በመቀለ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

በመቀለ የደረሰው የአየር ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Tigray Television

በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ በዛሬው ዕለት ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም የአየር ጥቃት መፈጸሙን የትግራይ ኃይሎች እና ነዋሪዎች ገለጹ።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የአየር ጥቃቱ የደረሰው መዋዕለ ህፃናት አካባቢ መሆኑን እና ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረገ ነው ሲሉ በዛሬው ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6፡30 የተፈጸመው ጥቃት በህፃናት ህንፃ፣ መኖሪያ፣ የህጻናት መዋያ እና መዋዕለ ህፃናት ላይ መሆኑንም የትግራይ ክልል ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን ሬድ ኪድስ ፓራዳይዝ የሚባል መሆኑን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ወታደራዊ አቅሞችን ዒላማ ያደረገ እርምጃ ይወስዳል ብሏል።

በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈው ምስል ላይ የፈራረሰ ህንፃ መሬት ላይ ቆስለው የወደቁ ህፃናትና ነዋሪዎች ያሳየ ሲሆን በጥቃቱ ሕፃናትን ጨምሮ የንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን ጣቢያው ዘግቧል።

የትግራይ ባለስልጣናት በዚህ ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ባይገልጹም በመቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረ ስላሴ ከሞቱት አራት ሰዎች መካከል ሁለት ህፃናት እንደሚገኙበት በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል።

የተጎዱሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ገልጸው ሟቾቹን ጨምሮ 13 የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

ሮይተርስ ያናገራቸው መቀለ ውስጥ የሚገኙ የረድኤት ድርጅቶች ባልደረቦች ፍንዳታዎች እና የአየር መቃወሚያ ተኩስ መስማታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ “የተመረጡ የጁንታውን ወታደራዊ አቅሞች” ይመታል ከማለት ውጪ ዛሬ የአየር ጥቃት ስለመፈጸሙም ሆነ ዒላማ ስለሆነው ቦታ ያለው ነገር የለም።

ሆኖም “በትግራይ የምትኖሩ ወገኖቻችን በተለይም የህወሓት ወታደራዊ መሳሪያዎች እና ማሠልጠኛዎች ካሉባቸው አካባቢዎች ራሳችሁን እንድታርቁ ይመክራል” ብሏል መግለጫው።

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሁለቱም ወገኖች ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ እያቀረበ ባለበት ወቅት ዐቢይ አሕመድ አየር ኃይሉን ልኮ በመቀለ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲደርስና በዚህም ወቅት መዋዕለ ህፃናት አካባቢ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል።

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደገና አገርሽቶ ለሦስተኛ ቀን ቀጥሏል።

የጦርነቱ ማገርሸት እንዳሳሰባቸውና ተፋላሚ ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ጥሪ አቅርበዋል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ አመራሮች መካከል ተደርሶ የነበረው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ከቀናት በፊት የተጀመረው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።

በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብአዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የእርስ በእርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም አዋቅረናል ቢሉም በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀሱ የሰላም ሂደቱን አደጋ ላይ ጥሎታል።