ከዩክሬን የተነሱት እህል የጫኑ መርከቦች ወዴት እየሄዱ ነው?

እህል የጫነች መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ “ለዓለም የተደረሰ ስምምነት” ሲሉ ጠርተውታል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ የተቋረጠውን የእህል ስርጭት ለማስቀጠል በተደረሰው ስምምነት ላይ ነው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ይህንን ንግግር ያደረጉት።

ሐምሌ 15/2014 ዓ.ም. በኢስታንቡል ባደረጉት ንግግር በጥቁር ባሕር ላይ እህል የጫኑ መርከቦች ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማለፍ እንዲችሉ የተደረሰው ‘ብላክ ሲ ግሬይን ኢንሺዬቲቭ’ የተሰኘው ስምምነት፣ “በረሃብ አፋፍ ላሉና በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑ ሕዝቦች” እፎይታ ያመጣል ብለዋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚህም ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩክሬንን እህል የጫኑ መርከቦች ከአገሪቱን የጥቁር ባሕር ወደቦች ለቀው ወደየአገራቱ እንዲያቀኑ አስችሏቸዋል።

ስምምነቱ ከተደረሰ ከአንድ ወር በኋላ ከ50 በላይ መርከቦች ዩክሬንን ለቀው ወጥተዋል። መርከቦቹ ከ1.2 ሚሊዮን ቶን በላይ የእህል ጭነትና ሌሎች የምግብ ሸቀጦችን ጭነዋል።

በወደቦቹ አቅራቢያ የሚደረገው ጦርነት እስካሁን ጭነቶቹን ያላስተጓጎለ ሲሆን፣ ሌሎች ተጨማሪ መርከቦችም እህል ለመጫን ወረፋቸውን እየጠበቁ ነው።

እህል የጫኑት መርከቦች መዳረሻ የት ነው?

በሚሊዮን የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ያሉ ሰዎችን ለመደገፍ ያቀደው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በተደረሰው ስምምነት ከዩክሬን መጠነኛ የሆነ እህል መግዛት ችሏል።

በዚህም በድርጅቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የተገዛውን የእርዳታ እህል የጫነችው የመጀመሪያዋ መርከብ ማክሰኞ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም. ጂቡቲ ደርሳለች።

ብሬቭ ኮማንደር የተሰኘችው ይህች መርከብ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሚገኙ በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች ታሳቢ በማድረግ 23 ሺህ ቶን ስንዴን ጭና ነው ጂቡቲ ወደብ የደረሰችው።

መርከቧ ከሁለት ሳምንታት በፊት የዩክሬን ፒቭደንኒ ወደብን ለቃ ነው ማክሰኞ ጂቡቲ የደረሰችው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሁለተኛዋ መርከብ ኤምቪ ካርቴሪያ 37 ሺህ ቶን ስንዴ ጭና ወደ የመን ለማድረስ ተዘጋጅታለች።

የተቋሙ ባለሥልጣናት ሌሎች እህል የጫኑ መርከቦች እንደሚከተሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሆኖም እነዚህ የእህል ጭነቶች ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር መጠናቸው በጣም አነስተኛ የሚባል ነው።

በአውሮፓውያኑ 2021 የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያደረገውን እርዳታ ስናይ 4.4 ሚሊዮን ቶን የምግብ እርዳታ በዓለም ዙሪያ አከፋፍሏል።

ከዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው የሚሆነው የተገዛው ከዩክሬን ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እነዚህ መጠነኛ ጅምሮች መሆናቸውን ቢገነዘቡም፣ ነገር ግን ሁኔታውን ሰፋ ባለ መልኩ መረዳት አስፈላጊ መሆኑን አጥብቀው ይናገራሉ።

“ወደቦች መከፈታቸውና የዩክሬን እህል በገበያው ላይ በከፍተኛ መጠን መገኘትን እኛ ከምንሰራው ጋር ልትለያዩት ይገባል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ ቃል አቀባይ ግሬግ ባሮው ተናግረዋል።

ካርታ

በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የዩክሬን እህል እንደገና መቅረቡ በእርግጠኝነት በዓለም ዙሪያ እፎይታን አስገኝቷል።

“ለአየርላንድ ግብርና ጥሩ ዜና ነው” ሲሉ የአየርላንድ የእንስሳት መኖና እህል ግንባር ቀደም አስመጪ ተቋም የሆነው አርኤንድኤች ሆል የንግድ ዳይሬክተር ጆን በርጂን ተናግረዋል።

33 ሺህ ቶን በቆሎ የጫነ ናቪ ስታር መርከብ በቅርቡ በአየርላንድ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ ፎይንስ መድረሱ እንደ መልካም እመርታ ታይቷል።

የእህል መርከቧ የተጫነችው የካቲት ወር ላይ ሲሆን ይህም የሩሲያ ወረራ በተጀመረበት ዕለት ነው።

“ጦርነቱ በተጀመረበት ማለዳ በዚያ መርከብ ላይ 28 ሺህ ቶን የእህል ጭነት ነበር” ሲሉ በርጊን ያስታውሳሉ።

“የእህል አቅራቢያችን መርከቧን መላክ አልቻለም። ከዚያም በኋላ ወደቡ የጦር አውድማ ሆነና ጭነቱ መውጣት አልቻለም” ብለዋል።

ጦርነቱ የዩክሬን ከፍተኛ ወጪ ንግድ ወቅት የሆነው ከታኅሣሥ እስከ ሚያዝያ ያለውን ወቅት ቀጥ እንዲል አድርጎታል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ድርቆች ምክንያት የእህል ዋጋ ቢጨምርም፣ ነገር ግን በቅርቡ መሻሻል አሳይቷል።

“ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አማካኝ የወጪ ንግድ ዋጋ ከ30 አስከ 40 በመቶ ከፍ ያለ ነበር” ሲሉ በዓለም አቀፉ የእህል ምርት ንግድ ምክር ቤት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አሌክሳንደር ካራቫይትሴቭ ተናግረዋል።

አክለውም “በአሁኑ ወቅት 8 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን ዋጋውም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል” ብለዋል።

ግራፍ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእህል ዋጋ የቀነሰው በወቅታዊ ተፅእኖዎች ምክንያት ነው፤ በመጀመሪያ ደረጃ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ምርት እየተሳለጠ ከመሄዱ በተጨማሪ ከዓለም ዋነኛ የእህል አምራቾች መካከል የዩክሬን ወደብ እንደገና መከፈቱ ያመጣው ሥነ ልቦናዊ አንድምታ ነው።

“በገበያው ላይ የተወሰነ መተባባርን ያመጣል” ይላሉ በርጊን።

የእህል ክምችቶች ባዶ ሆነው ባለበት ወቅት ቀደምሲል መውጫ አጥተው የነበሩ መርከቦች ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ ኢንዱስትሪዎች የተሻሉ ቀናት እንደሚመጡ ተስፋ አድርገዋል።

“የግብርና ምርቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ ፍሰታቸውን እንደሚቀጥሉ በርካቶች ተስፋ አድርገዋል” በማለት በዩክሬን ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው የእህል እና የቅባት እህል ላኪ የሆነው የቪቴራ ቃል አቀባይ ይናገራሉ፥።

"የመርከብ ባለቤቶች ወደ ዩክሬን ወደቦች ለመግባት ያላቸውን ፍላጎት እያየን ነው፣ ይህም መተላለፊያው ደኅንነቱ የተጠበቀ ከሆነ ይጨምራል” ይላሉ።

በሐምሌ ወር ኢስታንቡል ውስጥ የተደረገ ስምምነት ቢኖርም የጭነት ወጪዎች ከጦርነቱ በፊት በእጥፍ ጨምሯል።

ይህም መርከቦችን ወደ ጦርነት ቀጠና ከመላክ ጋር ተያይዘው ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን በተመለከተ የሰፈነውን የማያቋርጥ ስጋትን ያሳያል።

የሰፈነውም የአደጋ ስጋት ዩክሬን ለተጎዳው ኢኮኖሚዋ ገቢ እንድታገኝ የሚያስፈልጋትን ሽያጭ እንዳታገኝ መሰናክል እንዳይሆን ተፈርቷል።

“በየወሩ አምስት ሚሊዮን ቶን ለመሸጥ ዕቅድ ይዘዋል” በማለት የሚናገሩት የሎይድ ሊስት ዳታ ዘጋቢ ብሪጅት ዲያኩን ይናገራሉ። ሆኖም “የተለጠጠ ዕቅድ ይመስላል” ይላሉ ዘጋቢው።

በአሁኑ ወቅት ወደ ዩክሬን እየገቡ ያሉት አነስተኛ የመርከብ ማጓጓዣ ኩባንያዎች ናቸው።

ይህንን አደጋ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ የሆኑት እነዚህ ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ የቱርክ ሲሆኑ በርካታ የዓለም ታላላቅ ኩባንያዎች ወደ ዩክሬን ለመግባት ገና ፈቃደኛ አይደሉም፤ በማለት በሎይድ ሊስት ውስጥ ከፍተኛ የገበያ ዘጋቢ የሆኑት ኒዳአ ባክሽ ያስረዳሉ።

“እናም ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ዋስትና ማግኘት አልቻሉም” ብለዋል።

ሰዓቱ እያለቀ ነው። በተባበሩት መንግሥታት እና በቱርክ አደራዳሪነት የተደረገው የዩክሬ እና የሩሲያ ስምምነት የሚቆየው ለ120 ቀናት ብቻ ነው።

ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ሊራዘም ይችላል፤ ይህ ግን የሚሆነው ሩሲያ እና ዩክሬን ከተስማሙ ብቻ ነው።

ከስምምነቱ ስኬት ጀርባ በርካታ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ ለሚለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአራት ወራት በኋላ መቆሙ ፈታኝ ነው።

“ያ ገበያ እንደገና ከተዘጋ ዓለም ሌላ ትግል ውስጥ ይገባል” ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃለ አቀባዩ ግሬግ ባሮው ያስረዳሉ።

እህል የማመላለስ ስምምነቶች በተለምዶ ከ18 ወራት እስከ ሁለት ዓመታት በሚዘልቅ ወቅት ይደረጋሉ።

የራዞኒ መርከብ በጥቁር ባህር ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመጨረሻም፣ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ታላቅ አድናቆት ተችሯት ዩክሬንን ለቃ የወጣችው የመጀመሪያዋ መርከብ ራዞኒ የት ደረሰች የሚለው ነው?

የተባበሩት መንግሥታት ዝርዝር የመርከቧን መዳረሻ አስመልክቶ ገና እንዳልተወሰነ የሚያሳይ መረጃን አስፍሯል።

በመጀመሪያ ታስቦ የነበረው 26 ሺህ ቶን በቆሎ የጫነችው መርከብ ወደ ሊባኖስ ትሪፖሊ ወደብ ለማድረስ ቢሆንም አሳፋሪ በሆነ መልኩ ጭነቱ እዚያ አልደረሰም።

የእህል ጭነቱ ገዢ በጥራት ላይ ያለውን ስጋት በመጥቀስ እህሉን ውድቅ ማድረግ ተከትሎ ራዞኒ በምሥራቅ ሜዲትራንያን አካባቢ መዟዟሯ እንዲሁም ክትትል ማድረጊያ መሳሪያው እንዲጠፋ ተደርጎ ነበር።

በመጨረሻም አብዛኛውን የእህል ጭነት በሶርያ ታርተስ ወደብ አራገፈች።

የእህል ጭነቱ ሶሪያ መድረሱ ሕገወጥነት የለውም ወይንም መርከቦች አቅጣጫቸውን መቀየራቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም።

ነገር ግን የራዞኒ ምስጢራዊ ጉዞ እንደሚያሳየው ውስብስብ በሆነው የእህል ንግድ ዓለም ውስጥ፣ እያንዳንዱ ጭነት በመጨረሻ የት እንደሚደርስ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።