የሱተን የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት፡ ዩናይትድ ከአንፊልድ ነጥብ ማግኘት ይቻለው ይሆን?

ባለፈው የውድድር ዘመን ሊቨርፑል በአንፊልድ ማንቸስተር ዩናይትድን 7-0 በመረምረም ታሪካዊ ድል አስመዝግቧል። እሑድ በሚደረገው ግጥሚያስ ምን እንጠብቅ?
“አንዳንድ ሰዎች ዩናይትድ ወደ ሊቨርፑል ተጉዞ ተሟሙቶ ነጥብ ይዞ ይመጣል ብለው ያስባሉ” የሚለው የቢቢሲ ስፖርት ባለሙያው ክሪስ ሱተን “እንዴት ሆኖ?” የሚል ጥያቄ ያነሳል።
“ቦርንመዝ በገዛ ሜዳቸው አሸነፋቸው። ማሸነፍ በሚገባቸው የባየር ሙኒክ ጨዋታ አንድ ጎል እንኳ ማስቆጠር አልቻሉም” ይላል ሱተን።
“ምናልባት ሊቨርፑል 7-0 ላያሸንፍ ይችላል። ነገር ግን ዩናይትድ ያሸንፋል ከማለት ሊቨርፑል 7-0 ድጋሚ ያሸንፋል ብሎ መገመት ይቀላል።”
የዘንድሮውን ውድድር ዘመን 380 ጨዋታዎች ግምት የሚያስቀምጠው ሱተን የ17ኛ ሳምንት ግምቶችን እንዲህ አስፍሯል።
አርብ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከቶተንሃም
አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን የተሸነፉት ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው ሳምንት ከዎልቭስ አቻ በመውጣት ትንሽ እፎይታ አግኝተዋል።
ነገር ግን አሠልጣኝ ስቲቭ ኩፐር አሁንም ጫና ውስጥ ናቸው። ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ማግኘት አለባቸው።
ቶተንሃምም እንዲሁ በተከታታይ ነጥብ ከጣለ በኋላ ባለፈው ሳምንት ኒውካስልን በአስደናቂ ሁኔታ በማሸነፍ ወደ አቋሙ ተመልሷል። የአሠልጣኝ አንጅ ፖስተጎግሉ ልጆች ከዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 3
ቅዳሜ
ቦርንመዝ ከሉተን
ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድ በቦርንመዝ ሲሸነፍ በኦልድ ትራፈርድ ተገኝቼ ጨዋታውን ተከታትያለሁ፤ ቦርንመዝ በጣም ድንቅ ነበሩ።
ቦርንመዝ ኳስ ይዞ መጫወት ብዙም የሚያስጨንቃቸው አይደሉም። አማካዮቹ ራያን ክሪስቲ እና ሉዊስ ኩክ ጥሩ ተጣምረዋል። የፊት መስመሩን ደግሞ ዶሚኒክ ሶላንኪ ይመራዋል።
ቦርንመዝ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፈዋል፤ በአንዱ ደግሞ ከአስተን ቪላ አቻ ተለያይተዋል። በዚህኛውም ጨዋታ ሶስት ነጥብ እንደሚያገኙ እጠብቃለሁ።
ነገር ግን ሉተን ታውን በደንብ ተደራጅተው አይመጡም አልልም።
ግምት፡ 2 - 0

ቼልሲ ከሼፊልድ ዩናይትድ
አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ሼፊልድ ዩናይትድ ከሊቨርፑል ሽንፈት በኋላ ባለው ሳምንት ብሬንትፈርድን በመርታት ሶስት ነጥብ አስመዝግበዋል።
ሼፊልድ በፕሪሚዬር ሊጉ ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ በመጣል የሚያክላቸው የለም። ከሰባት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት።
ነገር ግን አሁን የሚገጥሙት ቼልሲን ነው። ስለቼልሲ ብዙ ጊዜ የገመትኩት የተሳሳተ እየሆነ ተቸግሪያለሁ።
ቢሆንም በዚህኛውም ጨዋታ ሶስት ነጥብ ያገኛሉ የሚል ግምት አስቀምጣለሁ። ነገር ግን ሙሉ እምነት የለኝም።
ግምት፡ 2 - 0
ማንቸስተር ሲቲ ከክሪስታል ፓላስ
ምንም እንኳ ማንቸስተር ሲቲ ባለፈው ሳምንት ሉተን ቢያሸንፉም አቋማቸው እንደ አምናው አይደለም።
ጄሬሚ ዶኩ እና ኧርሊንግ ሃላንድ ጉዳት ላይ ናቸው። ነገር ግን ክሪስታል ፓላስን ማሸነፍ ይሳናቸዋል የሚል ግምት የለኝም።
እንደውም ሲቲ በዚህኛው ጨዋታ ጎል አይቆጠርበትም እላለሁ። ሲቲ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ጎል ሳይቆጠርባቸው ወጥተው አያውቁም።
ፓላስ ባለፈው ሳምንት ዕድለኛ ሳይሆኑ ቀርተው በሊቨርፑል ቢሸነፉም ሲቲን የማሸነፍ አቅም ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም።
ግምት፡ 2 - 0

ኒውካስል ከፉልሃም
ፉልሃም ከሰሞኑ በጣም በርካታ ጎሎች እያስቆጠሩ ማሸነፍ ጀምረዋል። ይህን ጨዋታ መገመት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቀላል ይሆን ነበር፤ አሁን ግን ይከብዳል።
በዚያ ላይ ኒውካስል አሁን ያላቸው አቋም የምተማምንበት አይደለም። በቶተንሃም ከተሸነፉ በኋላ በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በኤሲ ሚላን በመርታት ከውድድር ውጭ ሆነዋል።
እንዲያም ቢሆን የኤዲ ሃው ልጆች ከዚህኛው ጨዋታ የተሻለ ነጥብ ይዘው እንደሚወጡ እገምታለሁ። በዚያ ላይ በሜዳቸው ያላቸው አቋም ጠንካራ መሆኑ እንድተማመንባቸው ያግዘኛል።
ግምት፡ 3 - 1
በርንሊ ከኤቨርተን
እርግጥ ነው ኡናይ ኤምሪ እና አንጅ ፖስቴኮግሉ በያዝነው የውድድር ዘመን ቡድናቸው ከቀየሩ አሠልጣኞች መካከል ናቸው። ነገር ግን የኤቨርተኑ ሾን ዳይሽም ከነሱ ተርታ መመደብ አለበት።
ኤቨርተን በደረሰበት ቅጣት ምክንያት 10 ነጥብ ቢቀነስበትም ሾን ዳይሽና ተጫዋቾቻቸው ይህ ቅስማቸውን ሳይሰብረው ድል ማምጣት ችለዋል።
ዳይሽ የቀድሞ ክለቡን ነው የሚገጥመው። እኔ ግምቴ ይህን ጨዋታ ኤቨርተን እንደሚረታ ነው።
ግምት፡ 1 - 2
እሑድ

አርሰናል ከብራይተን
ብራይተን በአውሮፓ ሊግ ፍልሚያ ምክንያት ሐሙስ ዕለት ጉዞ አድርገው ከዚያ ተመልሰው መጥተ ነው ወደ ኤሜሬትስ የሚያቀኑት።
ይህ መመላለስ ለብራይተን ጨዋታውን ከባድ የሚያደርገው ይመስለኛል።
አርሰናል ባለፈው ሳምንት ወደ አስተን ቪላ ሜዳ ተጉዘው ተሸንፈው ተመልሰዋል። ጨዋታውን ለመርታት የሚያስችላቸው ዕድል ቢፈጥሩም አልተጠቀሙበትም።
ብራይተን በያዝነው የውድድር ዘመን በርካታ ጎል እያስተናገዱ ነው። ይህ ደግሞ ለአርሰናል መልካም አጋጣሚ ይመስላል።
ግምት፡ 3 - 1
ብሬንትፈርድ ከአስተን ቪላ
አስተን ቪላ በሜዳቸው በጣም ድንቅ ናቸው። ከሜዳቸው ውጭ ግን ይህን ያክል አመርቂ የሚባሉ አይደሉም። በያዝነው የውድድር ዘመን ከሜዳቸው ውጭ ከስምንት ጨዋታዎች ሶስቱን ብቻ ነው ያሸነፉት።
የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ መጫወት ከፈለጉ አሊያም ደግሞ ለማለም ከባድ የሆነውን ዋንጫ ለማንሳት የሚሹ ከሆነ ከሜዳቸው ውጭም ግጥሚያዎችን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ብሬንትፈርድ አጥቂያቸው ብራያን ምቡዌሞን በጉዳት አጥተዋል። ቢሆንም ለአስተን ቪላ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ እሙን ነው።
እኔ ይህን ጨዋታ ቪላ በጠባብ ውጤት የሚያሸንፍ ይመስለኛል። ኦሊ ዋትኪንስ ደግሞ ያስቆጥራል።
ግምት፡ 0 - 1

ዌስትሃ ሃም ከዎልቭስ
ዌስት ሃም በአውሮፓ ሊግ ሐሙስ ምሽት ከፍራይቡርግ ጋር ተጫውተዋል። ይህ ለዌስት ሃም ተጨማሪ ጫና ነው።
ዌስት ሃም በአውሮፓ ሊግ ውድድር ወደ ቀጣዩ ዙር ቢያልፉም ተጫዋቾቹ እረፍት ማጣታቸው ለዴቪድ ሞየስ ተጨማሪ ጫና ነው።
እኔ ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 - 1
ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ
ሊቨርፑል ካለው የአጥቂ ተጫዋቾች ብዛት አንፃር ይህን ጨዋታ በእርግጠኝነት እንደሚያሸንፍ አምናለሁ። ዩናይትድ በፍፁም ሊያሸንፍ አይችልም።
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሉክ ሾው እና ሃሪ ማጓየር መጎዳታቸው ለኤሪክ ቴን ሃግ ተጨማሪ ራስ ምታት ነው።
ዩናይትድ ሊያሸንፍ የሚችለው በመልሶ ማጥቃት ነው። ለዚህ ደግሞ ወቅታዊ አቋማቸው ጥሩ የሆኑ አጥቂዎች ያስልጋሉ።
ምናልባት በቀኝ ክንፍ በኩል ጋርናቾ የሊቨርፑልን ተከላካዮች ሊያስጨንቅ ይችላል።
ራስመስ ሆይለንድ ጥሩ ይሁን አይሁን አላውቅም። ምክንያቱም የሚፈልገውን ኳስ እያገኘ አይደለም። ዩናይትድ ባለፉት 18 ጨዋታዎች 16 ጎሎች ብቻ ነው ያስቆጠሩት።
ዩናይትድ በያዝነው የውድድር ዘመን ከስድስቱ ኃያላን ቡድኖች ማንንም መርታት አልቻሉም። ይህን ጨዋታ እንዴት ሊያሸንፉ ይችላሉ?
ሊቨርፑል በጣም መልካም አቋም ላይ ነው የሚገኙት። ይህን ጨዋታም በደንብ ይረታሉ ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 4 - 0












