ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ተቃውሞ የገጠመው የሕግ ማሻሻያ እንዲዘገይ ወሰኑ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የወጣውን ቁልፍ የሆነ አወዛጋቢ እቅድ እንደሚያዘገዩ አስታወቁ።
በዚህም ለቀናት በተቃውሞ ስትናጥ በነበረችው እስራኤል መረጋጋት ታይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ዕለት ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ "በሕዝባችን መካከል ያለውን መከፋፈል ለመከላከል" ሲሉ የሕግ ማሻሻያው ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ መደረጉን ተናግረዋል።
በንግግራቸውም ‘ጽንፈኞች’ ያሏቸውን አካላት ሕዝቡን ለመከፋፈል ሞክረዋል ሲሉ የከሰሱ ሲሆን እቅዱን የተቃወሙ ተጠባባቂ ወታደሮችም ሥራ አንገባም በማለታቸው ወቅሰዋል።ይሁን እንጂ ለተፈጠረው ውዥንብር ኃላፊነት አልወሰዱም።
የእስራኤል ተቃዋሚዎች በበኩላቸው በእቅዱ ላይ እንደሚወያዩበት ተናግረዋል።
ሆኖም የእቅዱ መዘግየት ጊዜ ከመግዛት ውጪ ምን ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያስታወቁት እቅዱን በመቃወም የተናገሩትን የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ካባረሩ በኋላ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው።
በዚህ ባልተጠበቀ ክስተት በአገሪቷ ትልቁ የንግድ ማኅበር አድማ የጠራ ሲሆን በርካታ እስራኤላውያንም ሥራቸውን አቁመዋል።
ዋናውን አየር ማረፊያ ጨምሮ ሱቆችና ባንኮች እንዲሁም ሆስፒታሎች የሚሰጡትን አገልግሎት አቁመውም ነበር።
ይህ የማኅበረሰቡ የተቀናጀ እርምጃ ኔታንያሁ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ማሻሻያዎቹ እንዲጸድቁ ሲገፋፉ ከነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ ያለመ ነበር።
የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ዬር ላፒድ ተቃውሞውን “በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ቀውስ” ሲሉ ገልጸውታል።
የእስራኤል ቀኝ አክራሪ መንግሥት ዳኞችን የሚሾመውን ኮሚቴ በሙሉ ሥልጣን መቆጣጠር ይፈልጋል።
የሕግ ማሻሻያዎቹ፣ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን የመሻር ሥልጣን የሚሰጡ ሲሆን ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሥልጣን ብቁ አይደሉም ብሎ መናገር እና ከሥልጣን ማንሳትን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ኔታንያሁ በበኩላቸው ማሻሻያዎቹ ፍርድ ቤቶች ከሥልጣናቸው በላይ እንዳይሰሩ ያደርጋል ያሉ ሲሆን፣ ተቺዎች ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙስና ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ ራሳቸውን ለመርዳት ያለሙት ነው ሲሉ ተቃውመውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉቦ በመቀበል፣ በማጭበርበር እና በሕግ ጥሰት ሦስት ክሶች ቀርቦባቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ቆይተዋል። እርሳቸው ግን በቀረበባቸው ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን ክሱንም “ የስም ማጥፋት ዘመቻ” ብለውታል።
አዲስ የቀረበው የሕግ ማሻሻያ እቅድ ይፋ ከተደረገበት ታኅሳስ ወር መጨረሻ አንስቶ የአገሪቷን ጦር ጨምሮ በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ውሳኔ በተመለከተ ሰኞ ንግግር እንደሚያደርጉ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ አሜሪካ በእስራኤል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባት ገልጸው፤ እቅዱ መዘግየቱን በተመለከተ ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።












