በምንጃር ሸንኮራ የቤተ ክርስቲያን ግንባታ መሸጋገሪያ ተደርምሶ ቢያንስ የ36 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስትያን ለግንባታ የተረበረበ እንጨት

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስትያን ለግንባታ የተረበረበ እንጨት

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ቤተክርስትያን ለግንባታ የተረበረበ እንጨት ተደርምሶ ቢያንስ 36 ሰዎች ሕይወታቸው አለፈ።

ዛሬ የማርያምን ዓመታዊ በዓል ለማክበር በሥፍራው የተገኘው ምዕመን እየተሠራ ያለውን ቤተክርስትያን እየጎበኘ ባለበት ሰዓት የተረበረበው እንጨት በመደርመሱ በሰው ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል።

አደጋው የደረሰው መስከረም 21/2018 ዓ. ም. ማለዳ ከጠዋቱ 1:45 ላይ እንደሆነ እና በአደጋው 36 ሰዎች እስካሁን ድረስ ሕይወታቸው ማለፉ ሲረጋገጥ፣ ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ ገበየሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"የፎቁ መረማመጃ 14 ዓመት የቆየ ነው። ሰዎች በጉብኝት ላይ ሳሉ ከአቅሙ በላይ ስለተጫነው ተሰብሮ አደጋው ደርሷል" በማለት አደጋው እንዴት እንደተከሰተ አስረድተዋል።

የመደርመስ አደጋው የደረሰው ምዕመናን በወረዳው እየተሠራ ያለውን ቤተክርስቲያን ግንባታ በመጎብኘት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው የሚሉት የአካባቢው ኃላፊዎች ተጎጂዎችን በአካባቢው ወደሚገኙ የተለያዩ የሕክምና ተቋማት መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ ገበየሁ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስካሁን መሞታቸው የተረጋገጠው 30 ሰዎች ቢሆኑም ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል።

የአረርቲ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ ረፋድ ላይ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ በሰጡት ማብራሪያ ከርብራቡ ሥር ያልወጡ ዜጎች አንደሚገኙ እና እነርሱን የማውጣት ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ ገበየሁ ዛሬ ከሰዓት ለቢቢሲ እንደገለጹት ከሰዓታት በኋላ ሰዎቹን ከርብራቡ ሥር ለማውጣት ተችሏል።

"ቢያንስ ለሦስት ሰዓት ያህል ሰዎቹን የማውጣት ሥራ ሠርተናል። መከላከያም ሳይቀር በመረባረብ ሰዎቹን በሙሉ አውጥተናል" ብለዋል።

የቀን ሠራተኞች፣ መምህራን እና መነኩሴዎች ከሞቱት ምዕመናን መካከል እንደሚገኙበትም አክለዋል።

የአረርቲ ሆስፒታል ኃላፊ ተወካይ አቶ ስዩም አልታዬ ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ ወደ አረርቲ ሆስፒታል የመጡ ተጎጂዎችን ሕክምና እየሠጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አምስቱ ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

የአረርቲ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ 55 ሰዎች ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ገልጸዋል።

የደረሰውን አደጋ ተከትሎ መንግሥት ባወጣው የሐዘን መግለጫ "ሕይወታቸውን ያጡ፣ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸው በመሰማቱ መንግሥት የተሰማዉን ሐዘን ይገልጻል፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን፤ በሕክምና ላይ ለሚገኙት በፍጥነት ማገገምን እንመኛለን" ብሏል።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢኒስፔክተር አሕመድ የሞቱት ሰዎች ከ25 ዓመት እስከ 80 ዓመት እንደሚደርሱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ገብረወልድ ተስፋዬ የተባሉ የዐይን እማኝ "እንጨቱ ሲወድቅ የነበረው ጩኸት በጣም ያስፈራ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"መደናገጡ፣ ግርግሩና የሕዝቡ ወከባ ቢኖርም፤ የፀጥታ ኃይሎች፣ ምዕመናኑ እና የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮችም ተረባርበዋል። በተቻለው ፍጥነት የወደቀው እንጨት ተነስቷል" ሲሉም አክለዋል።

አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ሆስፒታል በአፋጣኝ ለመውሰድ ርብርብ መደረጉንም አቶ ገብረወልድ ገልጸዋል።

"የሕዝብ ውይይት ይደረጋል ስለተባለና ባዛርም ስለሚካሄድ ሕዝቡ በብዛት ታላቁ ንግሥ ላይ ሄዶ ነበር" ያሉት የዐይን እማኙ በእንጨት የተሠራው መወጣጫ ላይ የነበሩ የግንባታው ጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ለአደጋው መንስዔ መሆኑን አስረድተዋል።

እስካሁን የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 36 መድረሱን መስማታቸውንም አክለዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ 55 ገደማ መድረሳቸውንም ገልጸዋል።

የተደረመሰው እንጨት በአካባቢው ማኅበረሰብ ርብርብ ከተነሳ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴ እንደተከናወነ እና ነገ የሞቱት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር እንደሚፈጸም አቶ ገብረወልድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቃጥበብ አባቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ "በአካባቢው ማኅበረሰብ ገንዘብ መዋጮ እየተገነባ ያለው አዲስ ቤተ ክርስቲያን የጉልላቱ መስቀል የወጣበት ዕለት በመሆኑ" በዓሉ በስፋት ተከብሯል።

የግንባታውን ማጠናቀቂያና ሥዕላትን ለማየት በርካታ ሰዎች ወደ አዲሱ ሕንጻ መግባታቸውንም መጋቤ ሐዲስ ነቃጥበብ አክለዋል።

"እስከ ጣሪያው ያለውን ዲዛይን ለማየት ነው የወጡት። እጅግ አሳዛኝ፣ ልብ ሰባሪ ክስተት ነው። እንደ አገርም እንደ ቤተ ክርስቲያንም ትልቅ መርዶ ነው የገጠመን።"

ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ "ቤተ ክርስቲያን በረከት ለማግኘት ሄዶ አስክሬን መመለስ ልብ ውስጥ የሚፈጥረው ነገር ለማንም የሚሰወር አይደለም። የእግዚአብሔር ጥሪ ነው። እንደ ሰውኛ ግን ልብ የሚያደማ ነው" ሲሉም አክለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በግንባታ ወቅት መደረግ የሚገባቸውን ተገቢ ጥንቃቄዎች ባለማድርግ የተነሳ በሰው ላይ የአካል መጉደል እና የሞት አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ይታያል።