በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት እና የሰብአዊ ቀውስ እንዳሳሰባቸው ምዕራባውያን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሰሜን ኢትዮጵያ ተባብሶ የቀጠለው ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ስድስት ምዕራባውያን አገራት ጥሪ አቀረቡ።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ አውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በኩል ባወጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት ለወራት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ነበር ባላፈው ዓመት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ አገርሽቶ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ የሚገኘው።
ምዕራባውያኑ አገራቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በአስቸኳይ የሚያካሂዷቸውን ወታደራዊ ጥቃቶች እንዲያቆሙ፣ ግጭት ለማስወገድ እንዲስማሙ፣ ያልተገደበ እና ዘላቂ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በሚካሄድ የሰላም ድርድር ለጦርነቱ መፍትሄ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የኤርትራ ኃይሎች ተሳትፎን አውግዘው፤ የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያካሂደውን ወታደራዊ እንቅስቃሴን አቁሞ ከአካባቢው እንዲወጣ ጠይቀዋል። መግለጫው እንዲሁም ይህንን ግጭት የሚያባብሱ የውጭ ተሳታፊዎች ድርጊታቸውን ማቆም አለባቸው ብሏል።
ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ሠራዊቷ ተሳታፊ የሆነው ኤርትራ፣ መልሶ በተቀሰቀሰው ግጭት ውስጥ አሁንም ተሳታፊ እንደሆነች የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ኤርትራም ሆነች ኢትዮጵያ ይህንን በተመለከተ አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
የመንግሥታቱ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያካሄዱትን ምርመራ እና ሌሎችንም የጠቀሰው መግለጫው፣ ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ሠራዊቶች፣ በትግራይ ኃይሎች እና ፋኖን በመሳሰሉ የታጠቁ ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስታውሷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች መርማሪ ቡድን መስከረም 10/2015 ዓ.ም ባወጣው የመጀመሪያ የምርመራ ሪፖርቱ፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።
ሦስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚሽን የመብት ጥሰቶቹ “የጦር ወንጀል” እና “በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች” ናቸው ሊባሉ የሚያስችሉ ስለመሆናቸው አሳማኝ ምክንያቶች ማግኘቱን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች በተለያየ ደረጃ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን የሚያመለክቱ አሳማኝ መረጃዎች ማግኘቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ሪፖርቱ ገለልተኛነት የጎደለውና እርስ በርሱ የሚቃረን ፖለቲካዊ መግለጫ ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ምዕራባውያኑ አገራት ግን በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች መርማሪ ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ላይ ረሃብ እንደጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉ መገለጹ በጣሙን እንዳሳሰባቸው አመልክተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ መልሶ መጀመሩ ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ሊያደርግ የሚችል አደጋን ደቅኗል ብለዋል።
ሁሉም ወገኖች ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ እንደማይኖረው ተገንዝበው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ባለመው በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው ንግግር ውስጥ እንዲሳተፉ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ከአንድ ሳምንት በፊት ጦርነቱን ለማስቆም የቀጥታ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርቦ ከሁለቱም ወገኖች በኩል አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ በኋላ የ"ሎጂስቲክስ" በተባለ እክል ምክንያት እንዲሁም ከአሸማጋዮቹ አንዱ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መሳተፍ እንደማይችሉ በመግለጻቸው መስተጓጎሉ ይታወሳል።
ምዕራባውያኑ አገራት በመግለጫቸው ላይ የትኛውም ዘላቂ መፍትሄ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች ተጠያቂነትን ማካተት ይኖርበታል ያሉት ያሉ ሲሆን፤ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ፣ የረድኤት ሠራተኞች ደኅንነት እንዲጠበቅ እና ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆጣጣሪዎች አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀዋል።
በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ በመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን ማስከተሉ ሲዘገብ ቆይቷል።












