በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል የተወሰኑት ዛሬ ቀብራቸው ተፈጸመ

ባሳለፍነው ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል ቢያንስ የሰባት ሰዎች ቀብር ዛሬ ተፈጸመ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ሰዎች ዛሬ ከእኩለ ቀን በኋላ የ7 ሰዎች ስርዓተ ቀብር በሼኽ ኤሊያስ መካነ መቃብር መፈጸሙን ተናግረዋል።
የሟቾችን አስክሬን የሚረከብ የቤተሰብ አባል እስኪመጣ ድረስ ከጤና ተቋም አስክሬን ማውጣት ባለመቻሉ ቀብራቸው ያልተፈጸሙ ሰዎች እንዳሉም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
"7 ሰው ቀብረናል። ሌላውን አስክሬን ለመውሰድ ቤተሰብ ይምጣና ይፈርም ተብሎ አልተቀበሩም" በማለት በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የነበሩ እና በመጀመሪያ ስማቸው ብቻ እንድንጠራቸው የጠየቁን አቶ ዳውድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ዳውድ ጨምረው እንደተናገሩት፤ ከሟቾቹ መካከል ማንነታቸው እስካሁን ያልተለዩ ሰዎች አሉ።
ሌላኛው ዛሬ ሚያዚያ 20/2014 ዓ.ም. በተከናወነው የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ ተሳታፊ የነበረው ሙባረክ፤ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ወቅት የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች በአከባቢው ተሰማርተው እንደነበረ ይናገራል።
"የተኩስ ድምጽ ነበር። ግን ወዲያው ነው የቆመው። ቀብሩ ተፈጽሟል" በማለት በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበረው ሙባረክ ለቢቢሲ አስረድቷል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጎንደር ከተማ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሼህ ኤሊያስ መካነ መቃብር የቀብር ስነ ስርዓት ወቅት በተነሳ ግጭት ሳብያ ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ150 በላይ ሰዎችም ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጾ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Twitter
የጎንደሩን ክስተት በርካታ የሙስሊም ማሕብረሰብ አባላትን አስቆጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ በአንዋር መስጅድ በትናንትናው ዕለት የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
በዚህ ግጭት ካጋጠመው የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት በተጨማሪም በመስጂዶች ላይ ውድመት መድረሱ እና በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሀብት ንብረት መዘረፉን የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳይ ምክር ቤት አስታውቋል።
ማክሰኞ ሚያዚያ 18/2014 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ያጋጠመውን ክስተት የክልሉ መንግሥት እና የሃይማኖት ሕብረት ተቋማት አውግዘውታል።
ግጭቱ እንዴት ተነሳ?
የአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግጭቱ የተነሳው በሼኽ ከማል ለጋስ ቀብር ወቅት በመካነ መቃብሩ ስፍራ አጠገብ ካለው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ተነስቷል በሚል እንደሆነ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጎንደር ነዋሪ፣ የግጭቱ መነሻ ለሼኹ ቀብር የወጡ ሰዎች ከመካነ መቃብሩ አጎራባች ካለችና አዲስ ከተሠራችው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ለማንሳት በመሞከራቸው ነው ይላሉ።
"ከቤተ ክርስቲያኗ ድንጋይ ሲያነሱ ለምን ታነሳላችሁ? የሚል ነው የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላም ወደ ቡድን ግጭት ተቀየረ" ይላሉ።
ሐጂ ዑስማን በበኩላቸው "ይህ የተሳሳተ ነው። ቀብር ሲፈጽሙ ድንጋይ የሚያነሱት እዛው ቦታቸው ላይ ነው። ከቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ አይደለም። በሌሎች አካላት የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ወንጀለኞችንና አጥፊዎችን ላለመያዝና ጥፋተኞችን ወደኛ ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው" ብለዋል።
ለዚህ ግጭት መነሻ ሊሆን የሚችል ጉዳይ የለም ያሉት ሐጂ ዑስማን፣ "አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት የሚሉ ፅንፈኛ አክራሪዎች የፈጸሙት ድርጊት ነው" ይላሉ።
ሌላኛው የጎንደር ነዋሪ በበኩላቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ግጭት በጎንደር ተከስቶ እንደማያልቅ ተናግረው "ታላቅ አባት ሞተው በቀብር ድንጋይ ነው ግጭቱ ተነሳ የተባለው። ይህ ምክንያት አይሆንም። በመሃል የገቡ አንዳንድ ችግር ፈጣሪዎች ነበሩ" አሁን ግን በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
ሐጂ ዑስማን በትናንትናው ዕለት የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነና ላለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ።
"በሆደ ሰፊነት ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በአካልም ከሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ሰፊ ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርገናል" የሚሉት ሐጂ ዑስማን፣ "ነገር ግን የመንግሥት አመራሮች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው የተፈጠረ ችግር ነው" ይላሉ።
በአሁኑም ወቅት በሕግ አግባብ ችግሮች እንዲፈቱ፣ አጥፊዎች እንዲያዙ፣ ወንጀለኞች እንዲቀጡ፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።












