ለወራት ተዘግቶ የነበረው የኢትዮ-ሱዳን መንገድ ተከፈተ

የመተማ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Mulugeta Ayene/AP

የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ላለፉት ስድስት ወራት ተዘግቶ የቆየው እና አገራቱን የሚያስተሳስረው የጋላባት- መተማ ዋና መንገድ መከፈቱን የምዕራብ ጎንደር አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለቢቢሲ ተናገሩ።

በትናንትናው ዕለት ታኅሣሥ 26/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ በኩል በዞኑ አስተዳዳሪ የሚመራና ወታደራዊ አመራሮችን ያካተተ ቡድን፣ በሱዳን በኩል ደግሞ በሁለት የሱዳን ጦር ብርጋዴየር ጄነራሎች የተመራ ቡድን በምዕራብ ጎንደር መተማ ዮሐንስ ከተማ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ድንበሩ መከፈቱን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ይህንን መንገድ በሱዳን በኩል ወይም በጋላባት አስተዳደር ከስድስት ወራት በፊት በመዝጋቱ የድንበር እንቅስቃሴው ተቋርጦ እንደቆየም ተገልጿል።

ታዲያ ከምክክሩ በኋላ ተዘግቶ የነበረው ድንበር ተከፍቶ የሰዎች እና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዲሁም የንግድ ልውውጡም እንደተጀመረ አቶ ደሳለኝ ጠቅሰዋል።

የመተማ ዮሐንስ ኮሙኒኬሽን በበኩሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ የሱዳን ጉምሩክ ኃላፊ አህመድ ሰኢድን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረው ከባድ የጭነት ማጓጓዣዎች ገብተው የንግድ ልውውጥ እየተደረገ ነው።

ከድንበር ጉዳይ ባለፈ በውይይቱ የአገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያስገኙ ትስስሮች "በየጊዜው የሚከፈት የሚዘጋ ሆኖ ለምን ይቀጥላል በሚል አንድ የጋራ አጀንዳ" ላይ ምክክር መደረጉንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት ሱዳን "የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ወታደራዊ ቦታን የማስፋፋት ተግባር መቆም ቢችል፣ የድንበሩ ጉዳይ በድንበር ኮሚሽን ቢታይ" በሚል አጀንዳ እና "በስደተኛ ካምፕ ስም ኢትዮጵያን የሚጎዱ ፅንፈኛ ኃይሎች" በሱዳን መኖራቸው በተመለከተ ምክከር እንደተደረገም ገልጸዋል።

"በአጀንዳዎቹ በሱዳን ወገን ያሉት ተስማምተዋል፤ ውይይትና ድርድር የማድረግ የኛ ሥልጣን ሆኖ ሳይሆን ከሰላም እና ደኅንነት ጋር ተያይዞ ድንበር ላይ ያለው ጉዳይ ተጨማሪ ቀውስ እንዳይከተል በእነሱ በኩል መታረም ያለባቸው ነገሮች እንዲታረሙ፣ በኛም የሚታዩ ነገሮች ካሉ እንዲያነሱ ነበር" በማለት አጀንዳዎቹን አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

አቶ ደሳለኝ የተከፈተው የጋላባት- መተማ ዋና መንገድ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩ ሲሆን፣ በሳምንታት ውስጥ አካባቢው ወደቀደመ እንቅስቃሴው ይመለሳል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለው ገልጸዋል።

አገራቱ ከነበሩበት ውጥረት ተላቀው ውይይት መጀመራቸው በጎ ጀምር እንደሆነ የጠቀሱት አስተዳዳሪው በአገር አቀፍ ደረጃም መወያየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ባህላዊና ታሪካዊ ትሰስር የጠቀሱት የሱዳኑ የጦር መሪ ብርጋዲየር ጀነራል በሽር ሰኢድ፣ የአገራቸው ፍላጎት ከድንበር ከተሞች በዘለለ እስከ አዲስ አበባና ካርቱም ድረስ ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሆነ ተናግረዋል።

"የንግድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አይተናል ነገር ግን በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ የድንበር አካባቢ ሕዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲቀጥል እኛም ፍቃደኛ ነን" ማለታቸውም በማኅበራዊ ገጹ ላይ ሰፍሯል።

የሱዳን ጉምሩክ ኃላፊ አህመድ ሰኢድ በበኩላቸው የሁለቱ አገር ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ መከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ሚኒሻ በጥምረት አካባቢውን በመጠበቅና የሕዝቦቹንም ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ይገባኛል ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ቢሆን በትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አገራቱ ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ አምርተዋል።

ሱዳን በትግራይ ክልል ግጭት ከተነሳበት ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ከጥቅምት 27/2013 ዓ.ም ያላግባብ የያዘችውን መሬት ትልቀቅና ወደ ንግግር እንግባ የሚል ሃሳብ ኢትዮጵያ ስታነሳ ቆይታለች።

ሱዳን በበኩሏ የአገራቸው ሠራዊት ግዛቴ ነው ከሚላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠሩንና ይህም የማይቀለበስ እርምጃ መሆኑን ትገልጻለች።

ኢትዮጵያ ይህ የሱዳን እንቅስቃሴ "የሌሎች ኃይሎች" ፍላጎት ማስፈጸሚያ ነው በሚል በተደጋጋሚ የምትጠቅስ ሲሆን ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ የግዛቶቿ አካል የሆኑ መሬቶችን እንደወሰደች ትከሳለች።

በቅርቡም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት ድንበር ላይ ተጨማሪ ወታደሮችን ማስፈሯን አስታውቃለች።

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ውጥረት እንደቀጠለ ቢሆንም ቀጠናው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነም የሱዳን ጦር አመራሮች አስረድተዋል።

ሱዳን ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ባስታወቀችው መሰረት በአወዛጋቢው አል ፋሽቃ አካባቢ የሰፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ አካባቢውን መቆጣጠሯንና ወታደሮቹንም ከጥቅም ውጭ ማድረጓን አስታውቃለች።

ድል መቀናጀቷን ከማወጇ ከአራት ቀናት በፊት አወዛጋቢ በሆነው ብርካት ኑራይን በተባለ አካባቢ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በተፈጠረ ግጭት 21 የሱዳን ወታደሮች ሲገደሉ 30 ሰዎች ቆስለዋል የሚል ዘገባም ወጥቶ ነበር።

ሱዳን በኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቃት እንደተፈጸመባትና ወታደሮች እንደተገደሉባት ባሳወቀችበት ወቅት ኢትዮጵያ ግን ክሱን ማስተባበሏ ይታወሳል።

በወቅቱም የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የአገሪቱ ሠራዊት ጥቃት አለመፈጸሙን ነገር ግን በድንበር በኩል ሰርገው ለመግባት በሞከሩ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ይህ አገራቱን እስከ ወታደራዊ ግጭት የከተተ አለመግባባት እና ክፉኛ የሻከረው ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በይፋ ሳይገለጽ፣ ከሳምንታት በፊት በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀዳም ያደርጉት የነበረውን መደበኛ ምክክር አድርገው ነበር።

ይህ ከሆነ ከ10 ቀናት በኋላ ነው በምዕራብ ጎንደር ዞን ትላንት ማክስኞ ውይይት ተደርጎ አገራቱን የሚያስተሳስር መንገድ የተከፈተው።

line

ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ይዞታ ስር ከነበሩት፣ ሱዳን ይገባኛል ከምትለውና በሠራዊቷ ከሚጠበቀው አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ነበር ሱዳን ቦታውን በኃይል የተቆጣጠረችው።

በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች ለመፈናቀል ከመዳረጋቸው በተጨማሪ የእርሻ ስፍራዎች ላይ ውድመት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ላይ ደግሞ ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

ኢትዮጵያ የሱዳን ሠራዊት ከያዛችው ቦታዎች በመውጣት ለዓመታት ሲካሄድ ወደነበረው ውይይት እንድትመለስና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ብትጠይቅም፣ ከሱዳን በኩል ምላሽ ሳያገኝ እስካሁን ቆይቷል።

የአልፋአካባቢ

ሱዳንና ኢትዮጵያ በይገባኛል ከሚወዛገቡበት አካባቢ በተጨማሪ ረዥም የጋራ ድንበር ይጋራሉ። ሁለቱም አገሮች አወዛጋቢውንና ለም ነው የሚባለውን አልፋሽቃ አካባቢ በእጅጉ ይፈልጉታል።

ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።

በዚህ ድንበር በሁለቱም ወገን የሚገኙ ገበሬዎች ለም መሬቱ ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን ከሱዳን በስተምሥራቅ ከኢትዮጵያ ደግሞ በስተምዕራብ የሚገኝ ለእርሻ አመቺ በተለይ ደግሞ ለቅባት እህሎች ምርት የሚውል ለም መሬት የያዘ ቦታ ነው።

አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞች በቅርብ ይገኛሉ።

የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። ታዲያ በኢትዮጵያውያን እጅ ለምን ቆየ ሲባሉ፣ "የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን እያለሙት የነበረው" ይላሉ።

በኢትዮጵያ በኩልም ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ለዘመናት በቦታው ሰፍረው እያረሱ የኖሩበት የአገሪቱ ግዛት መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን እርምጃ "ወረራ" ሲሉ ይገልጹታል።

ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር ለመለየትና ለማካለል፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ቀደም ሲል የነበረው አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ሉአላዊ መሬት ለሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ተስማምቷል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ቢቆይም ይዞታው በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ስር ቆይቷል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳውቁ መመሪያ አስተላልፈው ነበር።

ሆኖም ግን አወዛጋቢውን ድንበር ለዓመታት መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ፣ ሁለቱም መሪዎች ከስልጣን ለቀው ሱዳን አካባቢውን በኃይል ተቆጣጥራዋለች።