ነገዎ እና ጋሽ በርሄ በተገናኙ ጊዜ ምን ተባባሉ?

የፎቶው ባለመብት, Negewo Jimma Facebook
ወጣቱ ነገዎ ጅማ ከጥቂት ወራት በፊት ቢቢሲ ላይ ብቅ ባለ ወቅት ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በወቅቱም ረዥሙ ወጣት ነገዎ፤ እስካሁን በቁመት ከእኔ ጋር የሚስተካከል አላገኘሁም ብሎ ነበር።
ትንሽ ቆይቶ ደግሞ 'በቁመት ከእኔ የሚስተካከል የለም' ያሉ ጎልማሳ ከአማራ ክልል አዊ ዞን ብቅ አሉ።
ጋሽ በርሄ ቁመቴ 2ሜትር ከ50 ሴንቲ ሜትር ነው ሲሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረው ነበር።
ወጣቱ ነገዎ ደግሞ ቁመቱ 2 ሜትር ከ25 ሴንቲ ሜትር ነው ሲል ነበር ያስረዳው።
ነገዎ እና ጋሽ በርሄ በቅርቡ በአካል ተገናኝተዋል።
የሁለቱ ረዣዥም ሰዎች በአካል መገናኘት የማሕበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
ለመሆኑ ነገዎ እና ጋሽ በርሄ በተገናኙ ጊዜ ምን ተባባሉ?
ነገዎ ከሳምንታት በፊት በቁመት ከሚስተካከለኝ ሰው ጋር ብገናኝ ደስታዬ ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።
የሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ደግሞ የነገዎን ፍላጎት ያሳካች ሆናለች።
"ዩቲዩብ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ለበርሄ ቃለ መጠይቅ ሊያደርጉለት አዲስ አበባ ጠርተውት ነበር። አዲስ አበባ ሲመጣ ለምን አትገናኙም ብለው ለእኔም ደወሉልኝ" በማለት ነገዎ ያስረዳል።
"እኔ እስካሁን ድረስ ዝቅ ብዬ የማየው ሰው እንጂ ቀና ብዬ የማየው ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። በርሄ በቁመት ከእኔ እንደሚበልጥ በጣም ሲወራ ስለነበረ በቁመት የሚበልጠኝን ሰው ማየት አለብኝ ብዬ ወደ አዲስ አበባ ሄድኩ" ይላል ነገዎ።
ነገዎ አዲስ አበባ ደርሶ ከጋሽ በርሄ ጋር በተገናኙ ወቅት ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ቁመት መለካካት ማለፋቸውን ያስታውሳል።
ሁለቱ ረዣዥሞች ቁመት ከተለካኩ በኋላ፤ ነገዎ በቁመት እንደሚበልጡት የተነገረው የአዊው ጋሽ በርሄ፣ እንደሚበልጣቸው ተረዳ።
"ፎቶ ላይ እንደሚታየው ሳይሆን ትንሽ ነው የምበልጣቸው።"
ቁመታቸውን ከተለካኩ በኋላ ጋሽ በርሄ፤ " 'ቁመትህ 2 ሜትር ከ50 ሴንቲ ሜትር ነው' ለምን አሉኝ ብሎ ትንሽ እንደመበሳጨት ሆኖ ነበር" በማለት ነገዎ ይናገራል።
የሁለታችንም ቁመት ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ ነው የሚለው ነገዎ፤ እንደተባለው በቁመት በልጠውኝ ቢሆን በጣም ደስ ይለኝ ነበር ግን ሳይሆን ቀርቷል ይላል።
የጠሩን ሰዎች የጋሸ በርሄ ቁመት ለመለካታ ፈልገው የነበረ ቢሆን እሳቸው ቁመታቸው እንዲለካ ፍላጎት ስላልነበራቸው የቁመት ልዩነታችንን ማወቅ አልቻልንም ሲል ነገዎ ያስረዳል።
የስጦት ልውውጥ
ነገዎ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋሸ በርሄን በሚዲያ በተመለከታቸው ወቅት በጫማ እጦት እድሜ ልካቸውን በባዶ እግራቸው ሲሄዱ መቆየታቸውን ሲናገሩ በመስማቱ እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት ይላል።
"ሚዲያ ላይ ጫማ በማጣታቸው እግራቸው ተጎድቶ ሳይ በጣም አዘንኩ። ከዛ ወዲያው ሰዎች ከውጭ አጋር በስጦታ መልክ ከላኩልኝ ውስጥ ሁለት ጫማ ልኬላቸው ነበር" ይላል።
ጋሽ በርሄም ከአዊ ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ ስጦታ ለነገዎ ይዘው ነበር። ነገዎ ጋሽ በርሄን አዲስ አበባ ባገኛቸው ወቅት የአዊ ባህላዊ ጋቢ በስጦታ መልክ አበርክተውለታል።
ሁለቱ ረዣዥሞ በነበራቸው የአንድ ቀን ቆይታ ስለ ቁመታቸው እና ከቁመታቸው ጋር በተያያዘ ስለሚያጋጥሟቸው የዕለት ተዕለት ጉዳዮች እንዳወጉ ይናገራል።
"እኔን የሚያክል ረዥም ሰው አይተው እንደማያውቁ ነግረውኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ ትከሻ ላይ እጅ ማስቀመጥ የቻሉት እኔ ላይ ነው። እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ ትከሻ ላይ እጄን ማስቀመጥ የቻልኩት የእርሳቸው ላይ ነው።" በማለት ተሞክሮውን ያስረዳል።
ጋሸ በርሄ ከነገዎ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ሃሳባቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።













