ሁለት የሩስያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጥቁር ባህር ላይ በከፋ ጉዳት ደረሰባቸው

 የሩስያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, Southern Transport Prosecutor's Office

ሁለት የሩስያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በጥቁር ባህር ላይ ክፉኛ ከመጎዳታቸው በላይ አደጋው ለነዳጅ መፍሰስ ምክንያት መሆኑን የሩስያ ባለስልጣናት አስታወቁ።

በሩስያው የደቡባዊ ትራንስፖርት ዓቃቤ ህግ የተለቀቀው ምስል የአንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ሙሉ በሙሉ ተሰብሮ ነዳጅ ውሃው ላይ ሲንሳፈፍ ይታያል።

በአደጋው ቢያንስ አንድ የመርከብ ሠራተኛ መሞቱ ተነግሯል።

ክስተቱ ሩስያን ከክሬሚያ በሚለየው በከርች ሰርጥማጋጠሙ ታውቋል። የዩክሬን ባሕረ ገብ መሬት የሆነው ክሬሚያ በአውሮፓውያኑ 2014 በሞስኮ በሕገ-ወጥ መንገድ ተወስዷል።

ጀልባዎች፣ ሄሊኮፕተሮች እና ከ50 በላይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ባሳተፈ የነፍስ አድን ስራ 13 ሠራተኞችን ከአንድ መርከብ ቢታደጉም በአየር ሁኔታ ምክንያት የነፍስ አደጋው ሥራው ተቋርጧል።

በሁለተኛው መርከብ ላይ ሲሠሩ ነበሩት 14 ሠራተኞች "ለህይወት ማቆያ የሚሆን አስፈላጊው ነገር ሁሉ" እንዳላቸው ቢገለጽም የአየር ጸባዩ እስኪሻሻል ለመቆት በዛው ይቆያሉ ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አደጋውን ለመቋቋም የሚያስችል እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቪታሊ ሳቬሌቭ የሚመራ ቡድን እንዲቋቋም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ባለስልጣናት በጉዳዩ ዙሪያ ቸልተኝነትን ስለመኖሩም እየመረመሩ ነው።

የመርከብ ኢንዱስትሪን በተመለከተ በሚዘግበው ሎይድ ሊስት መጽሔት ላይ በተንታኝነት የሚያገለግሉት ሚሼል ቦክማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁለቱ መርከቦች በቮልጋታንከር ኩባንያ ባለቤትነት የሚተዳደሩ በአንጻራዊነት አነስተኛ መርከቦች ናቸው።

በታስ የዜና አገልግሎት የሩሲያ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው መርከቦቹ እያንዳንዳቸው 4 ሺህ 300 ቶን የሚጠጋ ነዳጅ ይዘው ነበር።

የሩስያ ድፍድፍ ነዳጅን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመሸጥ የሚያገለግሉ ነዳጅ ጫን መርከቦች ወደ 120 ሺህ ቶን የሚጠጋ ነዳጅ የመሸከም አቅም አላቸው ያሉት ቦክማን ይህ ማለት እነዚህ አነስተኛ መርከቦች በሩሲያ ወንዞች ወይም በባህር ዳርቻዎች ነዳጅ ለማጓጓዝ ያገለግሉ ነበር ማለት ነው ብለዋል።

የከርች ሰርጥ የሩሲያ እህል ወደ ውጭ ለመላክ ቁልፍ መንገድ ሲሆን ድፍድፍ ዘይት፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ ለመላክም ያገለግላል።

እአአ በ 2007 ቮልጎኔፍት - 139 የተባለ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በከርች ሰርጥ ላይ በተከሰተ ማዕበል ምክንያት ለሁለት ተከፍሎ ከአንድ ሺህ ቶን በላይ ነዳጅ አፍስሷል።

እአአ በ2022 ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የኪዬቭ አጋር አገራት በሩስያ የነዳጅ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ ጥለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሩስያ ብዙ ጊዜ ጥሩ ጥገና የማይደረግላቸው እና ተገቢው መድን ያልተገባላቸው የነዳጅ መርከቦችን ተጠቅማ ነዳጅ ለማንቀሳቀስ እና ማዕቀቡን ለማለፍ ትሞክራለች ተብላ ትከሰሳለች። በእሑዱ ክስተት የተሳተፉት የነዳጅ መርከቦች በተመሳሳይ ድርጊት ላይ የተሳተፉ አይመስሉም ሲሉ ቦክማን ገልጸዋል።