በምንጃር ሸንኮራ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቀብር ተፈጸመ

በአርቲ ማርያም ቀብር ላይ የተገኘች ሴት ስታለቅስ

የፎቶው ባለመብት, Amensisa Ifa / BBC

በአማራ ክልል፣ሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስትያን በደረሰ አደጋ የሞቱ 36 ሰዎች ቀብር ዛሬ ተፈጸመ።

በምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ማርያም በየዓመቱ በሚከበረው ክብረ በዓል ላይ ትናንት መስከረም 21 2018 ዓ.ም. ታድመው የነበሩ 36 ምዕመናን ለግንባታ የተረበረበ እንጨት ተደርምሶ መሞታቸው ይታወሳል።

የሟቾቹ ቀብር ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።

የ22 ዓመቱ ፍቅሬ ጥላሁን በአደጋው እናቱን ማጣቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"እናትን ማጣት ከባድ ነው፤ በጣም ከባድ" ያለው ፍቅሬ ለቤተክርስትያኑ ግንባታ የተቀመጠ ርብራብ መደርመሱን የሰማው ወደ ሌላ ቦታ እየሄደ መሆኑን ያስታውሳል።

እናቴ በየዕለቱ ወደ ማርያም ቤተክርስትያን ሄዳ ትሳለም፣ትፀልይ ነበር የሚለው ፍቅሬ "አንድ ቀንም ቀርታ አታውቅም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ትናንት የማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይም "የቅዳሴ ጠበል ላምጣ" በሚል መሄዳቸውን የሚናገረው ፍቅሬ፣ እርሱ ለብቻው ስለሚኖር ያገኛቸው ከአንድ ቀን በፊት እንደነበር ገልጿል።

ማለዳ ከወንድሙ ጋር ተከራይተው ወደ ሚኖሩበት ቤት ሲሄድ እናቱ ወደ ማርያም ቤተክርስትያን በመሄዳቸው አላገኛቸውም።

ፍቅሬ አደጋው መድረሱን እንደሰማ ወደ ቤተክርስትያን የሄደ ሲሆን ከዚያም እናቱን ለመፈለግ ወደ ጤና ጣቢያ ቢሄድም እናቱን ሳያገኝ ቀርቷል።

"የአጎቴ ልጅ ነው ከዚያ በኋላ የደወለልኝ። ከዚያ ወደ ሆስፒታል ሄድኩ። እዚያ የእናቴን አስከሬን አገኘሁ"

የፍቅሬ እናት ከሞቱት 36 ሰዎች መካከል አንዷሲሆኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ተቋማት የሚገኙ ሰዎች በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት መስከረም 21 2018 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ቤተክርስትያን ምዕመናን የተገኙት የማርያምን ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓል ለመታደም ነበር።

በአደጋው እናቱን ያጣው ፍቅሬ ጥላሁን

የፎቶው ባለመብት, Amensisa Ifa / BBC

የምስሉ መግለጫ, ፍቅሬ ጥላሁን እናቱን ያገኛቸው ከመሞታቸው አንድ ቀን በፊት ነው

ከሞቱት ምዕመናን መካከል የቀን ሠራተኞች፣መምህራን እና መነኩሴዎች እንደሚገኙበት የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ ገበየሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ገብረወልድ የተባሉ የዓይን እማኝ በበኩላቸው በእንጨት የተሠራው መወጣጫ ላይ በቤተክርስትያኑ ጣርያ ላይ የተሳለውን ስዕል ለማየት በሚል በርካታ ምዕመናን ርብራቡ ላይ በመውጣታቸው የአደጋው መንስዔ መሆኑን አስረድተዋል።

ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው የርብራቡን መውደቅ ተከትሎ የተፈጠረው መደናገጥ እና ግርግር ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች 200 ሲሆኑ የከፋ ጉዳት ያጋጠማቸው ወደ አዲስ አበባ ለተሻለ ሕክምና ተልከዋል።

የሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቃጥበብ አባቡ ስለ አደጋው ለቢቢሲ "እጅግ አሳዛኝ፣ልብ ሰባሪ ክስተት ነው። እንደ አገርም እንደ ቤተ ክርስቲያንም ትልቅ መርዶ ነው የገጠመን።" ብለዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ "ቤተ ክርስቲያን በረከት ለማግኘት ሄዶ አስክሬን መመለስ ልብ ውስጥ የሚፈጥረው ነገር ለማንም የሚሰወር አይደለም። የእግዚአብሔር ጥሪ ነው። እንደ ሰውኛ ግን ልብ የሚያደማ ነው" ሲሉም አክለዋል።

የቀብር ስነስርዓት ሲፈጸም

የፎቶው ባለመብት, Amensisa Ifa / BBC

የደረሰውን አደጋ ተከትሎ መንግሥት ባወጣው የሐዘን መግለጫ "ሕይወታቸውን ያጡ፣ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸው በመሰማቱ መንግሥት የተሰማውን ሐዘን ይገልጻል፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን፤ በሕክምና ላይ ለሚገኙት በፍጥነት ማገገምን እንመኛለን" ብሏል።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ የሞቱት ሰዎች ከ25 ዓመት እስከ 80 ዓመት እንደሚደርሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በግንባታ ወቅት መደረግ የሚገባቸውን ተገቢ ጥንቃቄዎች ባለማድርግ የተነሳ በሰው ላይ የአካል መጉደል እና የሞት አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ይታያል።

የማሪያም ቤተክርስትያን

የፎቶው ባለመብት, Amensisa Ifa / BBC

የምስሉ መግለጫ, በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የምትገኘው አረርቲ ማርያም ቤተክርስትያን