በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ባጋጠመ የእሳት አደጋ ጉዳት ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Abdulmonam Eassa
በሱዳን በሚገኘው ዑምራኩባ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ታኅሣሥ 24/2014 ዓ. ም. ባጋጠመ የእሳት አደጋ ሳቢያ የስደተኞች መጠለያ ቤቶች እና ንብረቶች መውደማቸውን በካምፑ የስደተኞች አስተባባሪ እና የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም ለቢቢሲ ገለጹ።
ከዚህ ቀደም ሲል በታኅሣሥ መባቻ ላይ በስደተኞች መጠለያ ካምፑ ላይ በተመሳሳይ የእሳት አደጋ ተከስቶ ወደ 67 ገደማ የሚሆኑ መጠለያዎች መውደማቸው ይታወሳል።
በዑምራኩባ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የስደተኞች ኮሚቴ አስተባባሪ የሆነው ካህሳይ ገብረሚካኤል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የተከሰተው የእሳት አደጋ እሁድ ታኅሣሥ 24 ንጋት ላይ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"አንድ ስደተኛ ሴት አምሽታ ወደ መጠለያው ከገባች በኋላ እሳቱ እንደተነሳ ከስደተኞች ጥቆማ ስለደረሰን ጉዳዩ እስኪጣራ ብለን በቁጥጥር ስር አውለናታል" ብሏል።
ጉዳቱንም አስመልክቶ አስተባባሪው ሲናገር በእሳት አደጋው ሳቢያ 97 የስደተኞች መጠለያዎች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ግን የለም ብሏል።
በቤቶቹ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ የቤተሰብ አባላትም 150 እንደሚደርሱና ቃጠሎው የደረሰበት ቦታ በብዛት የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበትና በጣም የተጨናነቀ መሆኑንም ይናገራል።
"ከዚህ በፊት የእሳት አደጋ በተከሰተበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች ለአደጋ ጊዜ ወደተዘጋጀ ድንኳን እንዲገቡ ተደርጎ ነበር። አሁን በደረሰው የእሳት አደጋ ቤታቸውን ላጡ ሰዎች ግን ማቆያ ቦታ ሊገኝላቸው አልቻለም" ብለዋል።
በዚህም ምክንያት መጠለያቸው በእሳት የወደመባቸው ሰዎች እስካሁን ማረፊያ ስላልተሰጣቸው ከቤተሰብ ጋር ተጠግተው ወይም ሜዳ ላይ የሚያድሩ የስደተኞቹ አስተባባሪ ያጋጠማቸውን ችግር አስረድቷል።
የእርዳታ ድርጅቶቹ ማቆያ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም በአካባቢው የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር እና የተገነቡ መጠለያዎች ቁጥር በእርዳታ ድርጅቶች ከተመዘገበው በላይ ነው መባላቸውንም ለቢቢሲ ገልጿል።
የእርዳታ ድርጅቶች ከመዘገቧቸው ስደተኞች በላይ እና በሕጋዊነት ከገነቧቸው መጠለያዎች በላይ እንዳገኙ እንደተነገራቸው የገለጸው አስተባባሪው የስደተኞች ቁጥር ከመዘገቡት በላይ በመሆኑ ምክንያት ድጋፍ መስጠት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
"ቦታው የንግድ ቦታ ስለሆነ ለሥራ የመጡ ሰዎችም ተጨምረውበት ካልሆነ በስተቀር የስደተኞች ቁጥር ይህን ያህል አይደለም ብለዋል። ስለዚህም ትክክለኛውን የስደተኞች ቁጥር አጣርታችሁ አምጡልን ብለዋል። ቁጥሩን አጣርታችሁ ካልመጣችሁ ድጋፍ መስጠት አንችልም ብለውናል" በማለትም አስረድቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) የሱዳን ቃል አቀባይ የሆኑት ጁልያ ራፋኤሊ ስለ እሳቱ መነሻ ቢቢሲ የጠየቃቸው ሲሆን የታማኝ ምንጮችን ሪፖርት ዋቢ አድርገው እሳቱ የተነሳው በድንገት እንደሆነ ገልጸዋል።
ሆኖም ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግና አደጋ መከላከያ እርምጃዎችን የሚያጠናክር የቴክኒክ ቡድን መሰማራቱንም ጠቅሰዋል።
"ዑምራኩባ ውስጥ እንዲህ ያለ አደጋ ሲከሰት ይህ ሁለተኛው ነው። ሁለቱም በድንገት የተነሱ ናቸው። የሰው ሕይወት አልጠፋም። የአካል ጉዳትም አልደረሰም" ብለዋል።
ነገር ግን በእሳት አደጋዎቹ የስደተኞች መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ወደ 70 መጠለያዎች መውደማቸውን ያስረዳሉ።
ዩኤንኤችሲአር እንደ ኮር፣ ኬር፣ ኤንአርሲ ካሉ አጋሮቹ ጋር መጠለያቸውን እና ንብረታቸውን በእሳት ላጡት ስደተኞች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸው "የጠፉባቸውን ሰነዶች ለመመለስ እና የድንገተኛ ጊዜ ማቆያ ለመስጠት እየሞከርን ነው" ብለዋል።
በቀጣይ ተመሳሳይ እሳት አደጋ እንዳይከሰት የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ድርጅቱ በእያንዳንዱ የስደተኞች ካምፕ የእሳት አደጋ መከላከያ ለማቋቋም እየተሞከረ መሆኑን ቃለ አቀባዩዋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም በካምፖቹ ውስጥ በሚገኙ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የእሳት አደጋ ማጥፊያ እንደሚዘጋጅና ታኅሣሥ ወር በዑምራኩባ ካምፕ የእሳት አደጋ መከላከያ ስልጠና ተሰጥቷል። ከዚህም በኋላ ተጨማሪ ስልጠናዎች እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
በአደጋው ቤታቸውን ያጡ ስደተኞች ቋሚ መጠለያ እስከሚሰጣቸው በጊዜያዊ ማቆያ እንደሚኖሩና 10 ቤተሰቦች በዚያው አካባቢ ሌላ መጠለያ እንደሚሰራላቸው እንዲሁም ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሌላ የካምፑ አካባቢ እንደሚዛወሩም አስረድተዋል።
ከሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከኢትዮጵያ ሸሽተው ወደ ሱዳን የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ60 ሺህ በላይ እንደሆነ ዩኤንኤችሲአር አስታውቋል።
ባለፉት ሳምንታት ከኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር መቀነሱን የሚናገሩት ቃለ አቀባይዋ በታኅሣሥ ወር የመጨረሻው ሳምንት ውስጥ 38 ሰዎች ወደ ሐምዳይት ካምፕ፣ 21 ሰዎች ደግሞ ገዳሪፍ ግዛት ወደሚገኝ ካምፕ መግባታቸውን አስረድተዋል።
ሁሉም ስደተኞች ከድንበሩ ራቅ ባለ አካባቢ ላይ ሰፍረው መመዝገባቸውንም አክለው ገልጸዋል።












