በአዋሽ ፈንታሌ በድጋሚ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በአዲስ አበባ የመሬት ንዝረት ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቅምት 3/2017 እሑድ ጥዋት አካባቢ በአፋር ክልል በሚገኘው በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተሰምቷል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት አደም አሊ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ይህን የመሬት ነውጥ መከሰተን አረጋግጠዋል።
ዩኤስጂኤስ የተሰኘው የአሜሪካ መንግሥት የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ማዕከል በሬክተር ስኬል 4.6 ጥንካሬ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ መከሰቱን በድረ-ገፁ አመልክቷል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ እንደገለፁት የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬ እሑድ ጥዋት 1፡30 ገደማ ነው የተከሰተው።
አደም አክለው በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት እስካሁን ድረስ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጸዋል።
በአፋር ክልል በተለይ ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች እየተከሰቱ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የሚከሰቱ የመሬን መንቀጥቀጦችን ተከለትሎ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ እና በአጎራባች ከተሞች የመሬት ንዝረት እየተሰማ ነው።
እሑድ ጥቅምት 3/2017 የተከሰተውን መካከለኛ የመሬት ነውጥ ተትከሎ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት ንዝረት እንደሰሙ ነዋሪዎች በማኅበራዊ ሚድያ የትስስር ገፆች ላይ እያጋሩ ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Crisis24.garda.com
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳረጋገጡት በአዲስ አበባ በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ የመሬት ንዝረት ተከስቷል።
ዳይሬክተሩ አክለው ባለፉት ሳምንታት እየተከሰቱ ያሉ የመሬት መንቀጥቀጦች እና ንዝረቶች መካከለኛ እና ለጉዳት የማያጋልጡ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት እሑድ ምሽት 2፡10 ገደማ በተመሳሳይ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ 4.9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ይታወሳል።
የአሜሪካው ዩኤስጂኤስ እና ሌሎች የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከታተሉ ድረ-ገፆች በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ መጠን 4.6 እንዲሁም ጥልቀቱ 10 ኪሎ ሜትር መሆኑን አስፍሯል።
ክራይሲስ24 የተባለው ርዕደ መሬት የሚከታተል ድረ-ገፅ እሑድ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም. የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከሉ ከአዋሽ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አሳውቋል።
ድረ-ገፁ ጨምሮም በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሬት ንዝረት እንደነበር ገልጿል።
ደቡባዊ አፋር፣ ደቡብ አማራ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲሁም የተወሰኑ የሶማሊ ክልል አካባቢዎች የመሬት ንዝረት ሊሰማቸው እንደሚችል አስፍሯል።
ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ በተከሰተ “የመሬት መንቀጥቀጥ” ምክንያት ከተፈጠረ የመሬት ስንጥቅ ውስጥ ፍል ውሃ መፍለቅ መጀመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳደር ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ ባለው የአፋር ክልል ዱለሳ ወረዳ ፍል ውሃ መፍለቅ የጀመረው ሰኞ መስከረም 27/2016 ዓ.ም. ነው።












