የዓለም ጤና ድርጅት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ስም ሊሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library
የዓለም ጤና ድርጅት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ አዲስ ስያሜ ለመስጠት ከባለሙያዎች ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
ድርጅቱ የበሽታውን ስያሜ ለመቀየር የወሰነው ባለፈው ሳምንት ከ30 ባላይ ተመራማሪዎች በሽታውን ለሚያስከትለው ቫይረስ እና ለበሽታው “መገለልና መድልዎን የማያስከትል ስም በአስቸኳይ እንዲፈለግለት” ከጠየቁ በኋላ ነው።
ተመራማሪዎቹ ጨምረውም ቫይረሱ የአፍሪካ መሆኑን የሚያመለክቱ አገላለጾች መቀጠላቸው ትክክል ካለመሆኑ ባሻገር አግላይ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት በዓለም ዙሪያ 1,600 የሚሆኑ የበሽታው ክስተቶች ተመዝግበዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቀደም ብሎ ጀምሮ በተከሰተባቸው አገራት ውስጥ እስካሁን 72 ሰዎች በበሽታው መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፣ በቅርቡ በሽታው አዲስ በተከሰተባቸው 32 አገራት ውስጥ ግን ምንም ሰው አልሞተም።
የዓለም ጤና ድርጅት በሚቀጥለው ሳምንት በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዝብ ጤና ስጋት ነው አይደለም በሚለው ላይ ውሳኔ ይሰጣል።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በዓለም ሕዝብ ጤና ላይ አደጋ ናቸው በሚል የታወጁት የወፍ ጉንፋን፣ ፖሊዮ፣ ኢቦላ፣ ዚካ እና ኮቪድ ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት "የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ መከሰት ያልተለመደና አሳሳቢ ነው።”
"በዓለም አቀፍ የጤና ደንብ መሠረት በሚቀጥለው ሳምንት የአስቸኳይ ኮሚቴ ስብሰባ ለመጥራት የወሰንኩት፣ ወረርሽኙ የዓለም ማኅበረሰብ ጤና ጠንቅ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ነው” ብለዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ምንድን ነው?
በሽታው የሚከሰው መንኪፖክስ በተባለ ቫይረስ ነው።
ለፈንጣጣ (ስሞልፖክስ) ከሚያጋልጠው ቫይረስ ጋር ዝርያው ይቀራረባል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ከፈንጣጣ ጋር ሲነጻጸር የሚሰራጭበት ፍጥነት አናሳ ከመሆኑም በላይ ሕመሙም አይበረታም።
በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ አገራት በገጠራማ አካባቢዎች ነው በብዛት የሚከሰተው። በተለይም በጥቅጥቅ ደን (ሬንፎረስት) አቅራቢያ ያጋጥማል።
ቫይረሱ ሁለት ዓይነት ዝርያ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው የምዕራብ አፍሪካ ሁለተኛው ደግሞ የማዕከላዊ አፍሪካ የሚባሉ ናቸው።
ዬኬ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ሁለቱ ከናይጄርያ የተጓዙ ናቸው ተብሏል። ስለዚህ የተገኘባቸው የምዕራብ አፍሪካው ቫይረስ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
ይህ ቫይረስ ለከፋ ሕመም አያጋልጥም።
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ ሰዎች መካከል ይህ ነው የሚባል ግንኙነት አልተስተዋለም።
የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ታማሚዎችም ይገኙበታል።
ሰዎቹ ዩኬ ውስጥ ቫይረሱ ከተሰራጨ በኋላ በበሽታው እንደተያዙ ይገመታል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት እዚህም እዚያም ማበጥ እና በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል።
ሙቀቱ ጋብ ሲል ሰውነት ከፊት ጀምሮ ማሳከክ ይጀምራል። መላው ሰውነትን ቢያሳክክም ክንድና እግር የበለጠ ያሳክካሉ።
የሚከሰተው እከክ በጣም የሚያምና በተለያየ ደረጃ የሚያልፍ ነው።
ቆዳ ላይ የሚከሰተው እብጠት ኋላ ላይ ቆዳ እንዲቆስልና እንዲረግፍም ያደርል። ጠባሳ ጥሎም ሊያልፍ ይችላል።
ሕመሙ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ሲሆን ከ14 እስከ 21 ቀናት ይወስድበታል።
በሽታው እንዴት ይይዛል?
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ተጋላጭ ናቸው።
በቆዳችን ክፍተቶች በኩል፣ በዓይን፣ በአፍንጫ ወይም በአፍ በኩል ቫይረሱ ወደ ሰውነታች ይገባል።
በወሲብ ወቅት ባለ ንክኪም ቫይረሱ ይተላለፋል።
በቫይረሱ ከተያዙ ዝንጀሮዎች፣ አይጦች ወይም ሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ ከተደረገ ቫይረሱ ወደ ሰው ይተላለፋል።
ቫይረሱ በልብስ ወይም በሌሎችም ንክኪ ባላቸው ጨርቆች በኩልም ይተላለፋል።
ምን ያህል አስጊ ነው?
አብዛኞቹ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ለከፋ ሕመም አይዳረጉም።
ልክ እንደ ፈንጣጣ በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ ይጠፋል። ሆኖም ግን በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስም ይችላል።
በምዕራብ አፍሪካ በበሽታው ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አሉ።
በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ወሲብን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ንክኪ ሲኖር የበሽታው የመተላለፍ ዕድም ያለው ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ወንዶች ዘንድ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል ጨምሮ ታይቷል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በማቆያ ውስጥ ባለ ዝንጀሮ ላይ ነበር።
እአአ ከ1970 ወዲህ በ10 የአፍሪካ አገራት በሽታው ተከስቷል።
በ2003 በአሜሪካ ሲከሰት ከአፍሪካ ውጪ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። ወደ አገሪቱ ከገቡ እንስሳት ላይ አንድ ውሻ በቫይረሱ ተይዞ ነበር ሕመሙ የተነሳው።
81 ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙም የሞተ ሰው አልነበረም።
በ2017 በናይጄሪያ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተሰራጭቶ 172 ሰዎች መያዛቸው ይታወሳል።
75 በመቶ ታማሚዎች ከ21 እስከ 40 ዓመት የሆናቸው ወንዶች ናቸው።
ሕክምና አለው?
ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ሕክምና የለውም።
ነገር ግን ስርጭቱን መቆጣጠር ይቻላል።
ክትባቱ በሽታውን በመከላከል ረገድ 85 በመቶ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል።
በዩናትድ ኪንግደም የጤና ደኅንነት ተቋም የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጆናታን ባል እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት ከነበራቸው 50 ሰዎች አንዱ ብቻ በቫይረሱ መያዙ፣ የቫይረሱ የስርጭት መጠን ውስን መሆኑን ያሳያል።












