ዩክሬን ጦርነት፡ ምዕራባውያን መሪዎች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራባውያን መሪዎች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥሉ መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ጄን ሳኪ ማዕቀቡ የሩሲያ የፋይናንስ እና ባለቤትነታቸው የመንግሥት የሆኑ ተቋማትን እንዲሁም የተወሰኑ ባለሥልጣናትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸው ባለሃብቶችን [ኦሊጋርኮችን] ኢላማ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
ፕረስ ሴክሬታሪዋ አክለውም እርምጃው "የፑቲንን ጦር የሚደግፈውን የሩሲያ አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋል" ብለዋል።
በዩክሬን ቡቻ ከተማ በሩሲያ ጦር ተፈፀሙ የተባሉ የጭካኔ ድርጊቶችን ተከትሎ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል የሚደረጉ ጥሪዎች እየጨመሩ መጥተዋል።
የከተማዋ ከንቲባ ማክሰኞ ዕለት ለቢቢሲ እንደገለፁት የሩሲያ ኃይሎች ከተማዋን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት 320 የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል። የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውም በምዕራባውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
ፕረስ ሴክሬታሪዋ ሳኪ ማክሰኞ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በሩሲያ ሁሉንም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ይከለክላል ተብሎ የሚጠበቀው ማዕቀቡ "የሩሲያን መንግሥት ወሳኝ መሳሪያዎችን ያዳክማል፣ በሩሲያ ላይ ፈጣንና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የሩሲያ ትልቁ አበዳሪ ስበር ባንክ በማዕቀቡ ኢላማ ከተደረጉ ተቋማት አንዱ ሊሆን እንደሚችል ማክሰኞ ዕለት አስነብቧል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው ማዕቀቡ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ሁለት ሴት ልጆችን ኢላማ ሊያደርግ እንደሚችል ዘግበዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬስ ሴክሬታሪዋ በሪፖርቶቹ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ማዕቀቡም ከአውሮፓ ሕብረት እና ከሌሎች የጂ7 አገራት ጋር በመቀናጀት ይፋ እንደሚደረግም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ አክለዋል።
"ከጂ7 እና ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በመተባባር ሩሲያን በኢኮኖሚ፣ በፋይናንስ እና በቴክኖሎጂ ዋጋ የሚያስከፍሉ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይኖራሉ" ብለዋል።
ማክሰኞ ዕለት የአውሮፓ ኮሚሽን የሩሲያ የድንጋይ ከሰል ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ መከልከል እና በሞስኮ ውስጥ በመንግሥት የተያዙ የንግድ ተቋማት፣ ባለሥልጣናት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸው ባለሃብቶች ላይ ጨምሮ ሰፊ እና አዳዲስ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ሃሳብ አቅርቦ ነበር።
የ27ቱን የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ስምምነት የሚጠይቀውና የሩሲያን የድንጋይ ከሰል ላይ እገዳ ለመጣል የቀረበው ሃሳብ ከጸደቀ የአውሮፓ ሕብረት የሩሲያ የኃይል አቅርቦትን ሲከለክል የመጀመሪያው ይሆናል።
ኅብረቱ በየዓመቱ 3.3 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የድንጋይ ከሰል ከሩሲያ ይገዛል።
ጀርመንን ጨምሮ የተወሰኑ አገራት በሩሲያ ኃይል ላይ ጥገኛ በመሆናቸው በዘርፉ ላይ በቀጥታ እርምጃ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት አመንትተው ነበር። ይሁን እንጂ የሩሲያ የጦር ወንጀሎች ማስረጃዎች መውጣት ከጀመሩ በኋላ ሃሳባቸውን የለወጡ ይመስላሉ። የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የማዕቀብ ጥሪዎችን ተቀላቅለዋል።
አባል አገራቱ በአራት የሩሲያ ባንኮች ላይ እንዲሁም ከሩሲያ እና ከቤላሩስ በሚገቡና 4.59 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የእንጨት፣ ሲሚንቶ፣ የባህር ምግቦች እና የአልኮል መጠጦች ላይ ሙሉ ማዕቀብ ይጥላሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን፣ የአውሮፓ ሕብረት ወደቦችን ለሩሲያ መርከቦች ዝግ ለማድረግ እና የሩሲያ እና ቤላሩስ መንገድ ትራንስፖርት ኦፕሬተሮችን ከክልሉ ለማገድ እንዳሰቡ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንቷ ሩሲያ በዩክሬን ሰላማዊ ሰዎች ላይ "ጭካኔ የተሞላበት ጦርነት ታካሂዳለች" ሲሉ ከሰዋል።
በመሆኑም በዚህ ወሳኝ ወቅት በፑቲንና በሩሲያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና መደረግ አለበት ብለዋል።
ይሁን እንጂ የሉቱዌንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋብሬሊየስ ላንድስበርጊስ ማክሰኞ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበው የማዕቀብ ጥቅል "ተጨማሪ ግፍ መጋበዝ" ሲሉ ተችተዋል።
የቪልኒየስ ዋና ዲፕሎማት በትዊተር ገጻቸው ላይ "የድንጋይ ከሰል ፣ አራት ባንኮች… ወደቦች እና ድንበሮች እገዳ በእውነቱ እየደረሰ ላለው እልቂት በቂ የሆነ እገዳ አይደለም" ሲሉ ጽፈዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማክሰኞ እለት ባደረጉት ንግግር የሩሲያ መሪዎችን በአገራቸው የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ መስርተው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
"የሩሲያ ጦር አገራችንን የሚያገለግልን ማንኛውንም ሰው ፈልጎ ሆን ብሎ ይገድላል" ብለዋል። "ሙሉ ቤተሰቦችን፣ ጎልማሶችን እና ህጻናትን ገድለዋል፣ እናም አስከሬኖችን ለማቃጠል ሞክረዋል።" ሲሉም ከሰዋል።












