በአራብሳ በሁለቱ ሕጻናት ላይ የደረሰው አደጋ እንዳይደገም ምን እናድርግ?

ልጇን ጡት የምታጠባ እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአራብሳ ከወር በፊት የሆነው ከተሰማ ወዲህ ሺህ እናቶች ከቀልባቸው አይደሉም። በሥራ መሀል ይበረግጋሉ።

በአካል መሥሪያ ቤት ይሁን እንጂ ልባቸውን ቤት ጥለውት ነው የሚወጡት።

ሠራተኞቻቸው ጋር ደጋግመው ይደውላሉ።

“ልጄን አገናኝኝ!”፤ “ሚጣ ደህና ነሽ?” መልሰው መላልሰው ይጠይቃሉ።

ተበድረው ካሜራ ያስገጠሙም አሉ። በባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚንየም ውስጥ ባለ ሦስት ዓይን ካሜራ።

ወደው አይደለም። ወጥተው እስኪገቡ በልጆቻቸው ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።

በዚህ የተነሳ መቦረቅ ያለባቸው ሕጻናት ቤት ተቆልፎባቸው ነው የሚውሉት።

የእናቶቻቸው ፍርሃት ልጆች ላይ አልተጋባም አይባልም።

ሺህ ሕጻናት ከቤት ሠራተኞች ጋር ተፋጠው ነው የሚውሉት።

ሺህ ሕጻናትን በባዕድ ቋንቋ የሚለፍፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው የሚያሳድጋቸው። በኮሪያ ቋንቋ የሚዘምሩ ልጆች ተፈጥረዋል።

አዲስ አበባ ለብዙ ሕጻናት እስር ቤት ሆናለች።

ከዚህ ሰፊ እስር እንዴት እናውጣቸው? በግማሽ ልብ ሥራ የሚሠሩ እናቶችን እንዴት እንታደግ?

ልጅ ያቀፈች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልጆች መሥሪያ ቤት ለምን አይውሉም?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንዲት ልጆች ያሏት ሴት ሚኒስትርን እና አንዲት ጉሊት ቸርቻሪን ምን አንድ ያደርጋቸዋል?

እናትነት።

በዚህ ወቅት ሁለቱንም እጅግ የሚያስጨንቅ ጉዳይ ምንድነው?

የልጅ ጉዳይ።

“እኔ ሥራ ስውል ልጄ እንዴት ዋለች?” የሚለው ጥያቄ በብርቱ ያሳስባቸዋል።

ይህ ነገር መንግሥትንም ቀደም ብሎ አሳስቦት ከአራት ዓመት በፊት በሴቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር በኩል አዋጅ አውጥቶ ነበር።

አዋጁ፣ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሴት ሠራተኞች ከሦስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩበትና ጡት የሚያጠቡበት ማቆያ የማቋቋም ኃላፊነትን ይጥላል።

አዋጅ ካለ ታዲያ ማቆያ በብዛት የሌለው ለምንድነው? ብለን መጠየቅ ሳይኖርብን አይቀርም።

ወ/ሮ ጽጌ ታደለ በሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የአካቶ ትግበራ (mainstreaming) ክትትልና ቁጥጥር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

አዋጁ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሕጻናት ማቆያ እንዲያቋቁሙ ግዴታን ይጥላል፤ ለዚህም በአገር ደረጃ በአጭር ጊዜ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ወ/ሮ ጽጌ ያወሳሉ።

አክለውም፣ የእናት ሠራተኞችን ፈተና ለመቀነስ በሚል በተደረገ ርብርብ፣ በአጭር ዓመታት በአገር ደረጃ 382 የልጆች ማቆያዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መዘጋጀታቸውን አብራሩ።

ይህ ቁጥር እርሳቸው አበረታች ይበሉት እንጂ፣ ጠቅላላ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አሐዝ ስንሰማ የሚያስቆዝም ይሆናል።

በቅድሚያ በአገር ደረጃ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ጽሕፈት ቤቶች እና ሌሎች የክልል የመንግሥት መዋቅሮች ቁጥር 1871 መሆኑን ልብ እንበል፤ በተዋረድ።

ወደ ሁለት ሺህ ከሚጠጉት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ነው ታዲያ 382 ማቆያዎች አሉ የሚባለው።

ይህንን አሐዝ ግን ቆም ብሎ ላስተዋለ ብዙ ሺህ እናት የመንግሥት ሠራተኞች ብዙ መከራ ውስጥ መሆናቸውንም አብሮ ያሳብቃል።

“አዲስ ሐሳብ ነው፤ እናት የመንግሥት ሠራተኞች በልጆቻቸው ምክንያት ሥራ እየቀሩ ችግር መፈጠሩ በዳሰሳ ጥናት ስለተደረሰበት ነው አዋጅ የወጣው።... እዚህ የተደረሰውም ብዙ ተሠርቶ ነው፤ እኛ በቂ ነው ባንልም በበጎ ነው የምንመለከተው” ይላሉ ወ/ሮ ጽጌ።

አንዲት የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጽዳት ሠራተኛ ልጇን ለማን ትስጠው? ማን ይንከባከብላት? ሠራተኛ መቅጠርስ ትችላለች? አቅሙስ አላት?

የእርሷን ስቃይ ለሴኮንዶች ማሰብ ምናልባት ስለምን እያወራን እንደሆነ ለመደራት ይረዳ ይሆናል።

በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ያለው የህጻናት ማቆያ በከፊል

የፎቶው ባለመብት, ministry of education

የምስሉ መግለጫ, በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ያለው የህጻናት ማቆያ በከፊል

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለምን አይገደዱም?

ሴቶች ከልጅ መምጣት በኋላ በብዙ ግንባር ይፈተናሉ። የቤት ሠራተኛን ማግኘት አንዱ ግንባር ነው።

ስንት እናቶች የቤት ሠራተኛ ወጪን መሸፈን ይችላሉ? የሚለውም ሌላው ቁልፍ ጥያቄ ነው።

“ልጄንማ ለሠራተኛ ጥዬ አልወጣም” ብለው ከሥራ የቀሩትን ቤታቸው ይቁጠራቸው።

ይህ ደግሞ በሴቶች የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ላይ ትልቅ ፈተናን የደቀነ ነው።

እናትና ልጅን እንዴት ከዚህ ‘ደብዛዛ እስር ቤት’ እናውጣቸው ሲባል አንዱ አማራጭ የልጆች ማቆያን በሥራ ቦታ አስገዳጅ ማድረግ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የልጆች ማቆያ መገንባቱ ለብዙ እናቶች እፎይታን ሰጥቷል።

ችግሩ ታዲያ ለሁሉም ተደራሽ አለመሆኑ ላይ ነው።

የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በ2010 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕጻናት ማቆያ ማዕከል የአሠራር መመሪያ አውጥቶ ነበር።

የመመሪያው ዓላማ ሁለት መልክ አለው። አንደኛው እናቶች ተጨነቁ። ከሥራ ተሰናከሉ።

ሁለተኛው ልጆች ዕድገታቸው ተስተጓጎለ። በአእምሮ ቀነጨሩ።

በተለይ ሕጻናት እናቶቻቸው ሥራ ሲሄዱ ይቆዝማሉ። እናቶች ይጨነቃሉ። ልባቸው ክ-ፍ-ል ይላል።

ስለዚህ የሕጻናት ማቆያን በመሥሪያ ቤት ግዴታ እንዲሆን ተደረገ።

መመሪያው ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ማቆያዎችን በራሳቸው ወጪ እንዲሸፍኑ ያስገድዳል። ብዙ መሥሪያ ቤቶች ግን በጀት የለንም ይላሉ።

ለተለያዩ ጉዳዮች በርካታ ገንዘብ የሚያወጡት ተቋማት ለሴት ሠራተኞቻቸው አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር የገንዘብ ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ።

ፈረስ የሚያስጋልብ ግቢ ይዘው የቦታ እጥረት ገጠመን ይላሉ።

በግቢያቸው ውስጥ ችግኝ እየተከሉ ‘ለዛሬ አበቦች፣ ለነገ ፍሬዎች’ ሲሆን ግን ቦታ ከየት ይምጣ ይላሉ።

ሰበባቸው በጀትና ቦታ ብቻ አይደለም። የሰለጠኑ ሞግዚቶችን አጣን የሚሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አልጠፉም።

ይህ እምብዛም ስሜት የሚሰጥ አይመስልም።

ወ/ሮ ጽጌ ግን የአመለካከት እና አዋጁን ያለመቀበል ችግር በመሥሪያ ቤቶቹ የሚስተዋል ቢሆንም፣ በትክክልም የተዘረዘሩት ማነቆዎች እንደሚገጥሙ ይከራከራሉ።

በዚህም ከጠቅላላ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሰባት የሚሆኑት የልጆች ማቆያ የላቸውም።

“ኢንሳ በዚህ ረገድ መመስገን ያለበት መሥሪያ ቤት ነው። ወደ መቶ ሕጻናት የሚስተናገዱበት በጣም ሰፊ ቦታ፣ ደረጃውን የጠበቀና ወደ 1 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሕጻናት ማቆያ አዘጋጅቷል። የአመራር ቁርጠኝነት ስላለ ነው ይህን ማሳካት የቻሉት፤ ሌላ ምክንያት የለውም” ብለዋል ወ/ሮ ጽጌ።

በነገራችሁ ላይ ፓርላማ ግቢ፣ ገቢዎች፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ጤና ጥበቃም የልጆች ማቆያ እንደነገሩ በማዘጋጀት ምሳሌ መሆን የቻሉ ናቸው።

ለመሆኑ የትኞቹ መሥሪያ ቤቶች ይሆኑ እንደ ክፉ ሠርግ ጠሪ፣ “ለልጅ ቦታ የለንም” እያሉ ያስቸገሩት?

የወላጅና የልጅ ጥላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘ደላሎች የአእምሮ ህሙማንን በሠራተኞችን ያስቀጥራሉ’

በአገሪቱ ያሉ መሥሪያ ቤቶች የሕጻናት ማቆያ እስኪገነቡ ሌላ ምን መሠራት ይችላል?

ብሌን አስራት፣ ‘ትምራን’ አገር በቀል ድርጅትን በምክትል የቦርድ ሰብሳቢነት ትመራለች።

በአራብሳ ኮንዶሚኒየም ከወር በፊት የተሰማው ዜና፣ “...በተለይ ሥራ ውለው ለሚገቡ እናቶች ፍጹም አስደንጋጭ ነበር” ትላለች።

“ታውቀው እንደሁ አላውቅም፤ ሴቶችን የሚመለከቱ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የምንመክርበት መድረክ አለን። ሰሞኑን ትልቅ አጀንዳችን በቃ እሱ ነበር።”

ብሌን ሠራተኞችን የምንቀጥርበት ባህላዊው የደላሎች መስመር ራሱ መፈተሽ እንዳለበት ታነሳለች።

“ደላሎች የሰጡንን ነው የምንወስደው፣ ሙያቸውን ይቅርና ጤንነታቸውን የምናረጋገጥበት መንገድ የለም። ደላሎቹ ተጠያቂ ሆነውም አያውቁም።”

ብሌን የምትለው ነገር ስሜት ይሰጣል። ብዙ እናቶች በደላላ ተታልለዋል። የደላላ ነገር በቃን ብለው አገር ቤት ዘመድ ፍለጋ የተጓዙ፣ የዘመድ ልጅ ለማሳደግ የተገደዱ ብዙ ናቸው።

ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ ሌላ የኢኮኖሚ ጫናን ይፈጥራል።

በሠራተኛ ጣጣ ተማርረው ልጅ ደግሞ ለመውለድ የነበራቸውን ሐሳብ በድጋሚ ለማጤን የተገደዱ ወጣት እናቶች የሉምን?

ብዙዎቹ ችግሮች ታዲያ ከአፈ ጮሌ ደላሎች ይመነጫሉ።

“ደላሎች አስቸጋሪ ናቸው፤ በእኔ ልምድ እንደማስታውሰው ሠራተኛዋ ስሟን እንድትናገር ሁሉ ዕድል አይሰጧትም። በቃ ጎበዝ ናት የማትችለው ነገር የለም ይላሉ። ሕጻን ትወዳለች፣ የፈረንጅ ምግብ ትችላለች፣ ባለሙያ ናት ይላሉ። እነሱ በቃ ኮሚሽናቸው ነው የሚያስጨንቃቸው።”

በእርግጥ ደንበኛው ከሠራተኛዋ ጋር ተግባቦት እንዳይኖረው ደላሎች የሚከላከሉት ያለ ምክንያት አይደለም። “እንዳትዘላብድ” ነው።

“የትኛው ቤት ስንት ዓመት ሠራች፣ ከዚያ ቤት በምን ምክንያት ወጣች፤ ማንም አያውቅም” ደላላውን ጨምሮ።

ብሌን የቤት ሠራተኞችን የቀድሞ ታሪካቸውን የምናውቅበት መንገድ መፈጠር አለበት ትላለች።

ከዚህም በመነሳት በአጭር ጊዜ አንድ ልናስተካክል የምንችለው ነገር ደላሎችን ማሰልጠን ነው ብላ ታምናለች።

የአራብሳው አደጋ ከተሰማ በኋላ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ብዙ ጉድ ይዘው ወጥተዋል።

አንዳንድ የአእምሮ መታወክ የገጠማቸው ሠራተኞች ከሕጻን ልጅ ጋር ትንቅንቅ የገጠሙበት አጋጣሚም ተወስቷል።

ሌሊት ስትጮኽ የተሰማች የቤት ሠራተኛ ያጋጠማት እመቤት በጭንቅ ወደ ደላላ ብትደውል ጊዜ፣ “ውይ ተነሳባት ማለት ነው? በቃ ሌላ ልቀይርልሻ አምጪያት” ያለ ደላላም አልጠፋም።

“ሥልጠና የግድ ያስፈልጋቸዋል፤ ትርፉ ለእኛም ለእነሱም ነው፤ በሆነ መንገድ ተጠያቂ እንዲሆኑም መደረግ አለበት” ትላለች ብሌን።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሴት ደላሎች ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑ ደግሞ ሌላ ተስፋ ነው።

እነ ብሌን ባደረጉት ውይይት ከተነሱ ነጥቦች አንዱ ደላሎች “ከአእምሮ ሆስፒታል አምልጠው የወጡ ሠራተኞችን ያስቀጥራሉ” የሚለው ነበር።

በእርግጥም ችግሩ አስፈሪም አሳሳቢም ነው። ልጅ ትወዳለች ተብላ የመጣች የቤት ሠራተኛ፤ “ልጆቹን ሳያቸው እነቂያቸው፣ እነቂያቸው ይለኛል” የምትል ሆና ስትገኝ ነገሩ እንዴት አሳሳቢ አይሆንም?

ለ

በየሰፈሩ ሕጻናት ማቆያ ማዘጋጀት ከባድ ነው እንዴ?

አሁን ባለው እውነታ ሠራተኛ ማግኘት ብቻ አይደለም ፈተናው።

ሠራተኛዋ ከተገኘች በኋላም እናቶች ሥራ ቀርተው ፍቃድ ወስደው አዲስ ሠራተኛን የማሰልጠን የውዴታ ግዴታ አለባቸው።

አንዳንድ ቤት ሕጻናት በፍርሃት ቆፈን ቀኑን ሙሉ ውለው ነው ወላጆቻቸውን ማታ የሚያገኙት።

መሥሪያ ቤቶች ማቆያ ለማዘጋጀት ከለገሙ፣ የቤት ሠራተኞች ላይ እምነት ከታጣ፣ ደላሎች ግድ ከሌላቸው ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል?

እታፈራሁ በጉድ ሳማሪታን የፕሮግራም ኃላፊ ናት። የማኅበረሰብ ዕድገትና ትምህርት ላይ ሰፊ ተሞክሮ አላት።

ቀድሞ የጎልማሶች ትምህርት ላይ በምትሠራበት ወቅት ብዙ እናቶች ትምህርት ቤት ሲመጡ ሕጻናትን ይዘው ክፍል ይመጡ ነበር።

እናቶች ለመማር ነው የሚመጡት፤ የጎልማሳ ትምህርት። ልጆቹ ደግሞ ያስቸግሯቸዋል።

ከጊዜ በኋላ እናቶቹ ትምህርት መቅረት ጀመሩ።

“ምነው እማማ ትምህርት ቀሩሳ?” ሲባሉ “ልጄን ለማን ጥዬ፣ አንቺዬ!” ማለት ጀመሩ።

ችግሩን አይተን ለምን ለልጆቹ መቆያ አናዘጋጅም አልን ትላለች እታፈራሁ።

መላ መቱ። በየወረዳው በየቀበሌው ቦታ ፈለጉ። በጣም በትንሽ ወጪ የልጆች ማቆያ ሠሩ።

“ትምህርት ቤቶች የሆነች ጥግ እንዲሰጡን አደረግን። ፍራሽና ምንጣፍ ጨመርንበት። ከዚያ ወዲያ እናቶች ትምህርት መቅረት አቆሙ። ልጆቻቸው ሙሉ ቀን ቢውሉ ራሱ ደስተኛ ነበሩ።”

እነ እታፈራሁ ካዘጋጇቸው ውብ የሕጻናት ማቆያዎች አንዱ በአዲስ አበባ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኛል።

አሁን ቀን ላይ በፈለጋችሁት ሰዓት ወደዚህ ማዕከል ብትሄዱ በርካታ ሕጻናት እየቦረቁ ታገኛላችሁ።

እናቶቻቸው ጉሊት የሚሠሩ፣ የሶፍት ወረቀትና ፌስታል የሚቸረችሩ በኢመደበኛ ሥራ የተሠማሩ ናቸው።

አንዲት አትክልት ተራ ጎመን የምትሸጥ እናት ልጇን የት አስቀምጣው ጎመኗን ትቸርችር?

በኢመደበኛ ሥራ ውስጥ ያሉ እናቶች በዚህ ረገድ ፍዳቸውን ነው የሚበሉት።

በምኒልክ ትምህርት ቤት ማቆያ ልጃቸውን ጣል አድርገው ሥራ የሚበሩ እናቶች በወር ለአገልግሎቱ 350 ብር ብቻ ይከፍላሉ።

ይህ የከበዳቸው ምስኪን እናቶች ደግሞ በነጻ አገልግሎቱን ያገኛሉ።

“ወረዳው ተጻጽፎ፣ 6 ሥራ አጥ እናቶችን በሞግዚትነት አሰልጥኖ ነበር እንደዋዛ ይህ ሥራ የተጀመረው” ትላለች እታፈራሁ።

ትምህርት ቤቱም መመስገን ይገባዋል፤ ወረዳውም ጀግና ነው።

እታፈራሁ ከዚህ የልጆች ማቆያ በኋላ የነበረን የእናቶች የአእምሮ ሰላም አትረሳውም።

“እንዴት እንዳረፉ፣ እንዴት እንደሚደሰቱ፣ እንዴት ሕይወታቸው እንደተለወጠ።”

ልጆቹ ደግሞ እዚህ ምኒልክ ትምህርት ቤት ግቢ ሲቆዩ ከጊዜ በኋላ እኩዮቻቸውን መናፈቅ ጀመሩ።

ለዕድገታቸውም ምቹ ሆነ። በጣም ደስ ብሏቸው መዋል ጀመሩ።

እታፈራሁ በዚህ ሞዴል ሥራ ዛሬም ድረስ እርካታ ይሰማታል።

የሕጻናት ማቆያ በማኅበረሰብ ደረጃ ማሳካት እንደሚቻል በጽኑ ታምናለች።

በጀት የለንም፣ ቦታ የለንም የግዙፍ መሥሪያ ቤቶች ሰበብ ብዙም ስሜት የማይሰጣት ለዚሁ ነው።

በነገራችሁ ላይ ቅድም ይቆይ ብለናችሁ ነበር፤ የሕጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ሚኒስቴር ለሕጻናት ማቆያ የሚሆን ቦታ አለው።

“10 የሚሆኑ ልጆች ይስተናገዱበታል፤ ሞዴል እንዲሆን የተዘጋጀ ነው” ብላናለች ወ/ሮ ጽጌ።

መሥሪያ ቤቶች በቀላል ወጪ የልጅ ማቆያ ቢገነቡ የእናቶች ስቃይ ማቅለል ይችላሉ።

እነ እታፈራሁ ማቆያ ለማዘጋጀት ቅን ልብ እንጂ ሚሊዮን ብሮች እንደማያስፈልጉ አረጋግጠዋል።

“እኛ የምኒልክ ትምህርት ቤትን ስንጀምር ቦታው ቆሻሻ የሚቀመጥበት የድሮ ፋይል ማጠራቀሚያ ቦታ ነበር። እሱ ነው የ66 እናቶችና የ66 ሕጻናትን ሕይወትን የለወጠው” ትላለች።

ይህ የሚነግረን በብዙ ቦታዎች ተመሳሳይ ነገር መሠራት እንደሚቻል ነው።

ለምሳሌ በመስጊዶች እና አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ጭምር።

እታፈራሁ “የፍላጎት እንጂ የቦታ ችግር የለም” የምትለውም ለዚሁ ነው።

ለተለያዩ ዝግጅቶች እና የስፖንሰር ወጪዎች የሚውሉ ሚሊዮን ብሮች፤ የሚሊዮን እናቶችን ስቃይ ማስቆም እንደሚችል አለመዘንጋት ጥሩ ነው፤ አንዳንዴ።