ሩዋንዳ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ ስደተኞችን ከሊቢያ ተቀበለች

የፎቶው ባለመብት, Rwanda Ministry in charge of Emergency Management
ሩዋንዳ ኢትዮጵያውንን ጨምሮ ከሌሎች አገራት የተውጣጡ 91 ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሊቢያ መቀበሏን አስታወቀች።
እነዚህ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ የተላኩት በተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት በሚደግፉት ፕሮግራም ተካትተው ነው።
ሰባት ኢትዮጵያውያን፣ 33 ኤርትራውያን፣ 38 ሱዳናውያን እና ሁለት የደቡብ ሱዳን ዜጎች በዚህኛው ዙር እንደተካተቱም ተገልጿል።
በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትናወጠው ሊቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ስደተኞችን ለማስወጣትም የአደጋ ጊዜ ትራንዚት የሚል ፕሮግራም ተቋቁሟል።
በዚህም ፕሮግራም አማካኝነት ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮም 2 ሺህ 150 ስደተኞችን ከሊቢያ በማስወጣት ወደ ሩዋንዳም ማዘዋወር ተችሏል።
ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 600 የሚሆኑት በአሜሪካ እና በተለያዩ አውሮፓ አገራት መኖሪያ አግኘትው እንዲሰፍሩ መደረጋቸውንም ሩዋንዳ አስታውቃለች።
“ሩዋንዳ ለተቸገሩ ሰዎች መጠለያ ለመሆን ቁርጠኝነቷን እያሳየች ነው” ሲልም የሃገሪቱ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ሚኒስቴር ሐሙስ እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከሊቢያ ከሚመጡ ስደተኞች በተጨማሪ ዩናይትድ ኪንግደምም ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ እየሞከረች ትገኛለች።
በህገወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል የተባሉ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ተልከው ጥያቄያቸው ከዚያ የሚታይበትን የተለየ እቅድም ለመተግበር የዩኬ መንግሥት እየሞከረ ይገኛል።
ይህ እቅድም ከሩዋንዳ የደህንንት ስጋት ጋር በተገናኘ በፍርድ ቤቶች መታገዱ ይታወሳል።
እነዚህን ሙግቶችንም ለማሸነፍ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር አስተማማኝ አድርጎ የሚፈርጃት ‘የሩዋንዳ ሴፍቲ ቢል’ (የሩዋንዳ የደህንነት ረቂቅን) ለማጽደቅ እየሞከረ ይገኛል።
ከዚህ በተለየ ዩኬ በአገሯ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞችን እስከ 3 ሺህ ፓውንድ በመክፈል ወደ ሩዋንዳ ልትልክ መሆኑን በቅርቡ አስታውቃለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ በዘ ታይምስ ይፋ የሆነው ይህ አዲስ የስደተኞች ዕቅድ የጥገኝነት ጥያቄያቸው ያልተሳካላቸው ስደተኞች በበጎ ፈቃደኝነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ለዚህም የሚሆን ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።
የጥገኝነት ጥያቄያቸው በዩናይትድ ኪንግደም ውድቅ ለተደረገባቸው ለማንኛውም ስደተኞች ክፍት ይሆናል ተብሏል።
ይህ ዕቅድ በተለይም ወደ አገራቸው መመለስ በማይችሉ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ ነው።












