በአሜሪካ ገንዘብ ተቀብሎ አስከሬኖችን ለወራት ያስቀመጠው ቀብር አስፈጻሚ በፖሊስ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካዋ ኢንዲያና ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ባለቤት ቀብራቸውን እንዲያስፈጽም ክፍያ የተቀበለባቸውን አስከሬኖች ለረጅም ጊዜ አስቀምጦ ተገኘ።
ፖሊስ በቀብር አስፈጻሚ ድርጅቱ ላይ ባደረገው ፍተሻ ከ30 በላይ ለረጅም ጊዜ በአግባቡ ሳይቀመጡ በመቅረታቸው የተበላሹ አስከሬኖች አግኝቷል።
የቀብር አስፈሚ ድርጅቱ ባለቤት እና ኃላፊ በሆነው ራንዲ ላክፎርት ላይ ዐቃቤ ሕግ ገንዘብ ተቀብሎ ቀብር ሳይስፈጽም በመቅረቱ ከ40 በላይ የስርቆት ክስ አቅርቦበት በፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱን አምኗል።
ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛም ድርጊቱ እስከ 12 ዓመት የሚደርስ እስር ሊያስቀጣው እንደሚችል ገልጸው፣ በድርጊቱ ተጎድተዋል ላሏቸው 53 ለሚደርሱ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 46,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍልም አዘዋል።
ግለሰቡ ጥፋተኝነቱን ላመነበት ድርጊት በመጪው ሰኔ ወር ላይ የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሏል።
ኢንዲያና ግዛት ውስጥ የምትገኘው የጄፈርሰንቪል ከተማ ፖሊስ በላንክፎርድ ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ላይ ምርመራ ማድረግ የጀመረው በአካባቢው ከባድ ጠረን እንዳለ ጥቆማ ከደረሰው በኋላ ነው።
በዚህም በቀብር አስፈጻሚው ድርጅት ውስጥ በተደረገው ፍተሻ ለወራት በአግባቡ በማቀዝቀዣ ውስጥ ያልተቀመጡ አስከሬኖች በተለያየ ደረጃ ተበላሽተው ከባድ ጠረን ፈጥረው ተገኝቷል።
በተጨማሪም በእሳት ተቃጠለው ፍጻሜ ያገኙ የ17 ሰዎች ቅሪት አመድም በድርጅቱ ውስጥ ተገኝቷል።
በዚህም የተነሳ የቀብር አስፈጻሚው ድርጅት ባለቤት እና ኃላፊ የሆነው ግለሰብ የመጨረሻ ብይን አስኪሰጠው ድረስ በቤቱ ውስጥ በቁም አስር እንዲቆይ ተወስኖበታል።
ጉዳዩን እየተመለከቱ የቆዩት ዳኛ ግለሰቡ ለፈጸመው ጥፋት ለአራት ዓመታት እንዲታሰር፣ በተጨማሪም ከዚያ በኋላ በቁም እስር ስምንታ ዓመታት በቤቱ እንዲቆይ ሃሳብ አቅርበዋል።
የአካባቢው ዐቃቤ ሕግ ጄሬሚ ሙል እንዳሉት በ50 ዓመቱ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ባለቤት ላይ የቀረቡበት ክሶች በርካታ በመሆናቸው የተወሳሰቡ እንደሆነ አመልክተዋል።
ለዚህም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በተከሰቱ በርካታ ሞቶች ሳቢያ በፍጥነት ቀብር ለማስፈጸም አለመቻሉ አንዱ መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የቤተሰብ አባሎቻው አስከሬኖች በቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየባቸው ሰዎች ጉዳዩ በተሰማበት አርብ ዕለት ፍርድ ቤት የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው ዴሪክ ኪሲንጀር “የተፈጠረው ነገር በጣም ከባድ ነው፤ ነገር ግን ግለሰቡ ለፈጸመው ነገር ይቅር ብዬዋለሁ” ብሏል።
ነገር ግን ሌሎች ቤተሰቦች በቀብር አስፈጻሚው ላይ ሌላ የፍትሃ ብሔር ክስ በመክፈት ክስ እንደመሠረቱበት ተገልጿል።
ቤተሰቦቹ ለፍርድ ቤት ባቀረቧቸው ተጨማሪ ክሶች ላይ ከዚህ በፊት የተቃጠሉ የቤተሰቦቻቸው አስከሬኖች ቅሪት አመድ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን ፖሊስ ያደረገውን ፍተሻ ተከትሎ ትክክለኛውን አመድ ማግኘታቸውን ገልጸው ይህም ማጭበርበር መሆኑን የሚገልጽ ነው።
በተጨማሪም የሟች ቤተሰቦቻቸው ቀብር እንዲፈጸም ቢከፍሉም ሳይቀበሩ ወይም አስከሬናቸው ሳይቃጠል ቀርቷል በማለትም ክስ አቅርበዋል።












