ፊፋ የኳታር የዓለም ዋንጫ ዳኞች ምርጫን በተመለከተ የወጡት ዘገባዎች ሐሰተኛ ናቸው አለ

አርቢትር በአምላክ ተሰማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርቢትር ባምላክ ተሰማ

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ዳኞች ምርጫን በተመለከተ የወጡት ዘገባዎች ፍጹም የሐሰት ናቸው አለ።

ከትናንት መጋቢት 27/2014 ዓ.ም. ጀምሮ የምዕራብ አፍሪካ ድረ-ገጾች እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አርቢትር ባምላክ ተሰማን ጨምሮ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን እንዲዳኙ 8 አፍሪካውያን ዳኞች መመረጣቸውን ሲዘግቡ ነበር።

የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባምላክ ተሰማ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ መመረጡን የዘገቡት ፊፋን ዋቢ አድርገው ነው።

ይሁን እንጂ ፊፋ ይህ ፈጽሞ ሐሰተኛ ነው ብሏል። "ይህ ከፊፋ የወጣ አይደለም። ወደፊት የዳኞች ሹመትን የምናሳውቅ ይሆናል። ከዛ በፊት የሚወጡ በሙሉ ከፊፋ አይደሉም" ይላል ቢቢሲ ከማህበሩ ያገኘው መረጃ።

ጉዳዩን በተመለከተ ቀደም ሲል ቢቢሲ ዓለም አቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማ ባነጋገረ ወቅት "ለኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ በዳኝነት እንዳጫውት በፊፋ መመረጤን አላውቅም" ብሎ ነበር።

"ምንም ነገር አላውቅም። በይፋ የደረሰኝ ነገር የለም" ሲል ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"እንደዚህ ዓይነት መረጃ ከየት እንደሚመጣ አላውቅም" ያለው ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሰማ፤ ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ በፊፋ ስለመመረጡ የወጡ ዘገባዎችን መመልከቱን ግን ተናግሯል።

ባምላክ ፊፋ የዓለም ዋንጫን የሚመሩ ዳኞችን ማንነት ይፋ ለማድረግ ጊዜው የፈጠነ ነው ብሎ እንደሚያስብ ጨምሮ ገልጾ ነበር።

ከዚህ ቀደም በሩሲያ አዘጋጅነት በተደረገው የዓለም ዋንጫ፤ ፊፋ በውድድሩ ጨዋታዎችን እንዲዳኙ የመረጣቸውን ዳኞች ይፋ ያደረገው ውድድሩ ከመጀመሩ 10 ሳምንታት ሲቀሩት ነበር።

በቀጣይ ዓመት የሚካሄደው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የሚጀምረው ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሕዳር 2015 ዓ.ም. ነው።

ባምላክ ተሰማ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በመሃል ዳኝነት ባሳየው ድንቅ ብቃት በበርካቶች ሲወደስ ነበር።

ባምላክ ይህን ውድድር ልትዳኝ በፊፋ የምትመረጥ ይመስልሃል ወይ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

በሩሲያ አዘጋጅነት በተካሄደው የ2018ቱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ባምላክ ተሰማ ተሳፊ እንደነበረ ይታወሳል።