ትራምፕ ለምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ከአንድ ግለሰብ ብቻ የ50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኙ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty

አወዛጋቢ የሚባሉት አሜሪካዊው ቢሊየነር ቲሞዚ ሜለን ለትራምፕ የምርጫ ዘመቻ 50 ሚሊዮን ዶላር መለገሳቸው ተገለጸ።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ባለፉት ሳምንታት ያሰባሰበውን የገንዘብ መጠን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። በዚህም ትራምፕ ኅዳር 2017 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከ68 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱ ተመልክቷል።

በባንክ ሥራ ላይ የተሰማራው የሜለን ቤተሰብ ለትራምፕ የምርጫ ዘመቻ 50 ሚሊዮን ዶላር መደገፉን ሮይተርስ ዘግቧል። ሊዝ እና ዲክ ኡዩሌን ከተባሉ ባለሀብቶች ደግሞ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ድጋፍ ተደርጓል።

ቢሊየነሩ ሜለን የ50 ሜሊዮን ዶላሩን ድጋፍ ያደረጉት ትራምፕ የንግድ ሰነዶችን በማጭበርበር በኒው ዮርክ ችሎት በ43 ክሶች ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

እኚህ ባለሀብት በግላቸው ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ለሚወዳደሩት ሮበርት ኬኔዲ ጁኒየር ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ 20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

እነዚህ የገንዘብ ድጋፎች ‘ሱፐር ፓክ’ በተሰኘ ኮሚቴ አማካይነት ነው የሚሰባሰቡት። ‘ሱፐር ፓክ’ በአሜሪካ ለምርጫ ለሚወዳደሩ እጩዎች ያልተገደበ የገንዘብ መጠንን ከለጋሾች ያሰባስባል።

ሜለን ለትራምፕ ያደረጉት የ50 ሚሊዮን ዶላር ደጋፍ ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከተሰበበው የድጋፍ ገንዘብ በላይ እንዲሆን አስችሏል።

መገናኛ ብዙሃን መቅረብን የማይወዱት አሜሪካዊው ቢሊየነር በአሜሪካ ዋዮሚንግ ግዛት የሚኖሩ ሲሆን የትራንስፖርት ዘርፋ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ይመራሉ።

እንደ ፎርብስ ግምት ከሆነ የሜለን ቤተሰብ 14.1 በሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አለው።

በሌላ በኩል ሌላኛው አሜሪካዊ ባለሀብት ማይክ ብሉምበርግ በሱፐር ፓክ አማካኝነት ለትራምፕ የምርጫ ዘመቻ 20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል።

ባለሀብቱ ብሉምበርግ ለባይደን ያደረጉት ድጋፍ ለወቅቱ ፕሬዝዳንት ድጋፍ ላለው ቡድን 19 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍን የሚያጠቃልል ነው።

ተጨማሪ 900 ሺህ ዶላር ለባይደን ‘የድል ድጋፍ’ ለተሰኘው መርሃ ግብር እና ለዴሞክራቶች ፓርቲ በጋራ ድጋፍ ተደርጓል።

ትላንት ሀሙስ የኬንዲ የምርጫ ቡድን ባለፈው ወር 280 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማግኘቱን ገልጾ ከዚህ ውስጥ ከቢሊየነሩ ሜለን የተሰበሰበ ገንዘብ እንደሌለበት ታነግረዋል።