ኢትዮጵያ ‘በዳታ ማይኒንግ’ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የኃይል ሽያጭ በውጪ ምንዛሬ ማቅረብ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘በዳታ ማይኒንግ’ ዘርፍ ከተሰማሩ ሁለት የውጪ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
18 የ‘ዳታ ማይንኒግ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የኃይል አቅርቦት ስምምነት መፈራረማቸውን የተቋሙ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከነዚህ ኩባንያዎች 10 የሚሆኑት ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ግንባታ እያከናወኑ እንደሆኑ የጠቁሙት አቶ ሞገስ አራት ኩባንያዎች ደግሞ ኃይል መጠቀም መጀመራቸውን አንስተዋል።
ከአራቱ ኩባንያዎች አንዱ 10 ሜጋ ዋት የሚጠቀም፣ ሁለቱ 20 ሜጋ ዋት የሚጠቀሙ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ 100 ሜጋ ዋት በድምሩ 130 ሜጋ ዋት ኃይል እንደቀረበላቸው ጠቅሰዋል።
ኃላፊው ሌሎች 5 ኩባንያዎች ስራ ለመጀመር “በሂደት” ላይ እንደሆኑ ተናግረው ሶስት ድርጅቶች ደግሞ ፍቃድ ወስደው “ምንም አይነት ስራ ባለመጀራቸው በፍጥነት እንዲጀምሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል።
በአጠቃላይ ለ 25 የ‘ዳታ ማይንኒግ’ ኩባንያዎች ኤሌክትሪክ በውጪ ምንዛሬ የሚቀርብላቸው ሲሆን ኩባንያዎቹ ህጋዊ ስርዓትን አልፈው ወደ ተቋሙ እንደሚመጡ አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
ኩባንያዎቹ “አንደኛ በሀገሪቱ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችላቸውን ፍቃድ ያወጣሉ [በተጨማሪም] ይህንን ሥራ መስራት የሚችሉ እንደሆነ በኢንሳ ማረጋገጫ ይሰጣቸዋል። ከዚያ በኃላ እኛ ጋር የሚመጡት የኃይል ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ኤሌክትሪክ መሸጥ ስትጀምር የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍጆታን አይሻማም ወይ? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ሞገስ ሲመልሱ በሀገር ውስጥ ፍጆታ ላይ ተጸዕኖ የለውም ብለዋል።
“አሁን ባለን ሁኔታ፣ ከፍተኛው እየተጠቀምን ያለነው ወደ 3 ሺህ 500 ሜጋ ዋት አከባቢ ነው። የሀገር ውስጥም ኤክስፖር የተደረገውንም አሟልተን እንደ መጠባበቂያ የተያዘ ከ500 እና ከዚያ በላይ ኃይል አለን። ስለዚህ ይህንን ለመጠቀም የሚከለክለን ነገር የለም” ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ሞገስ ለኩባንያዎቹ ከብሔራዊ የኃይል ቋት እንጂ ከአንድ የተለየ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል እንደማይቀርብላቸው ተናግረዋል።
‘ዳታ ማይኒንግ’ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጥሬ መረጃዎች በማፈላለግ ወደ ቀላል፣ ጠቃሚ እና ለተግባር ወደሚመች የመረጃ አይነት የመቀየር ሂደት ነው።
የተቀየሩት መረጃዎች ደግሞ በተለያዩ የንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ግዙፍ የንግድ ተቋማት በሽያጭ ይቀርባል።
‘ዳታ ማይኒንግ’ ለአወዛጋቢው የዲጂታል ገንዘብ ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ አግልግሎትም ይውላሉ።
ታዲያ ይህንን ሥራ የሚያከናውኑ ማሽኖች ወይም ኮምፒውተሮች ውጤታማ እንዲሁም ከፍ ያለ መረጃዎችን ለማደራጀት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይልን ይጠይቃሉ።












