪካዊው የቴክኖሎጂ ተቋም የወር አበባ ፈቃድ መስጠት ጀመረ

ንጽህና መጠበቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የናይጄሪያው የቴክኖሎጂ ተቋም ክላሻ የወር አበባ ፈቃድ መስጠት ጀመረ።

የወር አበባ ፈቃድ በመስጠት በናይጄሪያ ግንባር ቀደሙ የቴክኖሎጂ ተቋም እንደሆነ ተገልጿል።

ተቋሙ እንዳለው በአዲሱ አሠራሩ መሠረት እስከ አምስት ቀን ድረስ ፈቃድ የሚሰጥ ሲሆን፣ አሠራሩ ሲተገበር ውጤታማነቱ እየተገመገመ የቀን ቁጥሩ ላይ ለውጥ ሊኖር ይችላል።

የተቋሙ ዋና ኃላፊ ጀስ አኑና “በእለት ከእለት የሥራ ሂደታችን ለሴቶች ተፈጥሯዊ ፍላጎቶች ቦታ መስጠት ይገባናል። ጉዳዩን አደባብሰን ከመተው ይልቅ የመተማመን እና ቅቡልነት ባህል ማዳበር እንፈልጋለን” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ከክላሻ ሠራተኞች 60% ሴቶች ናቸው።

የተቋሙ ውሳኔ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ድጋፍ ቢያገኝም፣ አተገባበሩ ላይ ጥያቄ ያነሱም አሉ።

ክላሻ እአአ በ2018 የተመሠረተ የበይነ መረብ ግዢ ተቋም ሲሆን፣ በስድስት የአፍሪካ አገራት ቅርንጫፍ አለው። በሌጎስ እና ሳን ፍራንሲስኮ ቢሮ አላቸው።

ከአፍሪካ የወር አበባ ፈቃድ የምትሰጠው ብቸኛ አገር ዛምቢያ ናት። በወር አንድ ቀን እረፍት ይሰጣል።

ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያ እና ደቡብ ኮርያ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የፈቃድ ቀናት ይሰጥባቸዋል።

እአአ በ2019 የተሠራ ጥናት እንደሚያመለክተው የወር አበባ የሚያስከትለው ሕመም አንዲት ሴት በዓመት ውስጥ ዘጠኝ የሥራ ቀናት እንድታጣ ያደርጋል።