በቤኒን የተሞከረው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, BTV
እሁድ ማለዳ የቤኒን ጦር ሠራዊት አባላት ሥልጣን መያዛቸውን ያስታወቁበት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉን እና ፕሬዝዳንቱ በደኅና ሁኔታ በፈረንሳይ ኤምባሲ ውስጥ አንደሚገኙ የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
የቤኒን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉን አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል በሌ/ኮሎኔል ፓስካል ቲግሪ የሚመራ የወታደሮች ቡድን በቴሌቪዥን ባስተላለፈው መልዕክት ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎንን ከሥልጣን አስወግዶ የአገሪቱን ሕገመንግሥት ማገዱን አስታውቆ ነበር።
በቤኒን የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባሠራጨው መረጃ በዋና ከተማዋ ኮቶኑ ውስጥ ባለው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ተኩስ እንደነበር አመልክቷል።
የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የዐይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን አና የተወሰኑ ለመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ታግተው እንደነበረ ገልጸዋል።
የቤኒን ፕሬዝዳንት አማካሪ ፕሬዝዳነቱ በደህና ሁኔታ ፈረንሳይ ኤምባሲ ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ዛሬ እሁድ ማለዳ ላይ ትንሽ ቁጥር ያላቸው የወታደሮች ቡድን የአገሪቱን መንግሥት እና ተቋማትን ለማናጋት የአመጽ ተግባር ፈጸሟል" ሲሉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው መክሸፉን የቤኒን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አላሳኔ ሴይዱ አስታውቀዋል።
"የቤኒን ጦር ኃይሎች አባላት እና አመራሮቹ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቃለ መሃላቸውን በማክበር፣ ለሪፐብሊኩ ታማኝ በመሆን በቁርጠኝነት ቆመዋል። የወሰዱት እርምጃ ሁኔታውን እንዲቆጣጠሩ በማስቻል የተቃጣውን [የመንግሥት ግልበጣ] ሙከራ ለማክሸፍ አስችሏል" ብለዋል ሚኒስትሩ።
"በመሆኑንም ሕዝቡ በተለመደው ሁኔታ ወደ ዕለት ተለት ተግባሩ እንዲመለስ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል" በማለት ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር መዋሉን አመልክተዋል።
በዋና ከተማዋ ኮቶኑ ሰማይ ላይ ሄሊኮፕተሮች ሲበሩ የነበረ ሲሆን፣ በርካታ የከተዋ መንገዶች ተዘግተው በጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ የወታደሮች እንቅስቃሴ ይታያል።
የፈረንሳይ እና የሩሲያ ኤምባሲዎች በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎቻቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ ከቤታቸው እንዳይወጡ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ደግሞ ዜጎቹ ከዋና ከተማዋ ኮቶኑ በተለይም የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ካለበት አካባቢ እንዲርቁ መክሯል።
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን የመሩት ወታደሮች ፐሬዝዳንቱ አገሪቱን እየመሩ ያሉበትን አካሄድ በመተቸት ለእርምጃቸው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከመፈንቅለ መንግሥት ሞካሪዎቹ ወታደሮች መካከል በቴሌቪዥን ላይ ቀረቦ እንዳነበበው "ሠራዊቱ ለቤኒን ሕዝብ ወንድማማችነት፣ ፍትሕ አና ሥራ የበላይ የሚሆኑበት እውነተኛ አዲስ ዘመን ለማምጣት በቁርጠኘነት ቃል ይገባል" ሲል መልዕክት አስተላልፎ ነበር።
አማጺዎቹ ወታደሮች ጠዋት ላይ መፈንቅለ መንግሥት ፈጽመው የአገሪቱን ሥልጣን መቆጣጠራቸውን ባሳወቁበት ጊዜ ሉተናንት-ኮሎኔል ቲግሪ ፓስካልን የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አድርገው መሰየማቸውን ገልጸው ነበር።
በተጨማሪም የሕገ መንግሥቱን ማገዳቸውን፣ የቤኒን የአየር ክልልን ከበረራ ውጪ ማድረጋቸውን እና የድንበር አካባቢዎች እንቅስቃሴዎችን ማገዳቸውን አስታውቀው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበረችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን በአፍሪካ የተረጋጋ ዴሞክራሲ ካለባቸው አገራት አንዷ ተደርጋ ትቆጠራለች።
ቤኒን በአህጉሪቱ ዋነኛ የጥጥ አምራች ከሆኑ አገራት አንዷ ብትሆንም ደሃ ከሚባሉት መካከል ናት።
የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባውቸ የ67 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ታሎን ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን አጠናቀው በመጪው ሚያዝያ ላይ አስተዳደራቸውን እንደሚያስረክቡ እየተጠበቀ ነው።
'የጥጥ ንጉሥ' በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ነጋዴው ፕሬዝዳንት በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የያዙት።
ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እና በምርጫ እንደማይወዳደሩም ገልጸዋል።
የቤኒን የከሸፈ የመፈንቅለ መንግሥት ዜና የተሰማው ከሳምንት በፊት በጊኒ ቢሳዎ ወታደሮች ሥልጣን መያዛቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።
መፈንቅለ መንግሥት የተፈጸመባቸው የጊኒ ቢሳዎ ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ ወደ አጎራቧች አገር ሴኔጋል ገብተዋል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ በምዕራብ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት ተበራክቷል። እስካሁን ድረስ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ፣ በማሊ እና በኒጀር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ተፈጽመዋል።
በዚህም ምክንያት የምዕራብ አፍሪካ የፀጥታ እና ደኅንነት ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ።















