የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ፕሮስቴት ካንሰር እንደተገኘባቸው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን፤ የፕሮስቴት ካንሰር ተገኝቶባቸው ሕክምና መከታተላቸውን ይፋ አደረጉ።
የ59 ዓመቱ ካሜሮን ለታይምስ ጋዜጣ እንደተናገሩት ምርመራ ለማድረግ የወሰኑት ወንዶች የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና ምርመራ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ የሚያደርገው ስራ ፈጣሪው ኒክ ጆንስ በቢቢሲ ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ካዳመጡ በኋላ ነበር።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተያዘው የአውሮፓውያኑ 2025 መጀመሪያ በሽታውን ለማግኘት የሚያስችል ደም (prostate-specific antigen - PSA) እንዲሁም ከሰውነታቸው ቁራጭ ህብረ ህዋስ ተወስዶ (biopsy) ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል።
የካንሰር ህዋሶችን ለማጥፋት እንደሚያገለግለው አልትራሳውንድ ያሉ የሕክምና ዜዴዎችን በመጠቀም እጢው ያለበት ቦታ ላይ ትኩረት ያደረገ ሕክምና መከታተላቸውንም አስታውቀዋል።
ዩናይት ኪንግደም ውስጥ አብዛኛዎቹ ወንዶች በፕሮስቴት ካንሰር ተይዘው የሚገኝ ሲሆን በየዓመቱም 55,000 ገደማ አዲስ ታካሚዎች ይመዘገባሉ።
ፒኤስኤ የተባለው ምርመራ ከፕሮስቴት ካንሰር ጋር ትስስር ያለውን ፕሮቲን ለማግኘት የሚደረግ ነው። ካሜሮን ያደረጉት ምርመራ በሰውነታቸው ያለው የዚህ ፕሮቲን መጠን ከፍተኛ እንደሆነ አሳይቷል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከጋዜጣው ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ ያሏቸውን መድረኮች በሙሉ በመጠቀም ለፕሮስቴት በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ወንዶች ምርምር እንዲቀርብ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ በብዛት የሚከሰተው ይህ የካንሰር ዓይነት በተለይም ከ75 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ወንዶች ላይ ይታያል።
እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች በሆነ ወንዶች ላይ የመከሰት እድሉ ዝቅተኛ ነው። በሽታው በጥቁር ወንዶች ላይም የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ነው።
"በተለየ መልኩ ስለግል የጤና ጉዳዬ ማውራት አልወድም፤ ግን መነጋገር እንደሚገባኝ ይሰማኛል" ብለዋል።
"እውነቱን እንናገር፤ ወንዶች ስለ ጤንነታቸው ማውራት አይወዱም። አንዳንድ ነገሮችን ችላ ወደማለት እናዘነብላለን" ሲሉም አክለዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2016 ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ወግ አጥባቂው ዴቪድ ካሜሮን፤ በሌላኛው ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሺ ሱናክ መንግሥት ውስጥም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
"ወደፊት ካልመጣሁ እና ያሳለፍኩትን የማልናገር ከሆነ መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። የስካን ምርመራ አድርጌያለሁ። ጥሩ ያልነበረውን ነገር እንዳገኝ ረድቶኛል። እንድፈታውም ዐዕድል ሰጥቶኛል" ብለዋል።
በፒኤስኤ የደም ምርመራ አስተማማኝነት ላይ በሚነሱ ስጋቶች ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የፕሮስቴት ካንሰር ምርመራ ፕሮግራም የለም።
ይህ የዴቪድ ካሜሮን አስተያየት የተሰማው የፕሮስቴት ካንሰር ምርመራ ሙከራ በአገሪቱ ከተጀመረ ከቀናት በኋላ ነው። ሙከራው የፕሮስቴት ካንሰርን ለመለየት የተሻለውን መንገድ የትኛው እንደሆነ ለመለየት ያለመ ነው።















