ሱዳን ጥቃት ተፈጽሞ ወታደሮቼ ተገደሉ ስትል ኢትዮጵያ አስተባበለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዳን በኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቃት እንደተፈጸመባትና ወታደሮች እንደተገደሉባት ስታስታውቅ ኢትዮጵያ ግን ክሱን አስተባብላለች።
የሱዳን ዜና ወኪል ሱና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በአልፋሽቃ አካባቢ በተሰማራው የሱዳን ሠራዊት ላይ የኢትዮጵያ ጦርና ሚሊሻ ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ግን የአገሪቱ ሠራዊት ጥቃት አለመፈጸሙን ነገር ግን በድንበር በኩል ሰርገው ለመግባት በሞከሩ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ሮይትርስ የዜና ወኪል ደግሞ የሱዳን ወታደራዊ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ቅዳሜ ዕለት ተፈጸመ በተባለው ጥቃት ስድስት የሱዳን ወታደሮች ተገድለዋል።
የሱዳን ጦር ኃይሎች ባወጣው መግለጫ ላይም ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ወታደሮች መገደላቸውን ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ ወገንም ጉዳት መድረሱንና ጥቃቱን መክተው መመለሳቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከሱዳን በኩል የቀረበውን ክስ አጣጥለው፣ አገራቸው ጥቃት አለመፈጸሟን ገልጸዋል።
ጄነራሉ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ ሱዳንን አላጠቃችም፣ ጥቃት የምትፈጽምበት ምክንያት የለም" ሲሉ ሱዳን ተፈጸመብኝ ያለችውን ጥቃት ውድቅ አድርገውታል።
በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ውዝግብ እንዳለ ያስታወሱት ኤታማዦር ሹሙ፣ ይህም በሕጋዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት አመለክተው "መሬታችን በሰላም፣ በሕግና በድርድር ይመለሳል ብለን ስለምናስብ፣ በዚህ ወቅት ሱዳንን የምናጠቃበት ሁኔታ ላይ አይደለንም" ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ከሱዳን በኩል የመተናኮል ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን የተቀሱት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ከሱዳን በኩል ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንደሚደረግና "የሕዳሴው ግድብ ግንባትን ለማደናቀፍ እየሰራች መሆኑን እናውቃለን" ሲሉ ከሰዋል።
በዚህም ምክንያት "እነሱ የላኳቸው ኃይሎች እየመጡ እየደመሰስናቸው ነው። የራሳችንን ተላላኪዎች መደምሰስ እንጂ ለምን ትልካላችሁ ብለን ከእነሱ ጋር ውዝግብ፣ ግጭትም ሆነ ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም" ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ከሱዳን በድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው ለመግባት የሞከሩ አሸባሪዎችን የመከላከያ ሠራዊቱና የአካባቢው ሚሊሻ እርምጃ ወስዶ መደምሰሳቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ውጪ በሱዳን ወታደሮች ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥቃት ፈጽሟል በሚል የቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ ለገሰ (ዶ/ር) ውድቅ አድርገውታል።
የሱዳን መንግሥት ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመው ኢትዮጵያና ሱዳን ለረጅም ዓመታት በይገባኛል ሲወዛገቡበት በቆየውና ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ ሱዳን ሠራዊቷን አሰማርታ በኃይል በያዘችው ለም በሆነው የአልፋሽቃ አካባቢ ነው።
ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ በስፍራው ሠራዊቷ ጥበቃ እንዲያደርግ በተሰማራበት ጊዜ የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት መፈጸማቸውን የሱዳን ጦር ኃይል አመልክቷል።
"በአርሶ አደሮች ላይ ስጋትን በመፍጠር የመኽር ጊዜውን ለማደናቀፍ ወደ ግዛታችን በመግባት ጥቃት ተፈጽሟል" በማለት ጥቃቱን መመከታቸውን እንዲሁም ከሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን ገልጿል።

ጥቅምት 2013 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ይዞታ ስር ከነበሩት፣ ሱዳን ይገባኛል ከምትለውና በሠራዊቷ ከሚጠበቀው አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ወታደሮቿን ማስወጣቷን ተከትሎ ነበር ሱዳን ቦታውን በኃይል የተቆጣጠረችው።
በዚህም በርካታ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች ለመፈናቀል ከመዳረጋቸው በተጨማሪ የእርሻ ስፍራዎች ላይ ውድመት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ላይ ደግሞ ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
ኢትዮጵያ የሱዳን ሠራዊት ከያዛችው ቦታዎች በመውጣት ለዓመታት ሲካሄድ ወደነበረው ውይይት እንድትመለስና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ አንዲፈለግ ብትጠይቅም፣ ከሱዳን በኩል ምላሽ ሳያገኝ አስካሁን ቆይቷል።
የአልፋሽቃ አካባቢ
ሱዳንና ኢትዮጵያ በይገባኛል ከሚወዛገቡበት አካባቢ በተጨማሪ ረዥም የጋራ ድንበር ይጋራሉ። ሁለቱም አገሮች አወዛጋቢውንና ለም ነው የሚባለውን አልፋሽቃ አካባቢ በእጅጉ ይፈልጉታል።
ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።
በዚህ ድንበር ሁለቱም ወገን የሚገኙ ገበሬዎች ለም መሬቱ ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን ከሱዳን በስተምሥራቅ ከኢትዮጵያ ደግሞ በስተምዕራብ የሚገኝ ለእርሻ አመቺ በተለይ ደግሞ ለቅባት እህሎች ምርት የሚውል ለም መሬት የያዘ ቦታ ነው።
አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞች በቅርብ ይገኛሉ።
የሱዳን ባለሥልጣናት አልፋሽቃ የሱዳን ግዛት ነው ይላሉ። ታዲያ በኢትዮጵያውያን እጅ ለምን ቆየ ሲባሉ፣ "የሱዳን መንግሥት ከአገሪቱ ጋር ባለው የትብብርና የመግባባት ስምምነት መንፈስ ነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች ቦታውን እያለሙት የነበረው" ይላሉ።
በኢትዮጵያ በኩልም ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ለዘመናት በቦታው ሰፍረው እያረሱ የኖሩበት የአገሪቱ ግዛት መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን እርምጃ "ወረራ" ሲሉ ይገልጹታል።
ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር ለመለየትና ለማካለል፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
ቀደም ሲል የነበረው አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ሉአላዊ መሬት ለሱዳን ቆርሶ ለመስጠት ተስማምቷል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ቢቆይም ይዞታው በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ይዞታ ስር ቆይቷል።
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያሳውቁ መመሪያ አስተላልፈው ነበር።
ሆኖም ግን አወዛጋቢውን ድንበር ለዓመታት መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቶ፣ ሁለቱም መሪዎች ከስልጣን ለቀው ሱዳን አካባቢውን በኃይል ተቆጣጥራዋለች።















