የአሜሪካ ሰላዮች ግብፃዊውን የአልቃይዳ መሪ እንዴት ደረሱበት? የገደሉትስ በምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ዓመት ነበር አሜሪካ በአፍጋኒስታን የነበራትን ቆይታ ጨረስኩ ብላ በጥድፊያ የወጣችው።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ በታሊባን በሚመራው አዲሱ አገዛዝ አፍጋኒስታን የአሸባሪዎች መሸሸጊያ እንደማትሆን ቃል ገቡ።
ቢያንስ በባይደን እና ኋይት ሃውስ በኩል ለአሥርት ዓመታት የዘለቀው በሽብር ላይ የተከፈተው ጦርነት አለማብቃቱን ለማመልከት ታስቦ የተሰጠ አስተያየት ነበር።
ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የፕሬዝደንቱ ከፍተኛ የደኅንነት አማካሪዎች ቀርበው አንድ ነገር ሹክ አሏቸው።
የደኅንነት ሰዎች የአል-ቃይዳው መሪ አይማን አልዛዋሂሪን አፍጋኒስታን ውስጥ ሳያገኙ እንዳልቀሩ ጠቆሟቸው።
ትልቁን ዒላማ መለየት
በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈው መንግሥት ባለፈው ዓመት መንኮታኮቱን ተከትሎ ዛዋሂሪ ወደ አፍጋኒስታን መመለሱን እንደሚያምኑ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር።
አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ከለቀቀችበት ጊዜ አንስቶ የአገሪቱ ሰላዮች ዐይንና ጆሯ እዛው ነበር።
የአልቃይዳ መሪዎች ቀስ በቀስ ወደ አፍጋኒስታን እየገቡ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶችን አንድ በአንድ ይከታተሉ እንደነበርም የባይደን አማካሪ ተናግረዋል።
ዛዋሂሪ ከባለቤቱ እና ከሴት ልጁ ጋር መሐል ካቡል ከትሟል ተባለ። ያውም ትልቅ የግንብ አጥር ባለው ግዙፍ ግቢ ውስጥ።
ዛዋሂሪ የመረጠዉ ሰፈር በአንጻራዊ ሁኔታ ጥሩ የሚባለውን ነው።
ቾርፑር የሚባል ሰፈር ሲሆን በቀድሞዉ አስተዳደር ወቅት የውጭ ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች መኖሪያ አካባቢ ነበር።
አሁን ደግሞ አብዛኞቹ የታሊባን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚኖሩበት የሚያምር ሰፈር ነው።
በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ የሲአይኤ ሰላዮች ለባይደን አማካሪዎች ያገኙትን መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አካፈሉ። ቀጥሎም ለፕሬዚዳንቱ ነገሯቸው።
የአልቃይዳውን መሪ እና ቤተሰቡን የሚደግፍ መረብ መለየታቸውን በበርካታ የመረጃ ምንጮች አስደግፈው አቀረቡ።
ሰላዮቹ የዛዋሂሪ ሚስት መሆኗን የገለጿትን ሴት ልዩ ባህሪን ጨምሮ የቤቱን ነዋሪዎች ባህሪ ቀስ በቀስ አጠኑ።
ካቡል ወደሚገኘው የባለቤቷ መሸሸጊያ ማንም እንዳያመራ የአሸባሪዎችን “ዘዴ” መጠቀሟን ባለሥልጣናቱ አውቀው ነበር።
ቤቱ ደረሱ። ዛዋሂሪ ከግቢው እንደማይወጣ ተመለከቱ። በተወሰነ ሰዓት ልዩነት ግን ወደ በረንዳው ብቅ ይላል። ግቢውን ዞር ዞር ብሎ ይመለከትና ተመልሶ ይገባል።
ታሪካዊውን ወረራ ማቀድ
በአሜሪካ በጣም ከሚፈለጉ ሰዎች አንዱን ለመግደል መሞከር ለባይደን በአደጋ የተሞላ ነበር።
ዛዋሂሪ በርካታ ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ነው የሚኖረው።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን በቆየችባቸው የመጨረሻ ቀናት በካቡል የድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላን) ጥቃት ፈጽማ ነበር።
በጥቃቱ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ እና ሰባት ሕጻናትን ጨምሮ 10 ንጹሀን ዜጎች ተገደሉ። ይህ ደግሞ የፕሬዝደንቱ የስጋት ምንጭ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ግንቦት እና ሰኔን ስለ ዩክሬን ጦርነት ሲብሰለሰሉ አሳልፈዋል።
በጠመንጃ ቁጥጥር እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሕጎችን በማውጣት ላይም አተኩረው ነበር።
በድብቅ ግን "በጣም ትንሽ እና የተመረጡ" ከፍተኛ የስለላ መኮንኖች ቡድን ተዋቀረ። ዓላማው ግብፃዊውን ለማንበርከክ አማራጮችን ማዘጋጀት ነው።
ባይደን ትዕዛዝ አስተላለፉ።
የዛዋሂሪን ቤተሰብ እና የታሊባን ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሲቪሎች በታቀደው ጥቃት አለመገደላቸውን እንዲያረጋግጡ ነው ትዕዛዙ።
ባይደን እአአ ሐምሌ 1 የሲአይኤ ዳይሬክተሩ ዊልያም በርንስን እና የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተሩን አቭሪል ሄይንን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሰበሰቡ።
ፕሬዝደንቱ እና አማካሪዎቻቸው የስለላ ባለሥልጣናት ገንብተው ወደ ኋይት ሃውስ በወሰዱትና የዛዋሂሪን ቤት በሚመስለው ሞዴል ዙሪያ ተሰባሰቡ።
ባይደን “በውይይቱ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በመረጃውም በጣም ተመስጠው ነበር” ተብሏል።
"እያንዳንዱ እርምጃ በጥንቃቄ መወሰዱን በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር" ሲሉ አንድ ከፍተኛ አማካሪ ገልጸዋል።
ባይደን ለሳምንት እረፍት ወደ ካምፕ ዴቪድ ከመብረራቸው በፊት ስለ ሕንጻው መዋቅር እና ጥቃቱ እንዴት እንደሚጎዳው መረጃ ጠይቀዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታት ባለሥልጣናቱ በኋይት ሃውስ የከፍተኛ መረጃ መከታተያ የዕዝ ማዕከል (ሲቹዌሽን ሩም) ውስጥ ይገናኙ ጀመር።
ይህ ክፍል ፕሬዝዳንቱ የአገር ውስጥ እና የውጭ ቀውሶችን እንዲቆጣጠሩ ከኋይት ሃውስ በታች የተቋቋመ ማዕከል ነው።
ፕሬዚዳንቱ ሊጠይቋቸው የሚችሏቸውን ማንኛቸውንም ጥያቄዎች በመገመት ሥራውን በጥንቃቄ አቅዱ።
ጥቂት የሕግ ባለሙያዎች ቡድን የጥቃቱን ሕጋዊነት ለመገምገም ተዋቀረ።
ዛዋሂሪ "አልቃይዳ ውስጥ ባለው የአመራርነት ሚና እና በአልቃይዳ ጥቃቶች ላይ ባለው ተሳትፎ እንዲሁም ድጋፍ" ላይ በመመሥረት ጥቃቱ ሕጋዊ መሆኑን ቡድኑ ደመደመ።
እአአ ሐምሌ 25 ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ከሰበሰቡ እና የከፍተኛ አማካሪዎቻቸውን አስተያየት ከጠየቁ በኋላ ባይደን ጥቃቱን ፈቀዱ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአሜሪካ ጥቃት እና የታሊባን መሪዎች መተራመስ
በአገሬው አቆጣጠር ሰዓቱ ጠዋት 12፡18 ይላል።
ሁለት ሚሳኤሎች ከድሮን ተተኮሱ። ዒላማቸው የዛዋሂሪ ቤት በረንዳ ነው።
የአልቃይዳው መሪ በጥቃቱ ተገደለ። የቤተሰቡ አባላት ግን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የስለላ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የቤቱ መስኮቶች ተሰባብረዋል። በሚያስደንቅ ሁኔታ ሌላ ጉዳት ግን የደረሰ አይመስልም።
ለዚህ ጥቃት ብዙም የማይታወቅ የሚሳኤል ዓይነት ጥቅም ላይ ውሏል። ሚሳኤሉ የመፈንዳት ባህሪ የሌለው ነው።
ይህ AGM-114R9X ተብሎ የሚጠራው ሚሳኤል ከመፈንዳት ይልቅ ወደ ዒላማው ሲቃረብ ከጎኑ ስድስት ስለታማ ብረቶችን ያስወነጭፋል።
ጉዳት የሚያደርሰው ከዚህ ባለብዙ ምላጭ መሣሪያ በፍጥነት የሚመነጨው ኃይል ነው። ዒላማ ያደረጋቸው ሲወገዱ፣ ሌላ ጉዳት ግን እንዳይፈጠር ያግዛል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮችን ርቀው ዋሽንግተን የሚገኙት ፕሬዚዳንት ባይደን ስለ ጥቃቱ ስኬት ተነገራቸው።
የታሊባን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ቶሎ ለተባለው የዜና ማሰራጫ፣ እሑድ የተቃጣ የሮኬት ጥቃት ባዶ ቤት መምታቱን እና ጉዳት አልመድረሱን ገልጸዋል። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ አልሆኑም።
የባይደን አስተዳደር ብዙም ሳይቆይ አስተያየት ሰጠ።
እጅግ ኃይለኛ የሚባለው የታሊባኑ የሃቃኒ ቡድን ተዋጊዎች፣ የዛዋሂሪን ቤተሰብ በፍጥነት ከስፍራው በማስወጣት ጥቃቱን ለመሸፈን ሰፊ ጥረት ማድረጋቸውን ገለጸ።
ሰኞ ማለዳ በመኖሪያ ቤቱ የደረሰው የቢቢሲ ጋዜጠኛ በታሊባን የፀጥታ ኃይል ከአካባቢው እንዲርቅ ተነገረው። ጠመንጃ በመደገንም “ምንም የሚታይ ነገር የለም” በማለት አጥብቆ ተናገረው።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት የዛዋሂሪን መሞት "በርካታ የመረጃ ምንጮች" አረጋግጠዋል ብለዋል።
ካቡል ውስጥ ግን ምንም ዓይነት አሜሪካዊ ጦር እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጥቃቱን ስኬት እንዴት እንዳረጋገጡ ግን ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የስለላ ድርጅቶች የሰላዮቻቸውን ማንነት ይጠብቃሉ።
በፕሬዝደንት ኦባማ ዘመን የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር የነበሩት ጀምስ ክላፐር በካቡል የሚገኙ የቀድሞ የአሜሪካ አጋሮች የተወሰነ መረጃ ሳይሰጡ አልቀሩም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዛዋሂሪ አስክሬን ከምን እንደደረሰ ግልጽ አይደለም።
ኦሳማ ቢን ላደን ሲገደል አስክሬኑን አሜሪካኖች ወስደዋል። ከዚህ በተቃራኒ የባይደን አስተዳደር ሰዎች የዛዋሂሪን አስክሬን ለመውሰድ ምንም ጥረት አላደረግንም ብለዋል።
ልዩ ኃይሎች የቢን ላደንን አስክሬን ማንነቱን ለማረጋገጥ ወስደዋል። የመቃብር ስፍራው የተከታዮቹ መሰባሰቢያ እንዳይሆን በማሰብም አስክሬኑን ባሕር ውስጥ ቀብረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታሊባን አካባቢውን በማጽዳቱ አስክሬኑ ሊወሰድ ይችላል ተብሏል።
ባይደን ከኋይት ሃውስ በረንዳ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ያደረጉት ንግግር በዓለም ዙሪያ ተዳርሷል።
የታሊባን መሪዎች በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስን ግዛታችንን ጥሳለች በሚል ድርጊቱን አውግዘዋል። ስለ ዛዋሂሪ ግን ምንም አልተገለጸም።
የታሊባን ከፍተኛ አመራሮች ዛዋሂሪ በካቡል ስለመኖሩ ምን ያህል ያውቁ ነበር በሚለው ዙሪያ መላምቶች እየተሰጡ ነው። ለጥቃቱ ምን ዓይነት እርዳታ ሰጡ? የሚለውም ሌላው መነጋገሪያ አጀንዳ ነው።
አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ የታሊባን ተዋጊዎች መንገዱን ሲጠብቁ ቆይተዋል። “የአፍጋኒስታን ዜጋ ያልሆኑ ነዋሪዎች” መኖራቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ይታወቃልም ብሏል።
ጥቆማው ለታሊባን መሪዎች አስቸጋሪ ጥያቄዎችን የሚጭር ይመስላል።












