አውስትራሊያ በሠራተኝነት ወደ አገሯ ለሚመጡ ሰዎች የምትሰጠውን የፍቃድ ቁጥር ከፍ አደረገች

አውስትራሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውስትራሊያ ከአስርት ዓመታት በኋላ በቋሚ ነዋሪነት ከተለያዩ አገራት የምትወስዳቸውን ስደተኞች ቁጥር ከፍ አደረገች።

አውስትራሊያ በዚህ 2022 የፈረንጆች ዓመት የ35 ሺህ ሰዎች ጭማሪ በማድረግ 195 ሺህ ሠተኞችን በቋሚ ነዋሪነት ትወስዳለች።

አገሪቱ የምትቀበለውን የሰለጠን የስደተኛ ቁጥር ከፍ ያደረገችው ተጨማሪ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልጋት ነው ተብሏል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ጥብቅ የሆነው የኢሚግሬሽን ሕግጋቶቿ በተለያዩ ዘርፎች የሠራተኛ እጥረት እንዲያጋጥማት ምክንያት ሆነው ቆይተዋል።

የአውስትራሊያ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ክፍት የሥራ መደቦችን ለመሙላት በአብዛኛው ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከዩናይትድ ኪንግደም ሠራተኞች ይፈለጋሉ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ 480 ሺህ ክፍት የሥራ መደቦች ያሉ ሲሆን አሰሪዎች ሠራተኞችን መቅጠር አልተቻላቸውም ተብሏል።

በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሆቴል እና ቱሪዝም፣ ጤና፣ ግብርና እና የንግድ ሥራ ዘርፎች ከፍተኛ እጥረት ያጋጠማቸው መስኮች ናቸው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአውስትራሊያ መዲና ካንቤራ በተካሄደ ብሔራዊ የሠራተኞች ቅጥርን በተመለከተ ስብሰባ ላይ በሠራተኛ እጥረት ምክንያት በአየር ማረፊያዎች መተረማመስ መፈጠሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም በግብርናው ዘርፍ ፍራፍሬዎች የሚሰበስባቸው አጥተው በዛፎች ላይ መበስበሳቸውን እና በሆስፒታል ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩ ተገልጿል።

የአውስትራሊያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ክሌይር ኦኒል ለአጭር ጊዜም ቢሆን በአውስትራሊያ ከፍተኛ የሠራተኛ እጥረት መኖሩን ገልጸዋል።

አውስትራሊያ በእአአ 2010 አጋማሾች ላይ በየዓመቱ ትቀበላቸው የነበሩ ቋሚ ነዋሪ ስደተኞች ቁጥር 190 ሺህ ገደማ ነበር።

ይሁን እንጂ ከ2017 ጀምሮ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ቁጥር ቀንሶ ቆይቷል።

የአውስትራሊያ መንግሥት የተከማቹ የቪዛ ጥያቄ ጉዳዮችን በፍጥነት መጨረስ እንዲቻል ተጨማሪ 36 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር መመደቡን ገልጿል።

ከእአአ 2016 ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያቸውን በአውስትራሊያ አድርገዋል።