ብራዚል በተጫዋቿ ላይ የተፈጸመውን የዘረኝነት ጥቃት አወዘገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከቱኒዝያ ጋር በነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ተመልካቾች አጥቂው ሪቻርለሰን ላይ ሙዝ እና ሌሎች ነገሮችን በመወርወር የዘረኝነት ጥቃት መድረሱን ብራዚል አወገዘች።
ፓሪስ ላይ ለቱኒዚያ ጋር በተካሄደው ጨዋታ ብራዚል 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።
የቶተንሃሙ አጥቂ የጨዋታውን ሁለተኛ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ድርጊቱ መፈጸሙ ታውቋል።
ከጨዋታው በኋላ የብራዚል እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ሲቢኤፍ) ባወጣው መግለጫ “ዘረኝነትን ለመዋጋት አቋሙን እንደሚያጠናክር እና የትኛውንም ጭፍን ጥላቻ እንደማይታገስ” አስታውቋል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት ብራዚል ተጫዋቾች ዘረኝነት የሚያወግዝ መልዕክት ይዘው ነበር።
የቡድኑ አባላት “ካለጥቁር ተጫዋቾቻችን ማሊያችን ላይ ያሉትን ኮከቦች አናሳካም ነበር” የሚል መልዕክት አስተላለፈዋል።
የሲቢኤፍ ፕሬዝዳንት ኤድናልዶ ሮድሪጌዝ በበኩላቸው “ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ እንዲህ ያሉ ባህሪያት ተቀባይነት የላቸውም” ብለዋል።
በጨዋታው ብራዚል በራፊንሃ ጎል ቀዳሚ ለመሆን በቅታለች።
ቱኒዝያ በሞንታሳር ታልቢ ጎል አቻ በመሆን ወደ ጨዋታው መመለስ ብትችልም ሪቻርልሰን በድጋሚ ብራዚል ቀዳሚ አድርጓል።
ኔይማር በፍጹም ቅጣት ምት ቡድኑ 3 ለ 1 እንዲመራ ያስቻለችውን ጎል አስቆጥሯል።
ራፊንሃ ለቡድኑ አራተኛውን ለራሱ ደግሞ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።
65 በመቶ የኳስ ቁጥጥር የነበራት ብራዚል አምስተኛውን ጎል በፔድሮ አማካይነት አግኝታለች።
በሁለቱ አገራት መካከል ፈረንሳይ ውስጥ የተካሄደው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ በመጪው ኅዳር ወር ኳታር ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ዝግጀት የተደረገ ነበር።
ብራዚል ከደቡብ አሜሪካ ቱኒዚያ ደግሞ ከአፍሪካ በዚህ የዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉ ቡድኖች መካከል የሚገኙ ናቸው።












