ከአዲስ አበባ ኮምቦልቻ ተቋርጦ የነበረው በረራ ሊጀመር ነው

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines facebook
ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ/ደሴ ተቋርጦ የነበረው በረራ ከታኅሣሥ 27/2014 ዓ.ም ሊጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
አየር መንገዱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አክሎ እንዳሰፈረው ከተጠቀሰው ዕለት ጀምሮ በየቀኑ በረራዎች እንደሚኖሩ ነው።
የደቡብ ወሎ ከተሞች የሆኑት ደሴና ኮምቦልቻ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነበር አየር መንገዱ ወደ ኮምቦልቻ የሚያደርገውንና ሁለቱን ከተሞች የሚያገለግለውን በረራ አቋርጦ የነበረው።
አየር መንገዱ በኮምቦልቻ አየር ማረፊያ የሚያደርጋቸውን የየቀኑ በረራዎች ለሁለት ወራት ያህል አቋርጦ ነበር።
ከኮምቦልቻ በተጨማሪ በላሊበላ ለወራት ተቋርጦ የነበረው በረራም በትናንትናው ዕለት ታኅሣሥ 25/2014 ዓ.ም መጀመሩን አየር መንገዱ በተጨማሪ ገልጿል።
በህወሓት ቁጥጥር ስር በነበሩ ከተሞች የመብራት፣ ውሃና ስልክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን መንግሥት እነዚህን ከተሞች በስሩ ማድረጉን ተከትሎ የመብራትና፣ ውሃና ስልክ አገልግሎት ተመልሷል።
በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞችም እንዲሁ ተቋርጦ የነበረው ኢንተርኔት አገልግሎት (ዳታ) መመለሱንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተመለሱ ሲሆን ትራንስፖርት በአንዳንድ አካቢዎች መጀመሩም ተነግሯል።
የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውንም ቢቢሲ ከነዋሪዎች በሰበሰው መረጃ መረዳት ችሏል።
ከጦርነቱና ትራንስፖርት መገደብ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ ንሮ የነበሩ መሰረታዊ ሸቀጣሸቀጦች ዋጋም በተወሰነ መልኩ መቀነስ እንዳሳየም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅትም በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች ለምሳሌ በሰቆጣ ከተማና አካባቢው የመብራትና ውሃ አገልግሎት አሁንም እንዳልተመለሰ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክና የባንክ አገልግሎቶች አሁንም እንደተቋረጡ ናቸው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ከአስራ አራት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት ቢያደርጉም ፍሬ አላፈራም።












