የዩክሬን ጦርነት፡ ፑቲን በጦር ወንጀለኛነት ለፍርድ እንዲቀርቡ ባይደን ጠየቁ

በቡቻ የመኖሪያ ህንጻ ፊትለፊት የሚታይ መቃብር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በቡቻ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈፀመው ግድያ ዓለም አቀፍ ቁጣ እየጨመረ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያ ጦር በዩክሬን ፈፀመ የተባለውን ግፍ የሚያሳይ ማስረጃ እየቀረበ በመሆኑ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦር ወንጀል እንዲከሰሱ ጠየቁ።

በዩክሬን ርዕሰ መዲና ኪዬቭ አቅራቢያ በምትገኘው ቡቻ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል መባሉ ዓለም አቀፍ ቁጣን አስከትሏል።

"ይህ ሰው ጨካኝ ነው" ሲሉ ስለ ሩሲያው ፕሬዝዳንት የተናገሩት ባይደን፤ ፑቲን "የጦር ወንጀለኛ ናቸው" ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ምንም ማስረጃ ያላቀረበችው ሩሲያ ምስሎቹ በዩክሬን የተቀናበሩ ናቸው ብላለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ማስረጃ ለመሰብሰብ ወደ ቡቻ የሚያቀናውን ዓለም አቀፍ ቡድን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የዩክሬን መንግሥት በበኩሉ በኪዬቭ አካባቢ የ410 ንፁሃን ዜጎች አስከሬን መገኘቱ ከተገለጸ በኋላ የጦር ወንጀል ምርመራ ጀምሬያለሁ ብሏል። አንዳንዶቹ በጅምላ መቃብር የተገኙ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ እጃቸው ታስሮ በቅርብ ርቀት በጥይት ተመትተው የተገደሉ ናቸው ተብሏል።

የኪዬቭ ባለሥልጣናት በአካባቢው የሚገኙትን የዩክሬይን ወታደሮች በመርዳት የከሰሷቸውን የሞቶይሂን መንደር መሪ፣ ባለቤታቸው እና ልጃቸው በሩሲያ ኃይሎች ተገድለዋል ሲሉ ከሰዋል።

"ፑቲንን የጦር ወንጀለኛ በማለቴ ትችት እንደደረሰብኝ ታስታውሳላችሁ። ቡቻ ውስጥ የሆነውን አይታችኋል። ይህም የጦር ወንጀል ነው ... ይህ በጦር ወንጀል እንዲታይ ሁሉንም ዝርዝር ማስረጃዎች መሰብሰብ አለብን።" ብለዋል ፕሬዚደንት ባይደን።

የቡቻውን የጅምላ መቃብር "አሳዛኝ" ነው ሲሉ የገለጹት ባይደን ጦር ኃይላቸው በዩክሬን ለፈጸመው ግፍ ፑቲን "ተጠያቂ ናቸው" ብለዋል።

ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል እንዳሰቡም አክለዋል።

ቡቻ በሩሲያ ጦር በተወረረበት ወቅት የቡቻ አውራ ጎዳናዎች ላይ አዲስ አስከሬኖችን የሚያሳዩ ምስሎች ማክሳር በተሰኘ የሳተላይት ምስል አቅራቢ ድርጅት ይፋ ሆነዋል።

በኒውዮርክ ታይምስ ፎቶ ትንተና መሠረት ሩሲያ ከተማዋን በተቆጣጠረበት መጋቢት 11 ቀን ቢያንስ 11 አስከሬኖች በጎዳና ላይ እንዳሉ አሳይቷል።

የሞስኮ "ሰፊና አስጨናቂ ዘመቻ" ሲል የገለጸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም በሩሲያ ኃይሎች የተፈፀሙ የአስገድዶ መድፈር፣ የማሰቃየት እና የሞት ዘገባዎች ዙሪያ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች እንዳሉት ገልጿል።

በዩክሬን ጥያቄ አቅራቢነት ዓለም አቀፍ አቃብያነ ሕጎች የዩክሬንን የጦር ወንጀል መርማሪዎችን ይደግፋሉ ተብሏል።

የሚንስትሩ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ "የቅዠት የሚመስሉ የጭካኔ ዘገባዎች እና ምስሎች ወጥተዋል" ብለዋል።

ፔንታጎን በበኩሉ በቡቻ ለተፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የሩሲያ እጅ መኖሩ ግልፅ ነው ብሏል። ተጠያቂዎቹ የትኞቹ ክፍሎች እንደሆኑ ለማጣራት ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ሰኞ ምሽት በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉበት ንግግር ሩሲያን በጦር ወንጀሎች ከሰዋል። የፑቲን አስተዳደር ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለመደበቅ እንደሚሞክርም ጠቁመዋል ።

"እርግጠኛ ነኝ የሩሲያ የፕሮፓጋንዳ አራማጆች የሩሲያ ጦር የቀረበበትን ውንጀላ ውድቅ ለማድረግ የሚሞክሩበትን የተለመደ አካሄድ እንደምታውቁ እርግጠኛ ነኝ" ሲሉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።

"አሁን ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ነው። ተመሳሳይ ውሸቶች። እውነታውን ለማጣመም እየሞከሩ ነው። ነገር ግን አይሳካላቸውም። ዓለምን በሙሉ ማታለል አይችሉም።" ብለዋል።

ፈረንሳይ እና ጀርመን ለቡቻው ግኝት ምላሽ ለመስጠት በሚል የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረራቸውን አስታውቀዋል።

የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ 40ዎቹ ልዑካን የተባረሩት ክሬምሊን በዩክሬን ላደረሰው "የማይታመን ጭካኔ" ምላሽ ነው ብለዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት "በርካታ" የሩሲያ ኤምባሲ ሠራተኞችን እንደሚያባርር ቢያስታውቅም ትክክለኛውን ቁጥር ግን አልገለጸም።

የሩሲያ ወታደሮች በዩክሬን ተፈጽሟል የተባለውን ግፍ በመጥቀስ ሊትዌኒያ የሩሲያን አምባሳደርን እያባረረች መሆኑን አስታውቃለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሞስኮ አምባሳደር በበኩላቸው ሩሲያ ለፀጥታው ምክር ቤት በቡቻ በተፈፀሙ ክስተቶች ዙሪያ የምዕራባውያን መግለጫዎችን ውድቅ የሚያደርጉ "ተጨባጭ ማስረጃዎችን" እንደምታቀርብ ተናግረዋል።

ቫሲሊ ኔቤንዚያ በኒውዮርክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት ዩክሬንን እና "ምዕራባውያን ስፖንሰሮች" ማስረጃዎችን በመፈብረክ እና በገዛ ሕዝቧ ላይ ለሐሰት ክስ ለማዋል ጥቃት ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል።

በቡቻ የሩስያ ወታደሮች በሰብአዊነት ኮሪደሮች በኩል ለቀው እንዲወጡ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በሚሸሹ ሰዎች ላይ መተኮሳቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

ቢያንስ የ20 ሰዎች አስከሬን መንገድ ላይ የተገኘ ሲሆን ብዙዎቹም ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ በቤተ መቅደስ ውስጥ በጥይት የተመቱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ታንክ እንዲሄድባቸው ተደርጓል ተብሏል።

በማክስር የተነሱ የሳተላይት ምስሎች 14 ሜትር የሚረዝም የጅምላ መቃብር በከተማዋ በሚገኙት ቅዱስ አንድሪው እና ፒየርቮዝቫኖሆ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ መኖሩን ያሳያሉ።