የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች በማሊ ፈጸሟቸው ስለሚባሉት የጭካኔ ግድያዎች የዐይን ምስክርነት

የቆመ ሰው ጥላ

ማሳሰቢያ፡ይህ ዘገባ የማሰቃየት እና የአካላዊ ጥቃትን በዝርዝር የሚገልጽ በመሆኑ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ ይችላል።

አንድ የሱቅ ጠባቂ በማሊ ጂሃዲስቶችን የሚዋጉ የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ዐይኑ እያየ ሁለት ሰዎችን በጭካኔ እንደተገደሉ እንዲሁም ጣቶቹን ቆርጠው እንደሚገድሉት እንዳስፈራሩት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ይህ የሩሲያ ተዋጊዎች በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ጨካኝ የሆነ የፀረ ሽምቅ ዘመቻ ሲያካሂዱ የተጠቀሙባቸውን እና በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች በስፋት የተወገዙ ዘዴዎችን ከሚያሳዩ በቢቢሲ ከተሰበሰቡ በርካታ ተመሳሳይ ምስክርነቶች አንዱ ነው ።

በ2021 በማሊ አንድ ወታደራዊ አገዛዝ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ የፈረንሳይ ወታደሮችን አመፅ ማስቆም አልቻሉም በሚል ከከሰሳቸው በኋላ እንዲወጡ አስገደዳቸው። ወታደራዊ ጁንታው ፊቱን ወደ ሩሲያ አዞረ፣ በወቅቱ ከክሬምሊን ጋር ግንኙነት ያለውን የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን እርዳታ ጠየቀ።

ቫግነር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገሪቷን ለቅቆ የወጣ ሲሆን፣ ሥራዎቹ በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ስር በሚገኘው የአፍሪካ ኮርፕስ ተወስደዋል።

ባለፈው ወር የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ባወጣው ሪፖርት መሠረት አንዳንድ የቫግነር ቅጥረኛ ወታደሮች በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ እስኪዘጋ ድረስ በግብዣ ብቻ በሚገባበት የቴሌግራም ቡድን ላይ የፈጸሙትን ግፍ አጉልተው አሳይተዋል ብሏል።

ሪፖርቱ አክሎም "በአማፂያን እና በሲቪሎች ላይ የግድያ፣ የመድፈር፣ የማሰቃየት፣ የሰው ሥጋ የመብላት እና አስከሬን የማዋረድ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን አዘውትረው ያጋሩ ነበር" ብሏል።

በሰኔ ወር የአፍሪካ ሪፖርት ህትመት ከቫግነር ጋር የተገናኘውን የቴሌግራም ቻናል "ሰርጎ" እንደገባ እና 322 ቪዲዮዎችን እንዲሁም 647 የጭካኔ ፎቶግራፎችን አግኝቷል፣ ጭንቅላታቸውን እና የተወጉ ዐይኖቻቸውን ጨምሮ "በዘረኝነት የተለጠፉ" ጽሁፎችን እንዳገኘ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለደኅንነቱ ሲባል አህመድ ብለን የምንጠራው እና ቢቢሲ ያነጋገረው የሱቅ ጠባቂ ከማሊ ሸሽቶ አሁን በሞሪታኒያ ድንበር በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ይኖራል። ከአህመድ በተጨማሪ ለደኅንነታቸው ሲባል በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት የሁሉም ተጎጂዎች ስም ተቀይሯል።

አህመድ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ መከራው የጀመረው የቫግነር ተዋጊዎች በነሐሴ 2024 በናምፓላ ማዕከላዊ ከተማ ወደሚገኘው ትልቅ መደብር በመኪና ሲሄዱ ነው።

የቫግነር ተዋጊዎች የሱቁ መደበኛ ደንበኞች ቢሆኑም፣ አለቃውን በክልሉ ውስጥ በብዛት ከሚንቀሳቀሱ ጂሃዲስቶች ጋር ተባብሯል ብለው እንደወነጀሉት እና ሊያስሩት ፈልገው እንደነበር አህመድ ተናግሯል።

"ወደ ተሽከርካሪው ወሰዱኝ እና እጄን አስረው ወደ ውስጥ ገፍተው አስገቡኝ" ሲል አክሏል።

"አንድ የቫግነር ወታደር ቢላዋ ወስዶ በጣቴ ላይ አደረገውና 'የሱቁ ባለቤት የት ነው?' ሲል ጠየቀኝ። በዋና ከተማው ባማኮ እንዳለ ነገርኩት፣ እሱ ግን 'የተሳሳተ መልስ' ሲል መለሰ።"

አህመድ በአስተርጓሚ የሚነጋገሩት የቫግነር ሰዎች ከዚያም ወደ ማሊያ ወታደራዊ ጣቢያ ወስደውት በአንድ የአውሮፕላን ማቆሚያ መጋዘን ውስጥ እንዳስቀመጡት ተናግሯል።

"እኔና ሦስት የቫግነር ሰዎች በመጋዘኑ ውስጥ ነበርን። አንድ በርሜል በውሃ ሞልተው ልብሴን እንዳወልቅ አዘዙኝ። እኔም አደረግኩት። አየር አጥሮኝ እስከምወድቅ ድረስ ጭንቅላቴን በውሃ ውስጥ ነከሩት። ከዚያም እግራቸውን ደረቴ ላይ ሲያደርጉት ቁና ቁና መተንፈስ ጀመርኩ።"

"ከዚያም ጭንቅላቴን እንደገና በውሃ ውስጥ ነከሩትና ስለ ሱቁ ባለቤት ለሁለተኛ ጊዜ ጠየቁኝና ባማኮ ውስጥ እንዳለ ነገርኳቸው" አህመድ ስቅይቱ ለሦስተኛ ጊዜ እንደተደገመ እና ተመሳሳይ መልስ እንደሰጠ ተናግሯል።

ከዚህ ፈተና በኋላ አህመድ ወደ አንድ ትንሽ የመጸዳጃ ቤት እንደተወረወረ ተናግሯል፤ እዚያም የሚያውቃቸው ሌሎች የአካባቢው ሰዎች ነበሩ - ሁሴንን ጨምሮ፣ በጣም ስለተደበደበ መጀመሪያ ላይ ሊያውቀው አልቻለም።

"ከ40 ደቂቃዎች ገደማ በኋላ ኡመርን [ሌላ የሚያውቀው ሰው] አመጡት። እሱም በጣም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነበር። አሠቃዩት። በዚያ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ተኛን፤ በማግስቱ ጠዋት ዳቦና ትንሽ ቡና ይዘው መጡ" ይላል አህመድ።

ከዚያም ወደ መጋዘኑ እንደተወሰደ እና የሩሲያ ተዋጊዎች ፊቱ እና ጭንቅላቱን ሸፈኑት።

"ማየት አልቻልኩም። መናገር አልቻልኩም። መስማት አልቻልኩም። ቢላ ጉሮሮዬ ላይ አድርገው አስተርጓሚውን ይህ የመጨረሻው ዕድል እንደሆነ እንዲነግረኝ ነገሩት። እውነቱን ካልነገርኳቸው አንገቴን ይቆርጡኝ ነበር። የማውቀውን መረጃ ሁሉ እንደሰጠኋቸው አስተርጓሚውን ነገርኩት።"

አህመድ የሩሲያ መርማሪዎቹ ማሰሪያውን አውልቀው ሌሊቱ ነው ከሌሎች ሁለት የማያውቃቸው ሰዎች ጋር እንዲያሳልፍ ኩሽና ውስጥ ጣሉት።

ሌሊቱን ከአህመድ ጋር ያሳለፉት ሰዎች ለምን እንደሆነ ሳያውቅ ከብት ከሚጠብቅበት የታሰረ የቱዋረግ ጎሳ አባል እና ግመሎቹን ሲፈልግ የታሰረ አንድ የአረብ ሰው ናቸው።

ግመል ላይ የተቀመጠ ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

በሰሜናዊ ማሊ ሰፊ በረሃዎች ውስጥ የሚዘዋወሩት የቱዋረግ እና የአረብ ማኅበረሰቦች በጥርጣሬ ይታያሉ። ለዚህ ምክንያቱ ከአስር ዓመት በፊት የቱዋረግ አመጽ አሁን በጃማአት ኑስራት አል-ኢስላም ዋል-ሙስሊሚን በሚል ስም በሚንቀሳቀሰው ጂሃዲስቶች መጠለፉ ነው።

አህመድ ሌሊቱን ከእነሱ ጋር ካደረ በኋላ ወደ መጋዘኑ ተወሰደ።

"ሁለቱን ሰዎች አምጥተው ዐይኔ እያየ ፊት ለፊቱ አንገታቸውን አረዷቸው" ሲል አህመድ ተናግሯል።

አህመድ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ለቢቢሲ ሲናገር እንባውን ለመግታት ሲታገል ነበር።

"ከአስከሬኖቹ አንዱን ወደ እኔ አቀረቡትና 'የሱቁን ባለቤት የት እንዳለ ካልነገርከን ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይደርስብሃል።'"

አህመድ ሕይወቱ የተረፈው አንድ የቫግነር አዛዥ ለማሊ የጦር መኮንን ደውሎ የሱቁ ባለቤት ከጂሃዲስቶች ጋር እንዳልተባበረ ካረጋገጠለት በኋላ ነው።

አህመድ አዛዡ እሱንም ሆነ ሌላ የሱቅ ባለቤትን እና ኡመርን ለመልቀቅ ወደ ሰፈሩ እንደሄደ ተናግሯል።

"ለ15 ቀናት እዚያ አሳልፌያለሁ። ከዚያም ከባለቤቴ እና ከልጆቼ ጋር ወደ ሞሪታኒያ ለመሄድ ወሰንኩ" ብሏል አህመድ።

ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡ የሩሲያ እና የማሊ የመከላከያ ሚኒስቴርን የጠየቀ ቢሆንም፣ ነገር ግን እስካሁን ምላሽ አልሰጡም።

በተዋናይ ጆርጅ ክሎኒ እና በቀድሞ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ጆን ፕሬንደርጋስት በጋራ የተቋቋመው 'ዘ ሴንትሪ' የተባለው የዘመቻ ቡድን በነሐሴ ወር በወጣው ሪፖርት ላይ የቫግነር ተዋጊዎች በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን ብቻ ሳይሆን በማሊ ወታደራዊ ተዋረድ ውስጥም "ግርግር እና ፍርሃት" ፈጥሯል፣ ይህም አዛዦች ዝም እንዲሉ አስገድዷቸዋል።

ሪፖርቱ አንድ የማሊ ባለሥልጣንን የቫግነር ኦፕሬተሮች "ከፈረንሳዮች የባሱ ናቸው። ሰዎቹ ከእነሱ የበለጠ ሞኞች እንደሆኑ ያስባሉ። 'ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ' ነው የሆነብን" ማለታቸውን ጠቅሷል።

ቫግነር የፀጥታ ሁኔታው እየተባባሰ ቢሄድም ተልዕኮው "መሳካቱን" በመግለጽ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ከማሊ መውጣቱን አስታውቋል፣ ተንታኞች አብዛኛዎቹ ተዋጊዎቹ በአፍሪካ ኮርፕስ ውስጥ እንደተካተቱ ተናግረዋል።

በሴኔጋል የሚገኘው የቲምቡክቱ ኢንስቲትዩት ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ኮርፕስ ተዋጊዎች ቀደም ሲል በቫግነር ውስጥ እንደነበሩ ይገምታል።

"እንደ እውነቱ ከሆነ አፍሪካ ኮርፕስ የቫግነርን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ከፍርድ ውጪ ግድያዎች እና የማሰቃየት ድርጊቶችን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይወርሳል" ሲል በሐምሌ ወር ባወጣው ሪፖርት ላይ ገልጿል።

ሆኖም፣ የግጭት ክትትል ቡድን አክሌድ እንደገለጸው ቀደምት አዝማሚያዎች የአፍሪካ ኮርፕስ ድርጊት ከቫግነር "ያነሰ" እንደሆነ ይጠቁማሉ።

"ሆነ ተብሎ የሚፈጸሙ የሲቪል ግድያዎችን ወይም የጅምላ ጭፍጨፋዎችን የሚያካትቱ ክስተቶች ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ ቀንሷል" ሲሉ የአክሌድ የምዕራብ አፍሪካ ከፍተኛ ተንታኝ ሄኒ ንሳይቢያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቫግነር አርማ በተዋጊ ክንድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ገለጻ፣ ግጭቱ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሞሪታኒያ ወደሚገኘው የምቤራ የስደተኞች ካምፕ እንዲሸሹ አስገድዷቸዋል።

ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት የባለቤቷ አስከሬን በወንዝ ውስጥ ከተጣለ በኋላ ከአምስት ልጆቿ ጋር ከመንደሯ እንደሸሸች ለቢቢሲ የተናገረችው ቢንቱን ይጨምራል። የአካባቢው ሰዎች ፈረሱ ላይ ሲጋልብ በተደጋጋሚ በጥይት እንደተመታ ነግረዋታል።

"ልጆቼን የሚንከባከበው ማነው? ማን ይንከባከበኛል?" ስትል ትጠይቃለች።

"ቫግነር የሚለውን ስም ስሰማ፣ በጣም እፈራለሁ። ቫግነር የሚለውን ቃል እጠላዋለሁ ምክንያቱም ሐዘን አምጥተውብኛል።"

ፈዛዝ ሰማያዊ ልብስ እና ነጭ ጥምጣም ለብሶ የዛፍ ጥላ ስር የተቀመጠውን ዩሱፍ ቢቢሲ ሲያገኘው ዐይኖቹ የገጠመውን የስሜት ቀውስ ያንጸባርቁ ነበር።

እሱ እና ጓደኞቹ ከሩቅ የአቧራ ብናኝ ሲያዩ በሞሪታኒያ ድንበር አቅራቢያ ከብቶችን እየጠበቁ እንደነበር እና ንጹህ ውሃ ለማግኘት አንድ ጉድጓድ አጠገብ ቆመው እንደነበር ያስታውሳል።

ዩሱፍ እንደተናገረው አንድ ተሽከርካሪ ወደ እነሱ በፍጥነት እየመጣ ነበር፣ ይህ ተሽከርካሪ ያለምንም ምክንያት ሰዎችን መደብደብ የጀመሩት የቫግነር ተዋጊዎች ነበር። በርካታ ስደተኞች ይህ ተሞክሮ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዩሱፍ አንድ የቫግነር ተዋጊ "ይዞኝ ወደ ጉድጓዱ ውስጥ እንደሚጥለኝ ዛተ" ሲል ያስታውሳል፣ ነገር ግን ሌላ ሰው ጣልቃ ገብቶ ታድጎታል።

ከዚያም እሱ እና ጓደኞቹ ሦስት የቫግነር ወታደሮችን ወደያዙ ተሽከርካሪዎች ውስጥ እንደተጫኑ ተናግሯል።

"እየነዱ እያለ፣ ሙሉ በሙሉ ደበደቡኝ፣ ረግጠውኝ፣ ጫማቸውን ፊቴ እና ጭንቅላቴ ላይ በመጫን፣ ደረቴ ላይ መቱኝ። ከብቶቻችን ምን እንደደረሰባቸው አላውቅም።"

የቆሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ከጓደኞቹ ጋር ከሌሬ ከተማ በስተሰሜን ወደሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ተወሰደ፣ እዚያም ስቅይት እንደተፈጸመባቸው ተናግሯል።

"አንድ ሰው የብረት ዘንግ ይዞ መጣ። በጣም ስለደበደበን ልሞት እንደሆነ ተሰማኝ። እንዳንንቀሳቀስ እጃችንን አሰሩት፣ እንዳንሸሽ ታፋችንን እና እግሮቻችን ላይ በኃይል መታን።"

ዩሱፍ ከዚያም ወደ ቢሮ እየተጎተቱ እንደተወሰዱ ተናግሯል፣ ድብደባው ራሱን እስከሚስት ድረስ እንደቀጠለም ተናግሯል።

ሲነቃ እጆቹን ከጓደኞቹ በአንዱ እንቅስቃሴ አልባ እጆች ጋር ታስሮ እንዳገኘ አክሏል።

"ከዚያም ሞተር ሳይክል ወደ ፊቴ አቀረቡ፣ ሞተሩን አስነሱት፣ እና ጭስ ወደ አፍንጫዬ ውስጥ በማስገባት ሙሉ በሙሉ ከእንቅልፌ እንድነቃ አደረጉኝ። ለጓደኛዬም እንዲሁ አደረጉለት፣ ግን ምላሽ አልሰጠም። ያኔ ነው እንደሞተ የተረዱት።"

ዩሱፍ የጓደኛው አስከሬን ምን እንደተደረገ እንደማያውቅ ተናግሯል፣ ነገር ግን እሱና ሌሎች ጓደኞቹ ያለምንም ማብራሪያ ተለቀቁ።

የቀድሞው የሱቅ ጠባቂ አህመድ፣ ከደረሰበት የማሰቃየት ተሞክሮ በፊት፣ ቫግነር በአንድ ወቅት መላውን የናምፓላ ከተማ እና በዙሪያው ያሉትን መንደሮች ከበባ ውስጥ በማስገባት የጅምላ ግፍ እንዴት እየፈጸመ ማየቱን ተናግሯል።

የሳተላይት ስልክ የሚጠቀመውን ሰው ለመለየት በእግር ኳስ ሜዳ ላይ እንዲሰበሰቡ ካስገደዱ በኋላ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግሯል።

"ሲኩ ሲሴይን ጠሩት። ባህላዊ ኮፍያ የለበሰ ሰው ነበር። ልብሱን አውልቀው በርሜል በውሃ ሞልተው እግሩን ያዙት። ከዚያም መተንፈስ እስኪያቅተው ድረስ ጭንቅላቱን በርሜል ውስጥ ነከሩት" ሲል አህመድ ተናግሯል።

የማሊ ወታደሮች እየተመለከቱ እያለ፣ የቫግነር ተዋጊዎች አካፋዎችን እና ዶማዎችን ወደ እግር ኳስ ሜዳ አምጥተው ሰዎች የሳተላይት ስልኩን እየተጠቀመ ያለውን ሰው ካልጠቆሙ በስተቀር የራሳቸውን መቃብሮች እንደሚቆፍሩ እንዲያስቡ አስፈራርተዋቸዋል ሲል አህመድ አክሏል።

ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ውስጥ ከቆዩ በኋላ በቅጥረኛ ተዋጊዎቹ ከተወሰደ እና ስለ ዕጣ ፈንታው ከማያውቀው ሰው በስተቀር ነዋሪዎቹ እንደተለቀቁ ተናግሯል።

አህመድ የቫግነር ተዋጊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እና ለፈጸሙት ግፍ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

በካምፑ ውስጥ ጥቁር ልብሱን እንደለበሰ በተቀመጠበት "ይህ ተሞክሮ ያስጨንቀኛል። ቅዠቶችን ይፈጥርብኛል" ይላል። ወደ መደበኛው የሱቅ መጠበቅ ሥራ ስለመመለሱ እርግጠኛ አልነበረም።