ኢንተርኔትን በመጠቀም ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይቻላል? የቲክቶክ መካሪዎችስ ምን ያህል ታማኝ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማኅበራዊ ሚዲያው በተለይ ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ተጨማሪ ገቢ ማግኛ መንገዶችን በሚያስተዋውቁ ሰዎች የተሞሉ ናቸው። እውን በእነዚህ መንገዶች በመጠቀም ገቢን ማሳደግ ሕይወትን መለወጥ ይቻላል?
የ38 ዓመቱ ዴቭሺ ተጨማሪ ገቢ ስለሚገኝባቸው መንገዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው የኮቪድ ወረርሽኝ ገብቶ ዓለምን ባስጨነቀበት ወቅት ነው።
በጊዜው ሁሉም ቤቱ ነበር የሚውለው። ዴቭሺ የፌስቡክ እና ቲክቶክ ገፁ ገንዘብ ማግኛ መንገዶች በሚሉ ቪድዮዎች መሞላቱን አስተዋለ። አብዛኞቹ ቪድዮዎች ‘በትንሽ ድካም ብዙ ገንዘብ ያግኙ’ ሲሉ ነው የሚያስተዋውቁት።
ከክሪፕቶከረንሲ ጀምሮ ቁጭ ብሎ ቪድዮዎችን በማየት እስከሚገኝ ገቢ ድረስ በመላው ዓለም ሰዎች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት የሚጠቀሟቸው መላዎች ናቸው።
ዩናይትድ ኪንግደም የሚኖረው ዴቭሺ በትርፍ ጊዜው ትንሽም ቢሆን ገንዘብ ለማግኘት ደፋ ቀና ማለት ጀመረ።
በቀድመው ጊዜ በእንግሊዝኛው ‘ፓሲቭ ኢንካም’ አሊያም ተጨማሪ ገቢ የተባለው ሐሳብ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የሚተገብሩት ነበር። እነዚህ ሀብታሞች አፓርትማ ገዝተው ያከራያሉ፣ አክሲዮን ይሸምታሉ፣ ሌላም. . . ሌላም።
ዘንድሮ ተጨማሪ ገቢ የማግኘት መንገድ በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ መልኩን ቀይሯል። ታዳጊዎች እና ወጣቶች ኢንተርኔትን ተጠቅመው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ይሞክራሉ።
በተለይ ገንዘብ ማግኘት እና አዲስ የሕይወት ዘይቤን መለማመድ በሚጓጉት ወጣቶች የሚዘወተሩት ቲክቶክ እና ኢንስታግራም “ተኝተው” ተጨማሪ ገቢ ያግኙ በሚሉ ጥሪዎች ተጥለቅልቀዋል።
ባለፈው ዓመት የተለቀቀ አንድ በሚሊዮኖች የታየ የቲክቶክ ቪድዮ ቤትዎ ተቀምጠው አማዞን በተሰኘው የኢንተርኔት መገበያያ በኩል “ረብጣ ዶላር ያትሙ” ይላል።
አንዲት ተፅዕኖ ፈጣሪ ደግሞ ለተከታዮቿ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ዕቃ በመሸጥ “በወር ከ5 አስከ 10 ሺህ ዶላር መሥራት እንደሚችሉ ያውቃሉን?” ስትል ትጠይቃለች።
ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የምናያቸው የተጨማሪ ገቢ ማግኛ መንገዶች ቀላል ብቻ ሳይሆኑ ኪሳችን እንዲዳብር እና ራሳችንን እንድንችል ያደርገናል የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ የሚሉት ‘ጄኔሬሽን መኒ’ የተሰኘ ተቋም ያላቸው አሌክስ ኪንግ ናቸው።
መሰል ቪድዮዎች በመላው ዓለም እንዲሠራጩ እና በቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ በስፋት እንዲዛመቱ እያደረገ ያለው አንዱ ጉዳይ ኢኮኖሚው ነው።
የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ያናወዛቸው ወጣቶች ለበርካታ ሰዓታት ሠርተውም ቢሆን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ዝግጁ ይመስላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቲክቶክ መካሪዎች ታማኝ ናቸው?
የአሜሪካው የመረጃ ቢሮ እንደሚለው 20 በመቶ አሜሪካውያን ተጨማሪ ገቢ ማግኛ መንገዶችን ተጠቅመው በዓመት በአካማይ 4 ሺህ ዶላር ያስገባሉ።
ነገር ግን በርካቶች ደግሞ ተጨማሪ ገቢ ማግኛ መንገዶች ልክ ቲክቶክ ላይ እንደምናያቸው ቪድዮዎች ቀላል አይደሉም ሲሉ ያማራሉ።
ዴቭሺ ከመደበኛ ሥራው በተረፈው ጊዜ ተማሪዎች ያለፉ ፈተናዎችን የሚያገኙበት ድረ-ገፅ አቋቋመ። ነገር ግን ይህ ተጨማሪ ገቢ ያመጣልኛል ብሎ የጀመረው ሥራ እንዳሰበው ቀላል አልነበረም።
በወር እስከ 244 ዶላር ቢያገኝበትም በቀን ቢያንስ ሁለት ሰዓታትን ለዚህ ሥራ ማዋል አለበት።
ካናዳዊው ቶማስ ብሌክ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲል ከትምህርት በተጓዳኝ የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ መሯሯጥ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ይሄኔ ነው “በወር ጥቂት መቶ ዶላሮች” የሚያስገኝ ሐሳብ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተመለከተው።
ቢሆንም በወር ያገኝ የነበረው ገንዘብ ከ25 - 40 ዶላር የሚሆን ብቻ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጨማሪ ገንዘብ ማግኛ መንገዶችን የሚያስተዋውቁ ሰዎች በሁለት ይከፈላሉ። ግማሾቹ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን የሚያጋሩ ሲሆኑ፣ የተቀሩቱ ለራሳቸው ጠቀም ያለ ገቢ እያገኙ ተከታዮቻቸውን የሚያጭበረብሩ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Aminah Al-Noor
ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይቻላል?
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለጉግል እና ፌስቡክ በመሸጥ የሚጠቀሙ በርካቶች ናቸው። ሜታ እና ጉግልን የመሳሰሉ ግዙፍ ድርጅቶች ከማስታወቂያ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላሮች ነው የሚያፍሱት።
ለምሳሌ ከሰሞኑ ጂንስ ሱሪ መግዛት ፈልገው ኢንተርኔት ላይ ይህን ሲያስሱ ቆይተው በነጋታው የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገፅዎ በጂንስ ማስታወቂያ ቢጥለቀለው አይግረምዎ።
የአንድ አውሮፓዊ መረጃ በአማካይ በቀን 376 ጊዜ ለተለያዩ ድርጅቶች ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል ይላል አንድ ጥናት። ወደ አሜሪካ ስንሄድ ይህ ቁጥር በእጥፍ ከፍ ይላል።
‘ሰርፍ’ የተባለው የካናዳ ድርጅት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በጎበኙት ድረ-ገፅ ልክ ገንዘብ ይከፍላል። ድርጅቱ ይህን የሚያደርገው ከተጠቃሚዎች በፈቃዳቸው መረጃ በመውሰድ ሲሆን፣ ይህን መረጃ ለትላልቆቹ ድርጀቶች በመሸጥ ለተጠቃሚዎች ‘ኮሚሽን’ ይቆርጣል።
ሰርፍ እንደሚለው እንደ ኢሜይል እና የስልክ ቁጥር ያሉ መረጃዎችን አሳልፎ አይሰጥም፤ ስምዎትን አለመጠቀም ይችላሉ። ነገር ግን ዕድሜ፣ ፆታ እና አድራሻ ይጠይቃል።
ሰርፍ ለተጠቃሚዎቹ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጥ ይፋ ባያደርግም እስካለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ድረስ 1.2 ሚሊዮን ዶላር ማከፋፈሉን ይናገራል።
ሰርፍ የተባለውን ‘የጉግል ክሮም ኤክስቴንሽን’ ከሚጠቀሙ ሰዎች መካከል አንዷ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ አሚናህ አል-ኑር ናት።
ይህን ኤክስቴንሽን በመጠቀም የምታገኘውን ገንዘብ በኢንተርኔት ላይ ለምታደርገው ግብይት ነው የምታውለው።
መጠይቆችን [ሰርቬይ] መሙላት፣ ቪድዮዎችን ተመልክቶ ገንዘብ ማግኘት፣ ክሪፕቶከረንሲ፣ ቶክን እና ሌሎችም ተጨማሪ ገንዘብ ማግኛ መንገዶች ናቸው።
በዚህ ዘርፍ ገንዘብ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ልምድ ያላቸው እንደሚሉት አንድ አዲስ ተጨማሪ ገቢ ማግኛ ሲመጣ ቀድመው ተመዝግበው የሚሠሩ ሰዎች የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስጠነቅቁት ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን እና የባንክ ሒሳባቸውን ለማንም እንዳያጋሩ ነው።
ስለዚህም በበይነ መረብ ላይ ባሉ ድረ ገጾች እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቀላሉ በሚከወኑ ሥራዎች ገቢ ማግኘት እንደሚቻል የሚለቀቁ አማላይ መስታወቂያዎችን በጥንቃቄ መመለክት ያስፈልጋል።
ካልሆነ ግን ጊዜን ባልተጨበጠ ነገር ላይ ከማጥፋት ባሻገር ግላዊ መረጃን ለአጭበርባሪዎች አሳልፎ በመስጠት ተጨማሪ ማግኘቱ ቀርቶ ያለንንም ልናጣ እንችላለን።












