3.2 ቢሊዮን ዶላር አጭበርብራ የተሰወረችው ‘የክሪፕቶ ንግሥት’ በኤፍቢአይ እየተፈለገች ነው

ሩጃ ኢግናቶቫ

ሩጃ ኢግናቶቫ ወይም “የጠፋችው የክሪፕቶ ንግሥት” በአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ በጥብቅ ከሚፈለጉ 10 ሰዎች ውስጥ ተካታለች።

የቡልጋሪያ ዜግንት ያላት ግለሰቧ ‘ዋን ኮይን’ በሚሰኝ የክሪፕቶ ከረንሲ አይነት ማጭበርበ ውስጥ ተሳትፎ አላት የሚል ውንጀላ ይቀርብባታል።

ተጠርጣሪዋ ከተለያዩ ሰዎች 3.2 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ገንዘብ አጭበርብራ መሰወሯን የአሜሪካ ፌዴራል መርማሪዎች ይገልጻሉ። 

ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ የገባችበት ያልታወቀው ሩጃ ኢግናቶቫ የእስር ማዘዣ የወጣባት ሲሆን መርማሪዎች ክትትል እያደረጉባት ነው።

ግለሰቧ ‘ዋን ኮይን’ የተባለው እና እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የተጀመረው የዲጂታል ገንዘብ/ክሪፕቶከረንሲ ውስጥ ተሳትፎ እንዳላት የምትጠረጠር ሲሆን ገዢዎች ብዙ ሰዎችን ባመጡ ቁጥር ብዙ ኮሚሽን እንዲገኙ አደርጋለው የሚል ነው።

ሆኖም ኤፍቢአይ ‘ዋን ኮይን’ ረብ የለሽ እና እንደሌሎች የክሪፕቶክረንሲ ዓይነቶች አስተማማኝ የደኅንነት መጠበቂያ ኖሮት የማያውቅ ነው ብሎታል።

የፌዴራል ጠበቆች እንደሚያቀርቡት ክስ ከሆነ ‘ዋን ኮይን’ አጭበርባሪ ሲሆን፣ ስሙን ቀይሮ በክሪፕቶከረንሲ መልክ ብቅ ያለ ነው።

ተጠርጣሪዋ “ክሪፕቶ ከረንሲ ሲጀመር የነበሩ እና በስፋት የሚወሩ መላምቶችን በሚገባ በመጠቀም ለማጭበርበር የሚበጃትን ትክክለኛ ሰዓት መርጣለች” ሲሉ ዳሚያን ዊሊያምስ የተባሉ ዐቃቢ ሕግ ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለች የማትታወቀዋን ግለሰብ ኤፍቢአይ በብርቱ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ማካተቱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ተጠርጣሪዋን በማፈላለጉ ሂደት ዜጎች እንዲረዱት ያግዛል ተብሏል።

ታዲያ እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ስምንት ክሶች የቀረቡበታን ኢግናቶቫ ለሚጠቁም የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

ሴትየዋ በኤፍቢአይ በጥብቅ ከሚፈለጉ 10 ሰዎች ውስጥ የተካተተች ብቸኛ ሴት ናት። በዚህ ዝርዝር ውስጥ መካተቷ ደግሞ የመያዝ ዕድሏን ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።

የግለሰቧን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩት አንድ መርማሪ ተጠርጣሪዋ ከሕግ ለመሰወር 500 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቷን የገለጹ ሲሆን ይህም ፍለጋውን እጅግ አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

 ራሷን የመደበቅ እና ሐሰተኛ ማንነት የመጠቀም ከፍተኛ ብቃት እንዳላት የተነገሩት መርማሪው በህይወት ላትኖርም ትችላለች የሚል ግምት አላቸው።

“የጠፋችው የክሪፕቶ ንግሥት” ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 ከቡልጋሪያ ወደ ግሪክ ባቀናችበት ጊዜ ሲሆን ከዚያ ጊዜ በኋላ ግን ደብዛዋ ጠፍቷል።