የቢትኮይን ዋጋ 100 ሺህ ዶላርን ተሻግሯል - ለመሆኑ ታሪካዊ የሚባሉት 7 አጋጣሚዎቹ የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቢትኮይን ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ተሻግሮ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል።
ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለክሪፕቶ ተስማሚ ፖሊሲዎችን እንደሚፈጥሩ መግለጻቸው የዓለማችን ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ ምንዛሪ ዋጋ ከቀን ቀን እየጨመረ ነው።
ትራምፕ የዎል ስትሪት ተቆጣጣሪነትን እንዲመሩ የቀድሞ የሴኩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (ኤስኢሲ) ኮሚሽነር ፖል አትኪንስን እሾማለሁ ካሉ ከሰዓታት በኋላ ዋጋው ተመንድጓል።
አትኪንስ አሁን ካለው የኤስኢሲ ኃላፊ ከሆኑት ጋሪ ገንስለር አንጻር የክሪፕቶከርነሲ ደጋፊ ተደርጎ ይወሰዳሉ።
ዋጋው 100 ሺህ ዶላር ማለፉ በዓለም ዙሪያ ባሉ የክሪፕቶፕ ተጠቃሚዎች ዘንድ ደስታን ፈጥሯል።
የቢትኮይን ዋጋ በጣም መዋዠቅ ሁልጊዜም ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። ዋጋው ከፍ ሲል ደጋፊዎቹ በደስታ ጮቤ ረግጠው ይናገራሉ። ዋጋው ካሽቆለቆለም ምናባዊውን ገንዘብ ለመከላከል የሚቀድማቸው የለም።
የአሁኑ ዋጋው ግን በተለየ በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቷል። ለሳምንታት ዋጋው መቼ 100 ሺህ ይደርሳል በሚል ሃሳባቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሽከረከሩ ቆይዋል።
ዋጋው ወደ 100 ሺህ ዶላር ሲጠጋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾች በበይነ መረብ ግብዣዎችን ተከታትለዋል።
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ የምናባዊው ኢንደስትሪ መለኪያ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው። አሁን የቢትኮይን ጠቅላላ ዋጋ 3.3 ትሪሊየን ዶላር ነው ተብሎ ይገመታል ሲል ኮይን ማርኬት ካፕ የተባለው የትንታኔ ድርጅት ገልጿል።
ባለፈው ወር ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸው ለዋጋው መጨመር ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተመራጩ ፕሬዝዳንት አሜሪካንን “የክሪፕቶ ዋና ከተማ” ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ትራምፕ እአአ በ2021 ቢትኮይንን “ማጭበርበሪያ” ብለው ከገለጹበት ክስ ተገልብጠው ነው አሁን ድጋፋቸውን የሰጡት።
አስገራሚው ነገር ደግሞ የቢትኮይን ዋጋ ከፍ ያለበት መንገድ ነው። አሁን ያለው 100 ሺህ ዶላር ዋጋ በአሜሪካ የምርጫ ቀን ከነበረው የ40 በመቶ ጭማሪ ያሳየበት ነው። ከዓመት በፊት ከነበረበት ዋጋው ደግሞ በእጥፍ ይበልጣል።
የቢትኮይን ዋጋ ከደረሰበት በላይ ግን በርካታ ጉዳዮች አሉ።
ከእንቆቅልሽ ፈጣሪው ጀምሮ የክሪፕቶ ንጉሥ እየተባለ የሚጠራውን እስከማዋረድ ድረስ ብዙ እሽክርክሪቶች ውስጥ ያለፈ ታሪክ አለው።
ቢቢሲም በቢትኮይን ታሪክ ወሳኝ የሚባሉትን ሰባት ጉዳዮች እንደሚከተለው ዳሷል።
1. ምሥጢራዊ የቢትኮይን ፈጣሪ
ትልቅ ስም ቢኖረውም በትክክል ቢትኮይንን ማን እንደፈጠረ ማንም በእርግጠኝነት አያውቅም። ሃሳቡ እአአ በ2008 ራሳቸውን ሳቶሺ ናካሞቶ ብለው በሚጠሩ ሰው አማካይነት በበይነመረብ መድረኮች ላይ ተለጠፈ።
ሰዎች በይነመረብ ላይ ምናባዊ ሳንቲሞችን እንዲልኩ ለማድረግ የአቻ ለአቻ ዲጂታል ገንዘብ አሠራር እንዴት እንደሚሠራ አስረድተዋል። ይህም ልክ ኢሜይል እንደመላላክ ያህል ነው።
ሳቶሺ በዓለም ዙሪያ ልዩ ሶፍትዌሮችን እና ጠንካራ ኮምፒተሮችን የሚጠቀሙ የበጎ ፈቃደኞችን ግዙፍ ኔትወርክ በመጠቀም ግብይቶችን የሚያሳልጥ እና አዳዲስ ሳንቲሞችን የሚፈጥር ውስብስብ የኮምፒውተር ሥርዓትን ፈጠሩ።
እሳቸውም ሆኑ እነሱ ማንነታቸውን ፈጽመው አልገለጡም።

የፎቶው ባለመብት, Reteurs
እአአ በ2014 ጃፓናዊው አሜሪካዊ ዶሪያን ናካሞቶ የማይታወቀው የቢትኮይን ፈጣሪ ነው ብለው ያሰቡ ጋዜጠኞች ተከታትለውት ነበር። በኋላም ይህ ሆነው በተሳሳተ የመረጃ ትርጓሜ ምክንያት የተከሰተ የውሸት ጥቆማ እንደሆነ ተረጋጠ።
አውስትራሊያዊው የኮምፒውተር ሳይንቲስት ክሬግ ራይት ከቢትኮይን ጀርባ ያለው ሰው እሱ መሆኑ እአአ በ2016 እሱ ተናገረ። ከዓመታት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ ግን ሳቶሺ አለመሆኑን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ደመደመ።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፒተር ቶድ የተባለ አንድ ካናዳዊ የቢትኮይን ኤክስፐርት ሳቶሺ ነው መባሉን አጥብቆ አስተባበለ። በዚህ ወር ደግሞ ብሪታኒያዊው ስቴፈን ሞላህ እሱ የቢትኮእን ፈጣሪ መሆኑን ለንደን ውስጥ ቢናገረም ማንም አላመነውም።
2. ከፒዛ ጋር ታሪክ መሥራት
ቢትኮይን አሁን የሁለት ትሪሊዮን ዶላር የክሪፕቶፕ ኢንደስትሪን እያንቀሳቀሰ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለበት ግብይት ግን የፒዛ ግዢ ነው።
እአአ ግንቦት 22 ቀን 2010 ላዝሎ ሀንዬዝ የተባለ ግለሰብ ሁለት ፒዛዎች ለመግዛት 41 ዶላር ዋጋ ያለው ቢትኮይን እንደሚሰጥ በክሪፕቶ መድረክ ላይ አሰፈረ።
የ19 ዓመቱ ተማሪ ግዴታ ነበረበት እና ቀኑ ለመገበያያ ገንዘቡ አድናቂዎች የቢትኮይን ፒዛ (#BitcoinPizza) ቀን ተብሎ በታሪክ ሰፈረ።
በክሪፕቶ ማኅበረሰብ ውስጥ ላሉ ሰዎች የማስታወሻ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የቢትኮይንን ኃይል አሳይቷል። እቃዎችን በበይነ መረብ ላይ በትክክልም መግዛት እንደሚያስችል አረጋገጠ።
ወንጀለኞችም ይህንን ታሪክ እየተመለከቱ እንደነበር እሙን ነው። ምክንያቱም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው በድብቅ የሚደረግ የዕጽ እና የሕገወጥ ንግድ ግብይት ተጀመረ።
ላዝሎ ፒዛ ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ በጣም ይመስላል። እነዚያን ሳንቲሞች እስካሁን ቢይዝ ኖሮ አሁን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ይኖራቸው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
3. ሕጋዊ ገንዘብ መሆን
በመስከረም 2021 የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡከሌ ቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያ ገንዘብ መሆን አደረጉ።
ፀጉር አስተካካዮች፣ ሱፐርማርኬቶች እና ሌሎች ሱቆች ከዋናው ገንዘባቸው ከአሜሪካን ዶላር ጋር ቢትኮይንን እንዲቀበሉ በሕግ ተገደዱ።
ብዙ የቢትኮይን አድናቂዎች እና ጋዜጠኞች አካባቢውን በመጎብኘታቸው ለአጭር ጊዜም ቢሆን የአገሪቱን ቱሪዝምን አሳድጓል።
እርምጃው በአገራቸው ያለውን ኢንቨስትመንት እንደሚያሳድግ እና የዜጎች የገንዘብ ልውውጥ ወጪን እንደሚቀንስ ፕሬዚደንት ቡከሌ ተስፋ ቢያደርጉም፣ እንደጠበቁት አልሆነም።
አሁንም ሎ ተስፋ እንደሰነቁ ቢሆንም ግን የአሜሪካ ዶላር አሁንም በአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ንጉሥ ሆኖ ቀጥሏል።
ፕሬዝደንት ቡኬሌ ሰዎች ቢትኮይንን እንዲቀበሉ ለማድረግ ከፍተኛ መጠን ያለው የሕዝብ ገንዘብ ከማውጣታቸውም በላይ እሳቸውም በአወዛጋቢ ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ሺህ በላይ ቢትኮይን ገዝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ የጥሬ ገንዘብ ላለባት አገራቸው ትርፍ ለማስግኘት በማሰብ ቢትኮይንን በተለያየ ዋጋ በመግዛት ቢያንስ 120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገዋል።
ከታኅሣሥ 2023 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋጋው ሲጨምር ሁሉም ነገር መልካም መስሏል።
በኔዘርላንድ የሶፍትዌር መሐንዲሱ ኤልያስ ዘሩክ የተገነባው ድረ-ገጽ የአገሪቱን የቢትኮይን ይዞታዎች እየተከታተለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሳንቲሞቹ ዋጋ 98 በመቶ ጨምሯል።

4. የካዛኪስታን ክሪፕቶ ማደግ እና ውጤቱ
ካዛኪስታን እአአ በ2021 የቢትኮይን ማይኒንግ ማዕከል ሆነች። ቢትኮይን ማይኒንግ ውስብስብ ስሌቶችን በመጠቀም የክሪፕቶ ግብይቶችን የሚረጋገጥበት መንገድ ነው።
አሁን ላይ ይህን ለመሥራት ቀኑን እና ሌሊቱን ሙሉ በሚሠሩ አዳዲስ ዘመናዊ ኮምፒውተሮች የተሞሉ መጋዘኖችን ይጠይቃል። በዚህ ዘርፍ ለሚሳተፉ ኩባንያዎች አዲስ ቢትኮይን በሽልማት መልክ ይሰጣል።
የኮምፒውተር መጋዘኖች ብዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠይቃሉ። ባላት ከፍተኛ ከድጋይ ከሰል በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ይግባው እና በርካታ ኩባንያዎች ኤሌክትሪክ በብዛት ወደሚገኝባት ወደ ካዛክስታን ተዛውረዋል።
ኢንቨስትመንትን በማምጣታቸው የአገሪቱ መንግሥት መጀመሪያ ላይ እጁን ዘርግቶ በደስታ ተቀብሏቸዋል።
በጣም ብዙ ኩባንያዎች ገብተው በኤሌክትሪክ አውታር ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር የአገሪቱን የመብራት ሥርጭት አደጋ ላይ እስከመጣል ደረሱ።
መንግሥት ዕድገቱን ለመግታት ገደቦችን ሲጥል እና ግብር ሲጨምር የካዛኪስታን የቢትኮይን ማይኒንግ ኢንዱስትሪ በአንድ ዓመት ውስጥ ከዕድገት ወደ ክስረት ተሸጋገረ።
በዓለም ዙሪያ የቢትኮይን ኔትዎርክ አንዲት ትንሽ አገር ከምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እንደሚስተካከል ይገመታል። ይህ አካሄድም የአካባቢ ተጽእኖ ስጋትን ፈጥሯል።

የፎቶው ባለመብት, James Howells
5. በቆሻሻ መጣያ ውስጥ የሚገኝ ቢትኮይን
ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የክሪፕቶ ዋሌት (ክሪፕቶ ዋሌት አንድን ክሪፕቶ ቁልፍ ሆኑ መረጃዎችን የሚይዝ ነው) እንዳልዎት ያስቡ። የይለፍ ቃልዎትን የያዘ ሃርድ ድራይቭ በድንገት ጣሉ።
የደቡብ ዌልስ ነዋሪው ጄምስ ሃውልስም ያጋጠመው ይህ ነው።
የክሪፕቶ ተፈጥሮ ሆኖ የይለፍ ቃልዎትን መልሶ ማግኘት ቀላል አይደለም። ባንኮች ካለመሳተፋቸውም በላይ ለደንበኞች ድጋፍ የሚሰጥበት መንገድ የለም።
እንደ አለመታደል ሆኖ በኒውፖርት የሚገኘው ምክር ቤት ኮምፒውተሩ በጣለበት የቆሻሻ መጣያ ገብቶ እንዲፈልግ አልፈቀደለትም። ከፈቀዱለት 25 በመቶ ቢትኮይኑን ለአካባቢው በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለመለገስ ሃሳብ ቢያቀርብም ይሁንታ አላገኘም።
“የመስመጥ ዓይነት ስሜት አለው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
6. አጭበርባሪው የክሪፕቶ ንጉሥ
እንደ ቀድሞው ቢሊየነር እና የክሪፕቶ ንጉሥ ሳም ባንክማን-ፍሪድ የከሰረ የለም። ባንክማን የግዙፉ ክሪፕቶ ተቋም ኤፍቲኤክስ መሥራች ሲሆን፣ የክሪፕቶ ንጉሥ የሚል ቅጽል ስም ከማግኘት ባለፈ በክሪቶ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ነበር።
ኤፍቲኤክስ ሰዎች መደበኛ የወረቀት ገንዘቦችን እንደቢትኮይን ካሉ ክሪፕቶዎች ጋር እንዲገበያዩ የሚያስችል የምሥጢራዊ የልውውጥ መድረክ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግለሰቡ 32 ቢሊዮን ዶላር እንዳለው ይገመት ነበር። በቀናት ውስጥ ሁሉም ነገር እስኪፈረካከስ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ይበር ነበር።
የባንክማን-ፍሪድ ኩባንያ የፋይናንስ ሁኔታ የተናወጠ እና የኤፍቲኤክስ ደንበኞችን ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር ለሌላኛውን ኩባንያውን አላሜዳ ሪሰርች ማዋሉን ጋዜጠኞች ደርሰውበታል።
እአአ በታኅሣሥ 2022 በባሃማስ በሚገኘው ቅንጡ አፓርታማው ውስጥ ሆኖ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት ጋዜጠኞችን አናግሯል። “ማጭበርበር የፈጸምኩ አይመስለኝም። ይህ እንዲሆን አልፈልግም ነበር። በእርግጥም እኔ ያሰብኩትን ያህል ተወዳዳሪ አልነበርኩም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ለአሜሪካ ተላልፎ ከተሰጠው በኋላ በማጭበርበር እና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ ተብሎ 25 ዓመት በእስር እንዲቀጣ ተወሰነበት።
7. የኢንቨስትመንት ባንክ መስፋፋት
በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩበትም ቢትኮይን የባለሀብቶችን እና የትላልቅ ኩባንያዎችን ትኩረት መሳቡን ቀጥሏል።
ጥር 2024 ላይ በዓለም ላይ ካሉት ታላላቅ የፋይናንስ ድርጅቶች አንዳንዶቹ ቢትኮይንን ስፖት ቢትኮይን ኢቲኤፍስ በማለት ወደ ይፋዊ የንብረት ዝርዝራቸው ውስጥ አስገብተዋል።
እነዚህ ልክ እንደ አክሲዮኖች እና ድርሻዎች ቢሆኑም ከቢትኮይን ዋጋ ጋር የተገናኙ ናቸው። ነገር ግን በግል ባለቤት መሆን አይቻለም።
ደንበኞች ወደ እነዚህ አዳዲስ ምርቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ሲያፈስሱ ቆይተዋል። ብላክሮክ፣ ፊደሊቲ እና ግሬይስኬልን ጨምሮ የተለያዩ ኩባንያዎች በሺህዎች የሚቆጠር ቢትኮይን ሲገዙ መቆየታቸው ዋጋውን ከፍ እንዲል ዋናውን ሚና ተጫውቷል።
ይህም ለክሪፕቶ ትልቅ ምዕራፍ ነው። አንዳንድ ደጋፊዎቹም በመጨረሻም ቢትኮይን ምሥጢራዊው ሳቶሺ እንዳሰበው በቁም ነገር እየተወሰደ ነው ብለው ማመን ጀምረዋል።















