በታንዛንያ በደቦ የተደፈረችን ሴት ከወሲብ ንግድ ጋር ያያዙት ፖሊስ ከኃላፊነት ተነሱ

የፎቶው ባለመብት, Tanzania Police
በታንዛንያ በደቦ የተደፈረችን ሴት ከወሲብ ንግድ ጋር በማያያዝ አስተያየት የሰጡት የፖሊስ ኮማንደር ከኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ስፍራ ተዛወሩ።
በመዲናዋ ዶዶማ አንዲት ሴት በቡድን ስትደፈር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ብስጭት እና ቁጣን ፈጥሯል።
ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉ አራት ወንዶች የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
በመዲናዋ የፖሊስ ኮማንደር የተደፈረችውን ግለሰብ አስመልክቶ “በወሲብ ንግድ ስራ ላይ የተሰማራች ትመስላለች” ሲሉ ለታንዛንያው ጋዜጣ ተናግረዋል።
የፖሊሷ አስተያየት የፈጠረውን ቁጣ እና ብስጭት ተከትሎ የታንዛንያ ብሄራዊ ፖሊስ ይቅርታ ጠይቆ ኮማንደሯ ወደ ሌላ ስፍራ መዛወራቸውን አመልክቷል።
“ፖሊስ በሚዲያዎች ላይ እየተሰራጨ ባለው አስተያየት የተነኩ እና የተበሳጩትን ሁሉ ይቅርታ ይጠይቃል” ሲሉ የብሔራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዴቪድ ሚስሜ ተናግረዋል።
ግለሰቧ ወደ ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት የተዛወሩ ሲሆን በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት መሆኑ አልተጠቀሰም።
ቃል አቀባዩ አክለውም የዶዶማ ግዛት ፖሊስ ኮማንደር ቴዎፒስታ ማልያ ለጋዜጣው በሰጡት አስተያየት ጥቃት የተፈጸመባት እንኳን “የወሲብ ንግድ ተዳዳሪ ብትሆን እንኳን በዚህ መንገድ ልትያዝ አይገባም” ሲሉ ተናግረዋል ብለዋል።
ሆኖም ይህ አስተያየታቸው በጋዜጣው ላይ እንዳልሰፈረ ቢቢሲ ተመልክቷል።
የጋዜጣውን ዘገባ አስመልክቶ ጠበቃው ፒተር ማዴሌካ የፖሊስ ኮማንደሯ አስተያየት “ ፖሊሶች በሴቶች መብት ላይ ያላቸውን ጭካኔ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
የህግ ባለሙያዋ እና ታዋቂዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ፋጢማ ካሩሜ “በወሲብ ንግድ የሚተዳደሩ ሴቶች እዚህች አገር ሊደፈሩ አይችሉም ማለት ነው?” ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
ወጣቷ ሴት ስትደፈር በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ ተጠርጣሪዎቹ “አፋንዴ” የተባለ ሰውን ይቅርታ እንድትጠይቅ ሲያስገድዷት ይታያል።
በታንዛንያ አፋንዴ እየተባሉ የሚጠሩት ወታደሮች ወይም ፖሊሶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በርካታ ተሟጋቾች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የተደፈረችው በጸጥታ ኃይሎች ሳይሆን እንዳልቀረ እየተናገሩ ነው።
ይህ የደቦ ወሲባዊ ጥቃት ቪዲዮ በማን እንደተቀረጸ ባይታወቅም ተጠቂዋ የዮምቦ ዶያ ሰፈር ልጅ እንደሆነች ታውቋል። ዮምቦ ዶያ ከዳሬሰላም ወጣ ብላ የምትገኝ ቦታ ናት።
ሰኞ እለት አራት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በደቦ በመድፈር እና ተፈጥሯዊ ያልሆነ ድርጊት በመፈጸም ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ግለሰቦቹ ማስተባበላቸው ተዘግቧል።












