ተመድ እንደ ዩክሬናውያን ሁሉ አፍሪካውያን ስደተኞችንም እንድትቀበል የአውሮፓ ሕብረትን አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ አውሮፓ ለዩክሬን ስደተኞች እንዳደረገችው ሁሉ ለሌሎች ስደተኞችም ለጋስ እንድትሆንና እንድትቀበል አሳሰቡ።
ኃላፊው ይህንን ያሉት በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በተጨናነቀ ጀልባ ላይ ተሳፍረው ሜዲትራኒያን ባህርን ሲያቋርጡ በደረሰ አደጋ መሞታቸውን ተከትሎ ነው።
በአደጋ 90 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማሕበር እንደገለፀው ቅዳሜ ዕለት በደረሰው በዚህ አደጋ ከሞት የተረፉት አራት ሰዎች ብቻ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፣ "አውሮፓ ዩክሬናውያን ስደተኞችን በለጋስነት እና በብቃት አስተናግዳለች፤ በመሆኑም በተመሳሳይ ሌሎች ስደተኞችንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባት" ብለዋል።
" ይህንን የአውሮፓን በር በሚያንኳኩ እና በጭንቀት ውስጥ ባሉ ሌሎች ስደተኞች ላይ እንዴት እንደሚተገበር በአስቸኳይ ማጤን አለባት" ብለዋል ኃላፊው እሁድ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች በአውሮፓ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ይሞክራሉ።
ይሁን እንጂ ከአሰቡበት የሚደርሱት ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በተጨናነቁ እና ባህር ለማቋረጥ በማይውሉ ጀልባዎች ላይ ተሳፍረው ባህር ሲያቋርጡ በየዓመቱ ይሞታሉ።
የአውሮፓ ሕብረት ከሊቢያ የባህር ዳርቻ ጥበቃ ጋር በቅርበት በመተባበር ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻ የሚደርሱ ስደተኞችን ቁጥር በመቀነሱ ትችት ገጥሟታል።
በርካታ ስደተኞችም በዚህ ሳቢያ ሲመለሱ በሊቢያ እስር ቤቶች ተጨማሪ እንግልትና ስቃይ ይደርስባቸዋል።












