ኢራን እስራኤል ላይ ጦርነት ትከፍታለች በሚል የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባ ተቀመጡ

የፎቶው ባለመብት, White House/ X
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ልትከፍት ትችላለች የሚለው ስጋት ማየሉን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከብሔራዊ ደኅንነት አባሎች ጋር ስብሰባ ተቀመጡ።
ከስብሰባው በኋላ ፕሬዝዳንት ባይደን ኢራን ጦርነት ብትጀምር አሜሪካ ለእስራኤል ለምትሰጠው ድጋፍ እየተደረጉ ስላሉ ዝግጅቶች ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንክን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረትን ለመቀነስ የአሜሪካ መንግሥት “ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኤል ሃኒያ ኢራን ውስጥ ከተገደሉ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት እጅጉን አይሏል።
ኢራን ለሐማስ መሪ ግድያ እስራኤል እና አሜሪካንን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን ለኢስማኤል ሃኒያ ሞት እስራኤል ከባድ ዋጋ ትከፍላለች ስትል ዝታለች።
ለሐማስ አጋርነቱን የሚገልጸው እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ እንዲሁ እስራኤል ላይ ሲዝት ቆይቷል።
ከኢስማኤል ሃኒያ ግድያ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ውስጥ የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኮማንደር ፉዓድ ሹክር በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉ ይታወሳል።
ኢራን እና ሄዝቦላ ዘመቻ ቢከፍቱ እስራኤል ሙሉ ወታደራዊ ኃይሏን ልትጠም ስለምትችል በመካከለኛው ምሥራቅ ሰፊ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ይህን ተከትሎ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና ጀርመን ያሉ አገራት ዜጎቻቸው ከሊባኖስ ማስወጣት ጀምረዋል።
በርካታ አየር መንገዶችም ወደ ሊባኖስ የሚያደርጉትን በረራዎች እየሰረዙ ይገኛሉ።
በአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ስብሰባ ላይ ባለሙያዎች ለፕሬዝዳንት ባይደን ኢራን መቼ እና ምን ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ግልጽ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ስብበሳ ቀደም ብሎ አንቶኒ ብሊንከን ኢራን እና ሄዝቦላህ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ እስራኤል ላይ ጥቃት ሊከፍቱ እንደሚችሉ ለቡድን 7 (ጂ7) አገራት መሪዎች ተናግረዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት ስላከረረው የሐማስ ፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ እስራኤል እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃይል ሃኒያ የተገደሉት በአሜሪካ ድጋፍ በእስራኤል በተፈጸመ ሴራ ነው ቢልም እስራኤል እስካሁን ድረስ ግድያውን በተመለከተ ያለችው ነገር የለም።
የሃኒያ ግድያን ተከትሎ የኢራን አብዮታዊው ዘብ ባወጣው መግለጫ እስራኤል "በተገቢው ጊዜ፣ ቦታ እና መንገድ ከባድ ቅጣት ይጠብቃታል” ብሏል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ውጥረት ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቀጠናው የሚያደርጉትን በረራ እስረዙ ነው።
የጀርመኑ ሉፍታንዛ ወደ እስራኤል እና ኢራን መዲናዎች ቴል አቪቭ እና ቴህራን እንዲሁም ወደ ሊባኖሷ ቤይሩት የሚያደርገውን በረራዎች በጊዜያዊነት ሰርዟል።
የአሜሪካው ዴልታ እንዲሁ ወደ ቴል አቪቭ የሚያደርገውን በረራ አቋርጧል።












