የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመራ ገቡ

 የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስመራ ሲገቡ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስመራ ሲገቡ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመራ መግባታቸው ተገለጸ።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስቴር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው እንዳስታወቁት ዛሬ ታኅሣሥ 16/2017 ዓ. ም. የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስመራ ሲገቡ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

መሪዎቹ "የሁለትዮሽ ግንኙነትን ስለማጠናከር እንዲሁም የጋራ ጠቀሜታ ስላላቸው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ይወያያሉ" ሲሉም አቶ የማነ ገልጸዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ወደ አስመራ ከማቅናታቸው ከሁለት ቀናት በፊት አገራቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር ጥሰው የሶማሊያ ጦር ላይ "ጥቃት ሰንዝረዋል" ብላ መክሰሷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አስተባብሎ ለክስተቱ ተጠያቂ "ሦስተኛ ወገኖች" ናቸው ማለቱም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ፣ አንካራ ከዓመት በላይ ሻክሮ የቆየ ግንኙነታቸውን አድሰው ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ውስጥ በነበሩበት ወራት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተደጋጋሚ ወደ አስመራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ታኅሣሥ 14/ 2017 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ይታወሳል።

ሰኞ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ዱሎው በተባለችው የጁባላንድ ከተማ "የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት ፈጽመዋል" ሲል ከሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ "የተስተካከለውን የሶማሊያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ማወክ በሚፈልጉ ኃይሎች የተፈጠረ ክስተት ነው" ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ማንነታቸውን ይፋ ያላደረገውና "ሦስተኛ ወገን" ያላቸው አካላት "የአፍሪካን ቀንድ ለመናጥ ቆርጠው የተነሱ የቀጣናው ሰላም አደፍራሾች" ናቸው ሲል ገልጿል።

ታኅሣሥ 15/ 2017 ዓ. ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ዓሊ ሞሐመድ ኦማር ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያው አቻቸው አብዱላሂ ሞሐመድ ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚድያቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ውስጥ በነበሩበት ወራት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተደጋጋሚ ወደ አስመራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተጉዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ ውስጥ በነበሩበት ወራት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተደጋጋሚ ወደ አስመራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተጉዘዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟን ተከትሎ ነው።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ እንዳለች ይታወቃል።

በተለይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ መተላለፊያ እንዲሁም ሚና እንዲኖራት ያላትን ፍላጎት ይፋ ካደረገች በኋላ በቀጥታም ባይሆን ኤርትራ ደስተኛ አለመሆኗን ስታሳይ ነበር።

በዚህም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኤርትራ ከሦስት ጊዜ በላይ ጉብኝት አድርገዋል።

ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ አስመራ ላይ የተፈረመው የሦስትዮሽ ስምምነት ከኢትዮጵያ አንጻር መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታኅሣሥ መባቻ ላይ በመንግሥታቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ስለወቅታዊ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ በሰጡበት ወቅት ግን ይህንን አስተባብለዋል።

ቱርክ በአገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ፕሬዝዳንቷን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት ለወራት ስትጥር ቆይታ ከስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።

የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንድታገኝ የሚያደርግ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።