ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ የገባችው ዩክሬን በአንድ በሳምንት ሁለተኛውን ድልድይ መደምሰሷን አስታወቀች

ዩክሬን ጥቃት ካደረሰችበት ድልድይ ቪድዮ ላይ የተወሰደ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian Armed Forces

ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ዘልቃ የገባችው ዩክሬን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሩሲያ ጦር ወሳኝ የተባለ ሁለተኛውን ድልድይ ማውደሟን አስታወቀች።

የዩክሬን መከላከያ ሠራዊት እሑድ ዕለት ይፋ ባደረገው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ ድልድዩ ሲደመሰስ አሳይቷል። ድልድዩ ዝቫኖ በተባለው አካባቢ ሰይም ወንዝ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ተነግሯል።

ጥቃቱ ከደረሰ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባደረጉት ንግግር ሠራዊታቸው ወደ ኩርስክ ግዛት ዘልቆ የገባው ከሩሲያ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል “የመከላከያ ዞን” ለመመሥረት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሞስኮ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 ኪየቭ ላይ ከከፈተችው ጦርነት በኋላ ዩክሬን ሩሲያ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት ስትፈጽም ይህ የመጀመሪያው ነው።

“አንድ ድልድይ ቀንሰናል” ሲሉ የዩክሬን አየር ኃይል አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል ሚኮላ ኦሌሹክ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው የአየር ጥቃቱን አያይዘው ለጥፈዋል።

ጄኔራሉ አክለውም “የዩክሬን አየር ኃይል አሁንም የጠላትን መሠረታዊ ሎጂስቲክ ነጥሎ በመምታት ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ የጦርነቱን አቅጣጫ የሚቀይር ነው” ብለዋል።

ቪድዮው ድልድዩ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ጭስ ወደላይ ሲወጣ እና የድልድዩ አንደኛው አካል ሲወድም ይታያል። ጥቃቱ መቼ እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም።

ባፈለው ሳምንት መባቻ ዩክሬን ግሉሽኮቮ ከተማ አካባቢ ሰይም ወንዝ ላይ የተዘረጋ ሌላ ድልድይ መደምሰሷ ይታወሳል። ይህ ድልድይ ሩሲያ ለወታደሮቿ አቅርቦታ የምታደርስበት ነበር።

የወታደራዊ ስትራቴጂ ተንታኞች በአካባቢው ሩሲያ ለወታደሮቿ አቅርቦት የምታደርስባቸው ሦስት ድልድዮች አሉ ይላሉ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ሙሉ በሙሉ አሊያም በከፊል ወድመዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዩክሬን ወታደሮች ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቀው ከገቡ ሁለት ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ ዕቅዳቸው በሥፍራው ለመቆየት እንደሆነ ገልጠዋል።

ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ ሠራዊታቸው በኩርስክ ግዛት ያለውን ይዞታ እያጠናከረ እንደሆነ እና ወደ ሩሲያ ድንበር ይበልጥ ዘልቆ እየገባ እንደሆነ ተናግረዋል።

እሑድ አመሻሹን በሰጡት መግለጫ ደግሞ “በኩርስክ ግዛት የምናደርገው ኦፕሬሽን በሩሲያ ሠራዊት እና በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ነው፤ የመከላከያ ኢንዱስትሪያቸው እና ኢኮኖሚያቸውም እየተጎዳ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ አክለው “ይህ ለዩክሬን ከመከላከልም በላይ ነው” ብለው ዕቅዱ “የሩሲያን የጦርነት አቅም በተቻለ መጠን መጉዳት እና ከፍተኛ መጠን ያለው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ መውሰድ” እንደሆነም ገልጸዋል።

የፕሬዝደንት ዜሌንስኪ አማካሪ የሆኑት ሚኻይሎ ፖዶልያክ፤ ዩክሬን ሩሲያን የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላት አስታውቀው ነገር ግን ሩሲያ ወደ ድርድር እንድትመጣ ለማስገደድ እንደሚሹ አስታውቀዋል።

ሞስኮ የዩክሬንን ወደ ድንበሯ ዘልቆ መግባት ትንኮሳ ነው ብላ የመልስ እርምጃ ለመውሰድ እና “ተመጣጣኝ ምላሽ” ለመስጠት ዝታለች።

ዩክሬን ወደ ምዕራባዊ የሩሲያ ግዛት የምታደርገው ግስጋሴ እንዳለ ሆነ ሩሲያ ደግሞ በበኩሏ በምሥራቅ ዩክሬን በኩል ዘልቃ እየገባች እንደሆነ እና ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ መንደሮችን እንደተቆጣጠረች አሳውቃለች።

የተባበሩት መንግሥት የኑክሌር ቁጥጥር ባለሥልጣን በቅርቡ የተደረገውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ በሩሲያ በተያዘችው ዛፖሪዢያ ግዛት ያለው የኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ይዞት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው ሲል ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

የዓለም አቀፉ አውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ማብላያው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ “ሁሉም አካላት” ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ተናግረው ሁኔታ “እጅግ እንዳሳሰባቸው” ተናግረዋል።

የኑክሌር ማብላያው በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የዋለው ጦርነቱ በተጀመረ ሰሞን ሲሆን በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል። ሁለቱም ወገኖች የሚቀርብባቸውን ወቀሳ በማስተባበል እርስ በርስ ይወነጃጀላሉ።

በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ጦርነት ያወጀችው ሩሲያ በቅርብ ጊዜያት በተለይ በምሥራቅ ዩክሬን ይዞታዋን እያስፋፋች ትገኛለች።

በምላሹ የዩክሬን ኃይሎች ወደ ኩርስክ ግዛት ዘልቀው የገቡ ሲሆን፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በግዛቲቱ ያላቸውን ይዞቱ እያጠናከሩ ይገኛሉ።

በሥፍራው ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን ቀያቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የውጭ ኃይል ወደ ሩሲያ ድንበር ዘልቆ ሲገቡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።